እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሳችሁ
ሐሙስ፣ ጳጉሜን 1 2010
ጷግሜ አንድ አልን ፤ አዲሱን 2011 ዓ.ም ልንቀበል አራት ቀናት ቀርተዉናል።በጠ/ሚ ዐብይ አሕመድ የሚመራዉ መንግሥት እለቱን የሰላም ቀን ሲል አዉጆአል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ኢትዮጵያ ላይ የሰላም ተስፋ ደምቆ ፈንጥቆአል። ይፈታሉ የተባሉ እስረኞች ባልታሰበ ሁኔታ መፈታታቸዉ፤ ዜጎች ከተሰደዱበት ሃገር ወደ ሃገራቸዉ ያለምንም ሃሳብ መግባታቸዉ፣ የኢትዮጵያ ቤተ-ክርስትያን አንድ መሆኑ፤ በሙስሊሙ ማኅበረሰብ መሪዎች ዘንድም ሰላም መዉረዱ፤ በሃገሪቱ አንፃራዊ ነጻነት እየታየ በመሆኑ በርካቶች ደስታቸዉን እየገለፁ ነዉ። እንዳያም ሆኖ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች አሁንም ግጭቶች መታየታቸዉ አልቀረም። በአዲስ ዓመት አዲስ ተስፋን የሰነቀዉ የሃገሪቱ ነዋሪ 2010 ን ሲሸኝ አዲሱ የኢትዮጵያ 2011 ዓመት እንደ አካባቢዉ እንደ ልማዱ እና እንደ ባህሉ በሰላም በደስታና በጤና በመተሳሰብ እና በፍቅር ለመኖር፤ በመመራረቅ ምኞት ደስታዉን፤ መገላለፅን ነዉ። የባህል መድረክ መሰናዶአችን ተሳታፊዎችን አነጋግረን የአዲስ ዓመት መልካም ምኞት መግለጫን አሰባስበናል፤ እንኳን አደረሳችሁ!
የአሮጌዉን ዓመት ስንሸኝ በባህል መድረክ መሳናዶ ተሳታፊ ከሆኑት አድማጮቻችን መካከል ጥቂቶቹን በስልክ አግኝተን የዘመን መለወጫ የመልካም ምኞታችሁን አካፍሉን ብለን አነጋግረናቸዉ ነበር። ከአንጋፋዉ የመድረክ እንቁ ከአርቲስት ደበበ እሸቱ እንጀምር። ደበበ እሸቱ ስለ መድረክ ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ ስንጠይቀዉ መንገድም ስራ ላይም ቢሆን ቆም ብሎ አስተያየቱን በደስታ ያካፍለናል። ዛሬም የአዲስ ዓመት ምኞቱን እንዲህ ነገረን።
« የኔ መልካም ምኞች በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ የተጀመረዉ የሰላም አካሄድ ዘላቂነት እንዲኖረዉ እና የኢትዮጵያ ሕዝብ የናፈቀዉን የዴሞክራሲ ሥርዓት ከወረቀት ባለፈ እንዲያገኘዉ፤ አካላቱ ፍትሕን በአግባቡ እንዲተረጉሙ ወጥተን በሰላም እንድንገባ የታመሙት ሠዎች ጤንነታቸዉ የተሟላ እንዲሆን፤ ተስፋ የቆረጡ ተስፋቸዉ እንዲለመልም ፤ እንዲያደርግልን፤ ቤተሰቤን እንዲጠብቅልኝ፤ እንዲሁም ሃገራችን ፤ የሚሰደዱባት ሳይሆኑ ሰላም የሰፈነባት ሃገር፤ የሚሰባሰቡባት ሃገር እንድትሆን ምኞቴ ነዉ። »
ጋሽ ደበበን በማመስገን፤ ወደ ጎንደር ደወልን። ወጣት መክት ካሳሁን ይባላል። ወጣት ካሳሁን በጎንደር ከሚገኙ ወጣቶች ጋር በተለያዩ በተለያዩ ኪነ-ጥበባዊ ሥራዎች ላይ ይሳተፋል። ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ ነዉ። የአዲስ ዓመት ምኞቴ አለ በመቀጠል፤
« በሃገራችን ባለፉት ሁለት ዓመታት የነበረዉን ሁኔታ ስናስብ የሁላችንም ምኞት ሰላም ዴሞክራሲና ፍትህ ነዉ። ወጣቶች ከሃገር ሲሰደዱና ሲገደሉ ያየንበት ዘመን ስለነበር፤ ይህ ጊዜ መልሶ እንዳይመጣ ብዙ ጥረት አድርገናል። አሁን ካለዉ የለዉጥ አንፃር የምንመኘዉ ሰላም አንድነት በሃገራችን ሰፍኖ የቀድሞዋን ኢትዮጵያን በሚቀጥለዉ 2011 ዓመት እንድናይ ነዉ።….»
የባህል መድረክ መሰናዶዋችን በኢትዮጵያ ጥንታዊ ታሪክ በተለይ ታሪካዊ ቅርስና መካነ ቅርሶች ላይ ሞያዊ አስተያየት እና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎች ሲኖሩን ለትብብር ወደ ኋላ የማይሉት አቶ ኃይለመለኮት አግዘዉ ናቸዉ። አቶ ሃይለመለኮትን ለአዲሱ ዓመት እጆ ከምን አልናቸዉ።
«በአዲሱ በ 2011 ዓመት የኢትዮጵያ አንድነቷ፤ ነጻነቷ ተከብሮ፤ ታፍራና ተከብራ የምትቀጥልበት፤ የዘር ፖለቲካ የሃይማኖት ክፍፍል የማይኖርበት እንዲሆን ታላቅ ምኞቴ ነዉ። እንዲሁም ደግሞ ኢትዮጵያዉያን ሃገራቸዉን በስደት ሳይሆን በመመለስ የሚገነቡበት የሚያንፁበት፤ የታመዉን የሚጠይቁበት የታሰረዉን የሚያስፈቱበት ሰላማዊ የፍቅር የአንድነት ሃገር እንድትሆን እመኛለሁ።
በጀርመን የኢትዮጵያዉያን የሙስሊም ማኅበራት ተጠሪ አቶ ብርሃን አባስ በተለይ የእስልምና በአላት ሲኖሩ ለተደጋጋሚ በባህል መድረክ ቀርበዋል። እስልምናን በጀርመን ዉስጥ ከ 1683 ዓ.ም ጀምሮ እስልምና ሃይማኖት መግባቱን፤ በጎርጎረሳዉያኑ 1732 የመጀመርያዉ መስጂድ በጀርመን በርሊን አጠገብ በሚገኘዉ የፖስትዳም ከተማ ዉስጥ መገንባቱን፤ ከዚያ ዘመን ጀምሮ ሙስሊሞች በጀርመን መኖራቸዉን የኢድ በዓልን አስመልክቶ በአዘጋጀነዉ መሰናዶ መናገራቸዉ ይታወሳል። በጀርመን በአሁኑ ጊዜ ከሦስት ሚሊዮን የሚበልጡ ሙስሊሞች ይገኛሉ። ለሕዝበ ሙስሊሙ ከ 2000 በላይ መስጂዶች እንደሚገኙም ተናግረዋል። አንጋፋዉ ጋዜጠኛ ንጉዜ አክሊሉም መልካም ምኞቱን በዚሁ መሰናዶ አስተላልፎአል።
ዛሬ ጷጉሜን አንድ አልናት፤ የዘመን አቆጣጠር መምህርና ጋዜጠኛ ሄኖክ ያሬድ ፈንታ እንደሚለዉ ቀደምት የኢትዮጵያ ሊቃውንት ጷጉሜን እንደ ዓመት ማጠቃለያ፣ እንደ ዘመን መፈጸሚያ አድርገው የሚያስቡበት ልዩ መንገድ አላቸው፡፡ እንዲሁም ‹‹ጷጉሜን የመጨረሻ አትምሰልህ የመጀመርያ እንጂ›› ይሉታል፡፡
በኢትዮጵያ ባሕረ ሐሳብ የወቅት አከፋፈል መሠረት በክረምት «ከሰኔ 26 እስከ መስከረም 25» ውስጥ ሰባት ንዑሳን ክፍሎች አሉ፡፡ ወደ አዲስ ዓመት መሸጋገሪያ ላይ ያሉት የመጨረሻዎቹ ስምንት ቀናት «ከነሐሴ 28 - ጷጉሜን 5» መጠርያቸው ‹‹ጎሕ፣ ነግህ፣ ጽባሕ፣ ብርሃን›› ነው፡፡ የአዲስ ዘመን ወጋገን፣ ጥዋት፣ ንጋት፣ ብርሃን ሊመጣ ነው የሚል ፍች አላቸው፡፡ የክረምቱ ጊዜ ለማለቅ መቃረቡንም ያሳያሉ። የአዲስ ዓመት ዋዜማዋ ‹‹ጷጉሜን 5›› በተለይ ‹‹ልደት›› የሚል መጠሪያ የተሰጣት በሚቀጥለው ዓመት ከሚከበረው የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ቀን ጋር ተመሳሳይ ስለሆነች ነው፡፡ ምንጊዜም ጷጉሜን 5 የሚውልበት ዕለት መጪውን ገና ያመለክታልና፤ ሲል የዘመን አቆጣጠር መምህርና ጋዜጠኛ ሄኖክ ያሬድ ፈንታ በፊስ ቡኩ ፅፎአል። መጭዉ 2011 ዓመት የጤና፤ የሰላም፤ የብርሃን ዘመን ይሁንልን!
ሙሉዉን ቅንብር የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ።
አዜብ ታደሰ
አርያም ተክሌ