1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

እስር በዎላይታ ሶዶ

ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ዓርብ፣ መጋቢት 12 2017

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዎላይታ ዞን የዩኒቨርሲቲ መምህራንና የሕግ ጠበቆችን ጨምሮ ሰዎች በጅምላ እየታፈሱ ነው ሲሉ ነዋሪዎች እና የታሳሪ ቤተሰቦች ተናገሩ።

የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ
የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ፎቶ ከማኅደርምስል፦ Wolaita Sodo University

እስር በዎላይታ ሶዶ

This browser does not support the audio element.

እስር በዎላይታ ሶዶ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዎላይታ ዞን የዩኒቨርሲቲ መምህራንና የሕግ ጠበቆችን ጨምሮ ሰዎች በጅምላ እየታፈሱ ነው ሲሉ ነዋሪዎች እና የታሳሪ ቤተሰቦች ተናገሩ። የታሠሩ ሰዎች መኖራቸውን ለዶቼ ቬለ ያረጋገጡት የዎላይታ ዞን ፍትህ መምሪያ ሀላፊ በበኩላቸው የታሰሩት ሐሰተኛ መረጃን በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በማሠራጨት ወንጀል ተጠርጥረው ነው ብለዋል። ከሀዋሳ ሸዋንግዛው ወጋየሁ ዝርዝር ዘገባ አለው  

እስር በዎላይታ ሶዶ

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዎላይታ ዞን ዎላይታ ሶዶ ከተማ በርካታ ሰዎች እየታሠሩ ይገኛሉ። የሰዎቹ እስር እየተካሄደ የሚገኘው አንዳንዶቹ ከመኖሪያ ቤታቸው ሌሎች ደግሞ ከመንገድ ላይ እየተያዙ መሆኑን የከተማይቱ ነዋሪዎች ይናገራሉ። ለእስር ከተዳረጉት መካከል የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ መምህራን እና የሕግ ጠበቆች እንደሚገኙበት ነዋሪዎቹ ጠቅሰዋል።

«ፖለቲካ ተናግሯል»

የቤተሰብ አባሎቻቸው የተያዙት በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሳይሆን ቤት ለቤት በተደረገ አሰሳ መሆኑን ሁለት የታሳሪ ቤተሰቦች ተናግረዋል። የጥብቅና ባለሙያ የሆነው የወንድማቸው ልጅ የክልሉን አመራሮች በፌስ ቡክ ተችተሃል ተብሎ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ መታሠሩን ለዶቼ ቬለ የተናገሩ አንድ ቅሬታ አቅራቢ «በትርፍ ጊዜው በፌስ ቡክ እና ቲክቶክ ገጹ ላይ በክልሉ ስለሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች የራሱን አስተያየት ከመግለጽ ውጪ የግለሰቦችን ሥም ጠቅሶ አያውቅም። ነገር ግን የፀጥታ አባላት የክልሉን አመራሮች ተናግረሃል በሚል አስረውታል» ብለዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዎላይታ ዞን በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሀሰት መረጃ በማሰራጨት በሚል በርካቶች መታሰራቸውን እማኞች ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል።ፎቶ ከማኅደርምስል፦ Shewangizaw Wegayehu/DW

ወንድማቸው መጋቢት 8 ቀን 2017 ዓም እኩለ ሌሊት ላይ በፀጥታ አባላት ለጥያቄ ትፈለጋለህበሚል መወሰዱን የጠቀሱት ሌላኛዋ ቅሬታ አቅራቢ ደግሞ «በወቅቱ ከሚመለከታቸው የፍትህ አካላት የመጥሪያም ሆነ የብርበራ ወረቀት ሳይዙ ነው ወስደው ያሰሩት፤ በማግሥቱ የተያዘው ፖለቲካ ተናግሯል በሚል መሆኑን ከሌሎች ሰዎች  ሰማን።፡ አሁን ላይ ወንድማችንን ማግኘትም ሆነ የታሠረበትን ቦታ እንኳን ማወቅ አልቻልንም» ሲሉ ተናግረዋል።

የጥላቻ ንግግር

ታሥረዋል የተባሉ ሰዎችን አስመልክቶ በዶቼ ቬለ የተጠየቁት የዎላይታ ዞን ፍትህ መምሪያ ሀላፊ አቶ እንዳሻው አባተ በከተማው የጥላቻ ንግግር ሲያደርጉ ተደርሶባቸዋል ያሏቸው ሰባት ሰዎች መታሠራቸውን አረጋግጠዋል። ተጠርጣሪዎቹ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም በተንቀሳቃሽ ምስል እና በጽሑፍ ሀሰተኛ መረጃዎችን ሲያሰራጩ ነበር የሚሉት አቶ እንዳሻው «መልዕክቶቻቸው በሕዝቦች መካከል ቅሬታ እና ቁጣን ሊቀሰቅሱ የሚችሉ ናቸው። አሁን ፖሊስ ማስረጃዎችን በማሰባሰብ ምርመራውን አጠናቋል» ብለዋል።

ቤተሰቦቻቸው ተጠርጣሪዎቹ «የታሰሩብን የክልሉን አመራሮች በመተቸታቸው ነው ይላሉ» ለዚህ ምን ምላሽ አልዎት በሚል በዶቼ ቬለ የተጠየቁት አቶ እንዳሻው «የታሠሩት ትችት በማቅረባቸው አይደለም። አሁን ጉዳዩን መዘርዘር አልፈልግም። ነገር ግን ትችት በማቅረባቸው አለመታሠራቸውን እነሱ ራሳቸው ያውቁታል። የተያዙትም ከፍርድ ቤት የማያዣ ትዕዛዝ ወጥቶ ነው። ፍርድ ቤቱ የሚሰጠው ውሳኔ ሁላችንንም የሚገዛ ይሆናል» ነው ያሉት።

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW