እንወያይ፣ ሥር የሰደደዉ የኢትዮጵያዉያን ክፍፍል መፍትሔ አለዉ ይሆን?
እሑድ፣ መስከረም 25 2018
ለዛሬዉ ዉይይታችን ኢትዮጵያ ዉስጥ ሥር የሰደደዉ ልዩነትወይም ክፍፍል፣ ጠብና ግጭት ምክንያት፣ ደረጃዉ፣ ጉዳቱ ና መፍትሔዉ የሚል ጥቅል ርዕሥ ሰጥነዋል።የኢትዮጵያ ሕዝብን ፖለቲካዊ፣ ማሕበረዊና ምጣኔ ሐብታዊ ኃላቀርነት፣ ተባለጥና ጭቆናን ለማስወገድ ከ1960ቹ ጀምሮ የተፈራረቁት ሙሑራንና የፖለቲካ ልሒቃን ተለያዩ አማራጮችን ጠቁመዋል።ገቢር አድርገዋልም።
በ1960ዎቹ በዩኒቨርስቲ ተማሪዎችና ሙሕራን የተመራዉ ንቅናቄ በአብዛኛዉ ለኢትዮጵያ ችግሮች ሁነኛዉ መፍትሔ መሬትን ለገበሬዉ ማዉረስ፣ የብሔር ብሔረሰቦችን መብት ማክብርና ሶሻሊስታዊ ሥርዓትን መገንባት ነዉ የሚል ነበር።ዘዉዳዊዉ ሥርዓት ተወገደ፣ መሬቱም ለአራሹ ታደለ፣ ማርክሲዝም-ሌኒኒዝምም የሐገሪቱ ፖለቲካዊ ርዕዮተ-ዓለምነቱ ታወጀ።
ይሁንና አንድ ርዕዮተ ዓለም የሚከተሉት ወይም እንከተላለን የሚሉት ኃይላት እብዙ ቦታ ተከፋፍለዉ ይገዳደሉ፣ ሕዝቡንም ግራ-ያጋቡት ገቡ።ከኤርትራ እስከ ኦጋዴን ጠረፍ በተለያየ ሥም የተደራጁት ኃይላትና ምናልባትም ምዕራባዉያን መንግሥታት ደም አፋሳሹን ግጭትና ጦርነት ለማስቆም መፍትሔዉ የወታደራዊዉ ሥርዓት መወገድ እንደነበር ሲያቀነቅኑም ነበር።
1983 ወታደራዊ ሥርዓት ተወገደ።ኤርትራ ነፃ ወጣች።በ1960ዎቹ መልስ አላገኘም የተባለዉ የብሔር-ብሔረሰቦች ጥያቄ መልስ አገኘ ተባለ።በጎሳ ላይ የተመሠረተ ፈደራሊዝም መመሥረቱም ታዋጀ።ጦርነቱ ግን ቀጠለ።ክፍፍሉም ከብሔሮች ወይም ጎሳዎች አልፎ ወደ ንዑስ-ብሔሮች፣ ከዚያም እስከ ጎጥ ቀጥሎ ዛሬ ያንድ ብሔር ወይም ጎሳ አባላት የሆኑ የማሕበረሰብ ክፍሎች እየተቧደኑ ወይም በተናጥል ይጋጫሉ፣ ይገዳደላሉም።
አንዳዶች እንደሚሉት የዘመኑ ኢትዮጵያዊ ትዉልድ ከኳስ ግጥሚያ-እስከ ሠርግ ድግሥ፣ ከቁንጅና ዉድድር እስከ ሙዚቃ ትርዒት፣ ከባንክ ኢንቨስትመትን እስከ ትራንስፖርት አገልግሎት፣ በተሰደደበት ሐገር ልዩነት ሳይቀር በሁሉም ነገር በምንም ጉዳይ ይጣላል።ወይም ለመጣላትና ለመለያየት ዝግጁ ነዉ።ለምን?
ሶስት እንግዶች አሉን።
ወይዘሮ ደስታ ጥላሁን--------በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዉስጥ አመራር የነበሩ።
አቶ ዳያሞ ዳሊ-----------የግሎባል ፒንስ ባንክ አመራር
ዶክተር ዓለማየሁ ዋሴ---------የሥነ ምሕዳር ባለሙያና ደራሲ
ዶክተር ሙከረም ሚፍታሕ-----በሲቪል ሠርቪስ ዩኒቨርስቲ ረዳት ፕሮፌሰርና የፖሊስ ጉዳይ አጥኚ
አዘጋጅና አቅራቢ----ነጋሽ መሐመድ