ኢትዮጵያ ባሳለፍነው 2017 ዓ.ም ከወደብ እስከ ግድብ፦ እንወያይ
እሑድ፣ መስከረም 4 2018
አሮጌውን 2017 ዓመት ተሰናብተን አዲሱን ዓመት መቁጠር ከጀመርን እነሆ ሦስተኛ ቀናችን ። በ2017 ኢትዮጵያ ውስጥ በዋናነት ምን ተከሰተ? የዕለቱ እንወያይ መሰናዶ ባሳለፍነው ዓመት የተከሰቱ ዐበይት ጉዳዮችን የምንቃኝበት ነው ። ሙሉውን ውይይት በድምፅ እና በጽሑፍ በማገናኛው መከታተል ይቻላል ።
በ2017 ኢትዮጵያ ውስጥ በዋናነት ምን ተከሰተ? ግንባታው ከ14 ዓመታት በላይ የፈጀው ታላቁ የኅዳሴ ግድብ በዚሁ ሳምንት ውስጥ መጠናቀቁ ተበስሯል። በተደጋጋሚ ናይል «የመኖር ኅልውናዬ» የምትለው ግብጽ የግድቡን ምርቃት በመቃወም ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተቃዉሞ ደብዳቤ ማስገባቷ ተሰምቷል ።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያን ከአዲስ አበባ ሞቃዲሾ ያጓተተ ቀጣናዊ ውጥረት ባሳለፍነው ዓመት ቀጥሎ ነበር ። በተለይ ኢትዮጵያ ራስዋን «የሶማሊላንድ ሪብሊክ» ብላ ከምትጠራዉ ግዛት ጋር ወደብ ለመኮናተር ታኅሣሥ 2026 ላይ የመግባቢያ ሰነድ መፈረሟ ከተሰማ በኋላ እሰጥ አገባው ከቀጣናውም አልፎ ዓለም አቀፍ ገጽታ ተላብሶ ነበር ። ግብጽ አጋጣሚውን በመጠቀም የጦር መሣሪያዎችን በወታደራዊ አውሮፕላን ጭና ሞቃዲሾ ማስገባቷ ከተሰማ ጥቂት ቀናት በኋላም ነበር 2017 የጀመረው ።
ሕወሓት እና የፌዴራሉ መንግሥት መካሰሳቸው ሲካረር፤ በሰሜኑ ጦርነት ኅብረት ፈጥረው የነበሩት የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግሥታት ጊዜያዊ ፍቅርም እንደ ማለዳ ጤዛ ተንኖ ዐይን እና ናጫ የመሰሉበት ዓመት ። ከኢትዮጵያ የተለያዩ የመገናኛ አውታሮች እና ፖለቲከኞች ወደ ቀይ ባሕር መጠጋት አለብን፤ ዐሰብንም ማስመለስ አለብን የሚሉ ጥሪዎች ተስተጋብተዋል በዓመቱ ።
በአገር ውስጥ ግጭት እና መፈናቀል ቀጥሎ፤ ከአገር ውጪ ለመሰደድ በተገደዱት ላይ ደግሞ በባሕር ላይ አደጋ እልቂት እና በሰው አገር መከራ ጎልቶበት ተገባድዷል ። የንብረት ማስመለስ፤ የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት እና ሌሎች ዐበይት ረቂቅ ሕግጋትም ይፋ ሆነውበታል 2017 ። የብር የምንዛሪ መጠን መጨመር እና ዋጋው ማሽቆልቆል፤ የነዳጅ እጥረት እና የኑሮ ውድነት፤ የጋዜጠኞች እስርም ተስተጋብቷል ባለፈው ዓመት ።
ለአንዳንዶች የኤኮኖሚ ለውጥ ለሌሎች የፖሊሲ ማሻሻያ የተባለው ለውጥም ተድጓል በ2017 ። በ«ኮሪደር ልማት» የቤቶች ፈረሳ፤ የሐኪሞች «አገልግሎታችን የሚመጥን የደሞዝ ክፍያ ይሰጠን» ጥያቄ እና የተከተለው እስር፤ በኋላ ላይም ለመንግሥት ሠራተኞች ጭማሪ የደሞዝ ማሻሻያ ከአዲስ ዓመት ጀምሮ እንደሚደረግ መወሰኑ ተሰምቷል ። ከብዙው በጥቂቱ ለመጥቀስ ያህል ነው እንጂ ሁሉንም መዳሰስ ይከብዳል ።
በውይይቱ ሁሉንም ጉዳዮች እንዳስሳለን ማለት ባይሆንም፦ ባለፈው ዓመት የተከሰቱ ዐበይት ጉዳዮችን ነቅሰን በአዲሱ ዓመት ተስፋ እና ምኞት የገለጥንበት ነው የዛሬው ውይይት ።
በውይይቱ ሦስት እንግዶች ተሳታፊ ናቸው ።
-
ዶ/ር አብዱልመናን ሞሐመድ፤ የፋይናንስ ባለሞያ
-
አቶ በፍቃዱ ኃይሉ፦ ጦማሪ እና የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች
-
ጋዜጠኛ ሰለሞን ሙጬ፦ በአዲስ አበባ የዶይቸ ቬለ ዘጋቢ ናቸው ።
ሙሉውን ውይይት በድምፅ እና በጽሑፍ ከመገናኛው መከታተል ይቻላል ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