የአፍሪቃ ሕብረት ግጭቶችን ለማስቆም ለምን ተሳነው?
እሑድ፣ የካቲት 15 2018
በጎርጎሪዮሳዊው 1963 ዓም የተመሠረተው የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ከአነሳሱ የክፍለ ዓለሙን አንድነት፤ ሰላምና ትብብርን የማስጠበቅ ሕልም ነበረው። በጎርጎሪዮሳዊው 2002 ደርባን ደቡብ አፍሪቃ ላይ ስያሜውን ወደ አፍሪቃ ሕብረት ሲለውጥ የአፍሪቃን ዘመን አመጣሽ ተግዳሮቶች በጋራ ለመቋቋም፤ ሰላም፤ ልማትና የክፍለ ዓለሙን ውህደት የሚያመቻች ጠንካራ መድረክ ለመፍጠር ታስቦ ነው። የሕብረቱ መሪዎች አፍሪቃ ውስጥ በየቦታው የሚሰማውን የጥይት ድምፅ ዝም እናስብላለን በሚል እቅድ ካወጡ ከ10 ዓመታት በላይ አልፈዋል። ግን በመላው ዓለም በመካሄድ ላይ ካሉ 56 ግጭት ጦርነቶች 50ዎቹ በአፍሪቃ ሃገራት ውስጥ መሆናቸውን የተመድ በቅርቡ ይፋ አድርጓል። ግጭቶቹ ከሚያስከተሉት ሰብአዊ እልቂትና ቁሳዊ ውድመት ባሻገር ሚሊዮኖችን ለረሀብ፤ ለመፈናቀልና ስደት በመዳረጋቸው 1,4 ቢሊየን ገደማ ሕዝብ የሚኖርባትና በተፈጥሮ ሀብት የበለጸገችው አፍሪቃ ዘወትር በምጽዋትና ድጎማ ስሟ ይነሳል። እስካሁን የተሳካ ሰላም ማስፈን ባለመቻሉ የሚተቸው የአፍሪቃ ግዙፍ ተቋም፤ ዘንድሮም እስከ ጎርጎሪዮሳዊው 2030 ግጭት አስቆማለሁ የሚለውን እቅዱን ደግሞ መግለጹ፤ ዓለም በጎራ ተቧዶኖ በሚወዛገብበት በዚህ ወቅት እንዴት ይሳካለታል በሚል አነጋጋሪ ሆኗል።
መቀመጫ በሆነችው ኢትዮጵያ እና በአፍሪቃው ቀንድ ጦርነት ባንዣበበት ወቅት ጉባኤውን ያካሄደው የአፍሪቃ ሕብረት ግጭቶችን ለማስቆም በእርግጥ አቅምም ሆነ ፍላጎቱ አለው? ሰላም ለማስፈን የተሳነው በመዋቅራዊ ችግር ወይንስ በፖለቲካ ፈቃደኝነት ጉድለት? ስንል ለውይይት ሦስት እንግዶችን ጋብዘናል። ተወያዮች አቶ ብርሃነ መሥቀል ነጋ የቀድሞ የኢትዮጵያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ በዲፕሎማትነት ያገለገሉ፤ በተመድ ቋሚ ጽሕፈት ቤት ኒው ዮርክ የፖለቲካ እና የሕግ ጉዳዮች ኃላፊ በመሆን የሠሩ ቆየት ብለው ደግሞ በመንግሥታቱ ድርጅት ውስጥ በሰላም ማስከበር እና በሰብዓዊ ጊዳዮች በተለያዩ የድርጅቱ ሥራዎች ከ20 ዓመታት በላይ የሠሩ፤ ዶክተር ተመስገን ቶማስ የሰላም እና ደኅንነት ተባባሪ ፕሮፌሰር፤ የተለያዩ ጽሑፎችን ለኅትመት ያበቁ አሁንም በዩኒቨርሲቲ በመምህርነት በማገልገል ላይ የሚገኙ እና በአዲስ አበባ በተለይ የአፍሪቃ ሕብረት ጉዳዮች ጋር በተገናኙ ዜናዎች የዶቼ ቬለ ዘጋቢ እስክንድር ፍሬው ናቸው።
ሙሉውን ውይይት ለማድመጥ ማዕቀፉን ይጫኑ
ሸዋዬ ለገሠ