እንቦጭን የማስወገዱ ዘመቻና ዘላቂው መፍትሄ
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 10 2013
ጣና በመጤ አረም መወረሩ የብዙዎች መነጋገሪያና ስጋት መሆኑ ከታየ ከረመ። በተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ የዕፅዋትና የአካባቢ መስተጋብር ተመራማሪ እንደሚሉት ግን የጣና ችግርም ሆነ ስጋት እምቦጭ ብቻ አይደለም። ኅብረተሰቡን ያሳተፈ የእምቦጭ ለቀማ ትናንት በይፋ ተጀምሯል። ዘመቻው ለአንድ ወር የሚዘልቅ ነው። ለዘለቄታቸው ጣናን ከእምቦች አረም ይታደገው ይሆን? የብዙዎች ጥያቄ ነው።
ከሦስት ዓመት በፊት በዚሁ መሰናዶ ስለጣና በመጤ የውኃ ላይ አረም መወረር ስናወሳ የብዙዎችን ትኩረት እንዲስብ ነበር። እርግጥም ጉዳዩ መነጋገሪያ ሆነና የሀገር አድባር የሆነውን የጣናን ሐይቅ ከገጠመው አደገኛ ወራሪ ለማዳን ብዙዎች ተንቀሳቀሱ። ወጣቶች በማኅበር ተሰባስበው ለነቀላው ወጡ፣ የቴክኒኩ ተሰጥኦና ዕውቀት ያላቸው ማሽን ለመሥራት በዚሁ ለማገዝ ተሰለፉ፣ በውጭ የሚገኙ ወገኖች ገንዘብ አሰባስበው በሌላው ዓለም ሥራ ላይ ውሎ ውጤት አስገኝቷል ያሉትን ማሽን ለመግዛት ተረባረቡ፣ ምሁራን በጥናት ምርምራቸው ይህን አረም ለማጥፋት ይበጃል ያሉትን ውጤት አበረከቱ። ጣና ዛሬም ከቀበኛው እንቦጭ አልተላቀቀም። ባለፈው ዓመት እንደም ባሰበት ተባለ። ትናንት ደግሞ አዲስ ተስፋ የሰነቀ ዘመቻ ተጀመረ። እንቦጩን ለማስወገድ። በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጎንደር ዙሪያ ወረዳ ምጥራ ጽዮን ማሪያም በተባለች ቀበሌ ብዙዎችና ያሳተፈው የእንቦጭ ነቀላ ዘመቻ ሲጀመር በስፍራው ተገኝቶ የተመለከተው የባሕር ዳሩ ዘጋቢያችን ዓለምነው መኮንን ያስተዋለውን እንዲያጋራን ጠየኩት።
«በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ ነበሩ። ሰዎችም ከተለያዩ አካባቢ እየመጡ ሢሠሩ ነበር። እንግዲህ ትናንት የተገነዘብኩት የእንቦጭ አረምን ማስወገድ የሚቻለው በሰው ኃይል ብቻ ነው። ሌላው ተሞክሮ ብዙም ውጤታማ አልሆነም።»
በተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ የዕፅዋትና የአካባቢ መስተጋብር ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ዓለማየሁ ዋሴ ከዚህ ቀደም እንቦጭን ከጣና ሐይቅ ላይ ለማስወገድ የተካሄዱ ጥረቶች፤ አረሙን አላጠፉም በሚል ሊናቁ አይገባም ነው የሚሉት። ዋናው ነገር የማጥፋቱ ጥረት እና የእንቦጭ የመንሰራፋት አቅም ተመጣጣኝ መሆን እንዳለበትም አጽንኦት ይሰጣሉ። እንቦጩን ለማስወገድ ኬሚካል መጠቀም የሚለውን ሃሳብ ለብዝሃ ሕይወትና ስነምህዳር ጥንቃቄ ከማድረግ አኳያ በግሌ አልመርጠውም የሚሉት ዶክተር ዓለማየሁ በሰው ኃይል ርብርብ የሚደረገው ጥረት ቀጣይነት ካለው ተመራጭ ነው ባይ ናቸው።
በዘመቻም ሆነ በየትኛውም መንገድ ውሎ አድሮ እምቦጭ ለጣና ሐይቅ ስጋት መሆኑ ቢቀር እንኳ ሌሎች አሳሳቢ ችግሮች በዙሪያው እንዳሉም ባለሙያው ያነሳሉ። እንዲያም ሆኖ ባለሙያው ዘንድሮ ተፈጥሮ ተራድታ ሐይቁ በውኃ ሞልቶ እንቦጩ ወደዳር በመገፋቱ ጥረቱ ሳያሰልስ ቀጥሎ የተሳካ ውጤት እንደሚገኝ ተስፋ አላቸው። ሥራውን በተመለከተም የሙያን ጉዳይ ለባለሙያ ይተው ሲሉም ይመክራሉ። አረሙን ለማጥፋት የሚደረገውን ጥረት የሚያስተባብረውን ኤጀንሲ በሚያስፈልገው ሁሉ መደገፍ እንደሚገባም ዶክተር ዓለማየሁ አሳስበዋል። እንቦጭ አሁን በሰሜንና ምሥራቃዊ የጣና ሐይቅ ዳርቻ ላይ እንደሚገኝ ነው ዶክተር ዓለማየሁ የገለፁልን። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በተጠቀሰው አቅጣጫ ወደ ሐይቁ የሚገቡ ወንዞች ማዕድን ይዘው ስለሚገቡ፣ የንፋሱ አቅጣጫም ከምዕራብ ወደምሥራቅ መሆኑ ወደዳር ስለሚገፋው፣ጥልቀቱም ቢሆን በዚህ በኩል አነስተኛ ስለሆነ መሆኑንም አስረድተዋል። አረሙ በተጠቀሰው የጣና ሐይቅ አካባቢ የሚገኙ አርሶ አደሮችን እንዲሁም ዓሣ አስጋሪዎችን የዕለት ተዕለት ሕይወት ከመፈታተኑ በተጨማሪ ታሪካዊ ገዳማትን እንቅስቃሴ ላይም ተፅዕኖ ፈጥሯል። ትናንት በተጀመረው አረሙን በሰው ኃይል ከሐይቁ ላይ የማስወገድ ዘመቻ ብዙዎች በመሳተፍ ሌሎችንም እየጋበዙ ነው። ተመሳሳይ ዘመቻ ተከታትሎ መደረጉ ባለሙያው እንደመከሩት ዘንድሮ የተለፋበትን ውጤት በቀጣይ ዓመታት እውን የማድረግ አቅም ይኖረዋል ተብሎ ይታሰባል። መሰል ጥረትም እምቦጭ ባዳረሳቸው ለቆቃ፣ ሻላ እና አብያታ ሐይቆችም ማድረግ ያለውን የውኃ ሐብት በአግባቡ ጠብቆ ለመጠቀም እንደሚረዳ ይታመናል። ለሰጡን ሙያዊ ማብራሪያ ዶክተር ዓለማየሁ ዋሴን እንዲሁም ያስተዋለሁን ያጋራንን የባሕር ዘጋቢያችንን በማመስገን እናብቃ።
ሸዋዬ ለገሠ
አዜብ ታደሰ