1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

እንቦጭ አረም ጣና ሐይቅ ላይ መንሰራፋቱ

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 18 2016

በጣና ሐይቅ ላይ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም የማስወገድ ሥራ በዚህ ዓመት ባለመከናወኑ አረሙ እንደገና በሐይቁ ላይ እየተስፋፋ መሆኑን የአካባቢው አርሶ አደሮችና ባለሙያዎች ተናገሩ። አረሙ ምን ያህል በሐይቁ ላይ እንደሰፋም ለማወቅ የአለው ወቅታዊ የሰላም ሁኔታ ልኬታ ለማካሄድ አልተቻለም ተብሏል።

በእንቦጭ አረም የተወረረው የጣና ሐይቅ፤ ፎቶ ከማኅደር
በእንቦጭ አረም የተወረረው የጣና ሐይቅ፤ ፎቶ ከማኅደርምስል፦ Alemneh Mekonnen/DW

እንቦጭ አረም ጣና ሐይቅ

This browser does not support the audio element.

እምቦጭ አረም ወይም በሳይንሳዊ መጠሪያው (Water hyacinth) በጣና ሐይቅ ላይ መታየት የጀመረው በ2004 ዓ ም ጀምሮ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ። የአረሙን ተፅዕኖ ለመከላከልና የሐይቁን ህልውና ለመታደግ በተለይም ከጥቅምት 2013 ዓ ም ጀምሮ ሰፊ ህዝባዊ ንቅናቄ ተፈጥሮ ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል። በመሆኑም የአረሙ አብዛኛው ክፍልም ተወግዶ እንደነበር በወቅቱ በተደጋጋሚ ተገልጧል።

የኮቪድን ስርጭት፣ የህልውና ዘመቻውንና አሁን ደግሞ የክልሉን ወቅታዊ የሰላም ሁኔታ ተከትሎ ግን አረሙን የማስወገድ ሥራው መቀዛቀዙን፣ ከዚያም ከነአካቴው መቆሙን ነው አስተያየት ሰጪዎቹ የሚናገሩት። በሐይቁዙሪያ ምሥራቅ ደንቢያ ከሚገኙ አርሶ አደሮች መካከል አንዱ ይህን አረጋግጠዋል።

«መንግሥትም ትኩረት አድርጎ (አረሙን) እየለቀመው ነበር፣ አሁን ወደ ኋላ አለ፣ አሁን አረሙ እየጨመረ ነው፣ አሁንም ትኩረት ተሰጥቶ እርምጃ ካልተወሰደ አረሙ በጣም እየተስፋፋ ነው። አምና እንደቆመ እስካሁን አልተጀመረም፣ ሀሳብም የለም።» ብለዋል። ሌላ የአካባቢው አርሶ አደርም በተመሳሳይ ካለፈው ዓመት ክረምት መግቢያ ጀምሮ አረሙን የማስወገድ ሥራው መቋረጡንና ምክንቱንም በውል የነገራቸው አካል እንደሌለ አመልክተዋል።

አንድ ሰሞን ኅብረተሰቡን በማስተባበር የውኃ ላይ አረሙን ለማስወገድ ብዙ ሥራ ተከናውኖ ነበር። ፎቶ ከማኅደር፤ እንቦጭ አረምን ከጣና ሐይቅ ላይ የማስወገድ ዘመቻ ምስል፦ Alemneh Mekonnen/DW

የጣና ሐይቅና ሌሎች የውሀ አካላት ጥበቃና ልማት ተቋም የምሥራቅ ደንቢያ የአካባቢ ጥበቃና ተፋሰስ አያያዝ ቡድን መሪ አቶ መሰለ ተባባል ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፣ «ከኮቪድ በኋላም ሥራው ተቋርጦ ነበር፣ በህልውና ዘመቻው ወቅትም ተጓትቶ፣ ተቋርጦም ነበር፣ አሁን ደግሞ ከሐምሌ ጀምሮ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር አረሙን የማስወገድ ተግባሩን ማከናወን አልተቻለም፣ እንቦጭመታረም የነበረበት በዋናነት በጥቅምት ወር ነበር  አበባ የሚያብበው ውሀው ላይ እንደተንሳፈፈ በዚህ ወቅት ነው፣ በትንሽ ጉልበት ብዙ ማስወገድ የሚቻለውም በዚህ ጊዜ ነበር፣ በፀጥታ ችግሩ ምክንያት ግን አረሙን የማስወገድ ሥራ አልተከናወነም።» ነው ያሉት።

የወረዳና የቀበሌ አመራርም አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት ወርደው የማስተባበር ሥራ ማከናወን እንዳልቻሉ አቶ መሰለ አመልክተዋል። የአረሙ መጠን በተለያዩ መንገዶች ይለካ እንደነበር የሚናገሩት ቡድን መሪው፣ አሁን ግን ያን ማድረግ ባለመቻሉ የአረሙን ስፋት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ መለካት አለመቻሉን ተናግረዋል።

የጣና ሐይቅና ሌሎች የውሀ አካላት ጥበቃና ልማት ተቋም ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ፋሲል ድልነሳም ባለው የክልሉ የፀጥታ ችግር ምክንያት ተግባሩን ማከናወን እንዳልተቻለ ዛሬ ለዶይቼ ቬሌ ገልጠዋል። እምቦጭ አረም በውሀ ብዝሀ ሕይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ ሲሆን በሂደትም የውሀ አካላት እንዲጠፉ የሚያደርግ የውሀ ላይ ተንሳፋፊ አረም እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ። የእንቦጭ አረም በሐይቁ አዋሳኝ በሆኑ ሦስት ዞኖች፣ ዘጠኝ ወረዳዎችና በ35 ቀበሌዎች በ4,300 ሄክታር ላይ ተስፋፍቶ እንደነበር ዶቼ ቬለ መዘገቡ ይታወሳል።

ዓለምነው መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW