1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዋጋ ንረት የተጫጫነው የአውደዓመት ገቢያ

ቅዳሜ፣ ጳጉሜን 4 2015

ወትሮም በአዲስ ዓመት መለወጫ በዓል መዳረሻ የሚደምቀው የአዲስ አመት ገቢያ ዘንድሮ ላይ ግን የመደብዘዝ ባህሪይ እንደተጫጫነው ሻጭና ሸማቾች ገልጻሉ፡፡ የጸጥታው መደፍረስ እና የዋጋ ንረቱ የሰውን የመግዛት አቅም እንዳዳከመም ገመታል፡፡

Äthiopien | Addis Ababa
ምስል Seyoum Getu/DW

የዓመት በዓል ገበያ

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያውያን አዲሱ 2016 ዓ.ም. አሮጌውን 2015 ዓ.ም. ስፍራ ሊያስለቅቅ አሁን የ48 ሰዓታት ገደማ እድሜ ብቻ ቀርተውታል፡፡
ወትሮም በአዲስ ዓመት መለወጫ በዓል መዳረሻ የሚደምቀው የአዲስ አመት ገቢያ ዘንድሮ ላይ ግን የመደብዘዝ ባህሪይ እንደተጫጫነው ሻጭና ሸማቾች ገልጻሉ፡፡
የጸጥታው መደፍረስ እና የዋጋ ንረቱ የሰውን የመግዛት አቅም እንዳዳከመም ገመታል፡፡
አቶ ሙሉቀን ተካ ሙሉቀን  የማር ውጤት እና ቅቤን በገፍ ይዘው አዲስ አበባ አራት ኪሎ በተዘጋጀው የአዲስ ዓመት መዳረሻ የንግድ ትርዒት ላይ ታድመዋል፡፡ በአቶ ሙሉቀን የመሸጫ መደብር አንድ ኪሎ ቅቤ ከ670 እስከ 680 ብር ዋጋ ተቆርጦለታል፡፡ ይህ ደግሞ ከባለፈው ተመሳሳይ የአውዳመት ገቢያ ጋር ሲነጻጸር የ30 ብር ጭማሪ መደረጉን ሻጩ ይናገራሉ፡፡ በበርካታ ኢትዮጵያውያን ዘንድ በበዓል ቀናት ከሚዘወተሩ ባህላዊ መጠጦች አንዱ የሆነው ጠጅ በዚህ መደብር አንዱ ሊትር 150 ብር ይሸጣል፡፡ አንድ ኪሎ ማር ደግሞ በ400 ብር ነው የሚሸጠው፡፡
እኚህ ነጋዴ እንደሚሉት ለዚህ በዓል የቀረቡ የተለያዩ ቁሳቁሶች ላይ የተወሰነ ጭማሪ ቢኖርም ተጋኗል የሚባል ግን አይደለም፡፡ “እኔ ጋ አሁን ቅቤም ላይ እስከ 30 ብር ጭማሪ ነው ያለው፡፡ ደንበኞቼንም እንዳላጣ የተጋነነ ጭማሪ ማድረግ አልወድም” ይላሉ፡፡
ለጠጅ ምርታቸው ማር በብዛት ከጎጃም እንደሚያመጡ የሚናገሩት ነጋዴው አቶ ሙሉቀን ቅቤ ደግሞ በገፍ ከዚሁ ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ ከሚገኙ እንደ ሸኖ ካሉ አከባቢዎች በማምጣት ለተጠቃሚው እንደሚያቀርቡም ይናገራሉ፡፡ ዘንድሮ በኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ጎልቶ የተስተዋለው ግጭት አለመረጋጋቱ በተለይም ዘንድሮ ደግሞ በአማራ ክልል ክፉኛ መስፋፋቱና በተለያዩ የአገሪቱም አከባቢዎች የህብረተሰቡን የተለመደ እንቅስቃሴ በመግታቱ የአዲስ ዓመት መለወጫ ድባብን ስለማቀዝቀዙ ይነገራል፡፡ አቶ ሙሉቀንም በገቢያቸው ይህንኑን በጉልህ ማስተዋላቸውን ያስረዳሉ፡፡ “የበዓል ድባብ እጅግ በጣም ቀዝቃዛ ነው፡፡ እንኳን የሚገዛን የሚጠይቀን እንኳ አጥተናል” ሲሉም የገቢያው መቀዛቀዝ ትዝብታቸውን አጋርተውናል፡፡
