እንወያይ፤ ማኅበረሰቡን ያስጨነቀዉ የትግራይ ፖለቲከኞች ሽኩቻ
እሑድ፣ መጋቢት 14 2017
እንወያይ፤ ማኅበረሰቡን ያስጨነቀዉ የትግራይ ፖለቲከኞች ሽኩቻ
በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ /ህወሓት/ አመራሮች መካከል የተከሰተዉ ክፍፍል የአካባቢዉን ነዋሪዎች፤ ስጋት ላይ ጥሏል። ደም አፋሳሹ እና ለሁለት ዓመት የዘለቀዉ የትግራይ ጦርነት ፤ በፕሪቶርያዉ ግጭት የማስቆም ዉል ካበቃ በኋላ፤ በክልሉ ዘላቂ ሰላም ይሰፍናል የሚል ተስፋ አሳድሮ ነበር። ሆኖም በህወሓት አንጃዎች መካከል ለወራቶች መፍትሄ ሳያገኝ የቀጠለው ክፍፍል ዳግም ግጭት ያስነሳ ይሆን የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አልቀረም። ስጋቱ የክልሉ ነዋሪ ብቻ ሳይሆን የሃገሪቱ ህዝብ፣ ብሎም የዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ሆኗል። “መፈንቅለ-መንግሥት” ወይስ “ሕግ ማስከበር” የትግራይ ቅርቃር
የህወሓት አመራሮች ሽኩቻ፣ በህብረተሰቡ መካከል መከፋፈል እንዲፈጠር አድርጓል፤ የሚሉ የክልሉ ነዋሪዎች ጥቂቶች አይደሉም። ጦርነት ቢቀሰቀስ ሸቀጥ ወደ ትግራይ ላይገባ ይችላል በሚል ስጋት የሸቀጣ ሸቀጦች ዋጋ መጨመሩ፤ እጥረትም መከሰቱ እየታየ ነዉ። በክልሉ የነዳጅ እጥረት ከፍተኛ ችግር ከመሆኑም በላይ፤ ዋጋዉ በ 200% እጥፍ መጨመሩ ተመልክቷል። ከአካባቢዉ እንደሚሰማዉ የነዳጅ እጥረት ሳይሆን ነዳጅ ክልሉ ላይ የለም።በትግራይ የተፈጠረው ፖለቲካዊ ቀውስ
አንድ ግዜ ሞቅ ሌላ ጊዜ ደግሞ ጋብ እያለ፤ ለወራት በቀጠለዉ የህወሓት የውስጥ ክፍፍል፤ ዜጎች ለጉዳት መዳረጋቸው ተሰምቷል። የትግራይ ፖለቲከኞች በጠረቤዛ ዙርያ እንዲቀመጡ እና ችግራቸዉን እንዲፈቱ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት፤ የአፍሪቃ ህብረት፤ ብሎም ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ፤ ሊጫወቱዋቸዉ የሚችሏቸዉ ሚናዎች ምንድን ናቸዉ። የትግራይ ፖለቲከኞች ሽኩቻ እስከመቼ የዜጎችን ሰላም እየነሳ ይቀጥል ይሆን? የዛሬው እንወያይ የመነጋገሪያ ርዕስ ነው።
በዚህ ዉይይት ላይ ሃሳባቸዉን ያካፈሉት፤
1,አቶ አወት ልጅዓለም፤ ቀደም ሲል ትግራይ ፤ መቀሌ በሚገኘዉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያገለገሉ የህግ ባለሞያ ከመቀሌ፤
2,አቶ ጽጋቡ ቆብዓ--የትግራይ ዴሞክራስያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር - ከአዲስ አበባ
3,አቶ ደያሞ ዳሌ፤ የቀድሞ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና ቀደም ሲል በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ያገለገሉ የፖለቲካ ተንታኝ - ከሲዳማ፤ እንዲሁም
4,ሚሊዮን ኃይለሥላሴ፤ የዶቼ ቬለ ዘጋቢ - ከመቀሌ ናቸዉ።
አዜብ ታደሰ