እንወያይ፤ የትራምፕ ውሳኔዎች መዘዝ ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን
እሑድ፣ ጥር 25 2017
ለሁለተኛ ጊዜ በቅርቡ ዳግም የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ሆነው ቃለ መሃላ የፈፀሙት ዶናልድ ትራምፕ፤ በበዓለሲመት ንግግራቸው የኃይል አቅርቦት እና ስደትን የመሳሰሉ በርካታ ጉዳዮችን ለማስፈፀም ቃል ገብተዋል።
47ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ዋይት ሃውስ የተመለሱት ዶናልድ ትራምፕ በ‹‹አሜሪካ ትቅደም›› ፖሊሲያቸው ይታወቃሉ።ይህንን ተግባራዊ ለማድረግም ስልጣን በያዙ በጥቂት ቀናት በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ወንጀለኞች ያሏቸውን ያልተመዘገቡ ስደተኞችን በጅምላ እንደሚመልሱ በገቡት ቃል መሰረት ህጋዊ ፈቃድ የሌላቸው ስደተኞችን ማባረር ጀምረዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ትልቋ ለጋሽ ሀገር አሜሪካ ከዓለም የጤና ድርጅት እንድትወጣ እና የፓሪሱን የአየር ንብረት ስምምነት እንድትሰርዝ አድርገዋል።
የዩኤስ የውጭ ፖሊሲ ከአሜሪካ ትቅደም አጀንዳ ጋር መጣጣማቸውን ለማረጋገጥ እና .የውጭ እርዳታ መርሃ ግብሮችን ለመገምገም በሚልም የውጭ እርዳታ ለ90 ቀናት እንዲቆም ወስነዋል።ይህም በጎርጎሮሳዊው 2024 ዓ/ም ብቻ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ርዳታ ለገኘችው ኢትዮጵያ ትልቅ ፈተና መሆኑ ይነገራል።
በሌላ በኩል ዶናልድ ትራምፕ በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው ከአፍሪካ መንግስታት ጋር ለነበረው ግንኙነት ብዙም ፍላጎት አላሳዩም በሚል በውጪ ጉዳይ ፖሊሲያቸው ይተቻሉ። በሁለተኛ የስልጣን ዘመናቸው በዓለሲመት ላይ ባደረጉት ንግግርም ትራምፕ በአህጉሪቱ ላይ ያላቸው ትኩረት ስለመቀየሩ የሚጠቁም ፍንጭ አልታየም።
ከዚህ አንፃር ከመቶ ዓመት በላይ ከአሜሪካ ጋር የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ባላት አፍሪቃዊት ሀገር ኢትዮጵያ፤ትራምፕ በውጭ ግንኙነት ፣ በእርዳታ እና ብድር፣ በስደት እና በፀጥታ ጉዳዮች ላይ ምንአይነት ስልት ሊከተሉ ይችላሉ? የትራምፕ ውሳኔዎች በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያውያን ላይስ ምን ተፅዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ? በድህነት እና በሀገር ውስጥ ግጭት ለምትታመሰው ኢትዮጵያ የትራምፕ መምጣት ዕድል ወይስ ፈተና? የዚህ ሳምንት የእንወያይ ዝግጅት ማጠንጠኛ ነው።
በዚህ ውይይት ሶስት እንግዶች ተሳትፈዋል።
- ጋዜጠኛ አበበ ፈለቀ ከአሜሪካ ከዋሽንግተን ዲሲ
- አቶ ባይሳ ዋቅወያ ዓለም አቀፍ የህግ ባለሙያ ከኖርዌ
- ዶክተር አብዱልመናን መሀመድ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ከለንደን
ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው እንዲያደምጡ እንጋብዛለን።
ፀሐይ ጫኔ