በከተማዋ ከሽንኩርት እስከ የተለያዩ የቤት ውስጥ ፍጆታ ቁሳቁሶችን በያዘው ሱቃቸው በንግድ ስራ የተሰማሩት ወ/ሮ ትዕግስት የተባሉ ነጋዴም የበዓሉ መዳረሻ ገቢያው እንደወትሮው ደማቅ እንዳልሆነላቸው ነው የሚገልጹት፡፡ ምናልባት በየአከባቢው የተከፈቱ ባዛሮች ለሸማቹ አማራጭ ሆነው ወደዚያ አምርተው እንደሆነም መላምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ “ስራው እኮ ሙቷል፡፡ የቤት ኪራይ ብቻ ነው የማይቀንስ እንጂ እንቅስቃሴው በእጅጉ ተዳክሟል” ሲሉም ደብዛዛ ያሉትን የበዓል መዳረሻ ገቢያውን ድባብ ገልጸውታል፡፡
በቅርቡ ዋጋቸው ከናሩ የቤት ውስጥ ፍጆታ ውስጥ እንደ ሽንኩርት እና ቲማትም ያሉ ምርቶች ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህን ምርቶች ይዞ በባዛር ገቢያ የተሰማራው ወጣት ነስረዲን ደግሞ የበዓል ገቢያው አንጻራዊ መረጋጋት ማሳየቱን ያወሳል፡፡ “ጥራት ያለውን ሽንኮርት እስከ 60 ብር ነው የምንሸጠው፡፡ ቲማትም ደግሞ እስከ 40 ብር እንሸጣለን፡፡” 
የበዓል ሸመታ አከናውነው ሲመለሱ ያገኘኋቸው ወ/ሮ ስንታየሁ ግርማ ደግሞ በተለያዩ ቦታዎች በስፋት የተከፈቱየበዓል ንግድ ትርዒቶችን ለአንጻራዊው የገቢያው መረጋጋት ያመሰግናሉ፡፡ “ሽንኩርት ከ55 እስከ 60 ብር አለ፡፡ አንድ ኪሎ ግራም ቃሪያ 60 ብር፣ ዝንጅብል 65 ብር፣ ቀይስር 30 ብር፣ ፎሶሊያ 60 ብር፣ አቮካዶ 30 ብር እና አንድ ኪሎ ጥቅል ጎመን 35 ብር ነው ያገኘሁት፡፡ ፈጣሪ ይመስገን እንቅስቃሴው መልካም ነው” ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡
ወ/ሮ አይናለም መኮንን ደግሞ ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ተመድበው በየባዛሩ እየተዟዟሩ የቁጥጥር ስራ ሲከውኑ አግኝቼ ነው ያነጋገርኳቸው፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ በከተማዋ በተለያዩ አከባቢዎች በተከፈቱ የንግድ ባዛርና ማዕከላት ምርትን በገፍ የማቅረብ ጥረት የበዓል ገቢያው ያለቅጥ እንዳያጋሽብ ረድቷል፡፡ “የወሰድነው ምርትን በብዛት የማቅረብ እና የገቢያ አማራጩን የማስፋት ስራ በጣም ውጤታማ ሆኗል፡፡ ከዚህ ቀደም እስከ 100 ብር ደርሶ የነበረው የሽንኩርትና ቲማትም ዋጋ በእጅጉ ቀንሰዋል፡፡ እንደ እንቁላልና ቅቤ ያሉ የአውደአመቱ ተፈላጊ ምርቶች ላይም መጠነኛ ቅናሽ ተደርጓል፡፡ 15 ብር ገብቶ የነበረው አንድ እንቁላል አሁን ገቢያ ላይ 10 ብር ይሸጣል፡፡ ቅቤም ኪሎው እስከ 600 ብር ይገኛል፡፡”
በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ በፍጥነት የጋሸበው የዋጋ ንረት የህብረተሰቡን የኑሮ ፈተና ማክበዱ ነው የሚነገረው፡፡ ጤፍ እንኳ መዲናዋ አዲስ አበባ ላይ አንዱ ኪሎ ከ100 እስከ 130 ብር እየተሸጠ መሆኑ የዋጋ ግሽበቱን ጣሪያ አጉልቶ የሚያሳይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የህብረተሰቡ የመግዛት አቅም ጋር ብርቱ ፈተና ስለመደቀኑ ይታመናል፡፡

ዋጋን ለማረጋጋት ያስችላል የተባለ የዓመት በዓል ልዩ ገበያምስል Seyoum Getu/DW
በዓመት በዓልዋዜማ የሸቀጦች ዋቃ አለቅጥ ንሯል።ምስል Seyoum Getu/DW

ስዩም ጌቱ 

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW