እንወያይ፣ የኢትዮጵያ ፈርጀ-ብዙ ቀዉስ፣ ምክንያቱና መፍትሔዉ
እሑድ፣ የካቲት 2 2017
ለዛሬዉ ዉይይታችን የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ቀዉስ፣ ምክንያቱና መፍትሔዉ የሚል ጥቅል ርዕስ ሠጥተነዋል።ኢትዮጵያ ካንዱ ግጭት-ፖለቲካዊ ቀዉስ ወደ ሌላዉ እየተላተመች፣ ዓመት በዓመት መተካቷን ቀጥላለች።ሐገሪቱን ለረጅም ጊዜ የገዛዉ ህወሐት-ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት በ2010 በሕዝባዊ አመፅ ከሥልጣን መወገዱ ለሐገሪቱ ህዝብ የዴሞክራሲ ጭላንጭል፣ የልማት ዕድገት ተስፋ የፈነጠቀ መስሎ ነበር።ግን ብዙ አልቆየም።
ከሶማሌ-ኦሮሚያ ክልሎች ድንበር እስከ ጌዲኦ፣ ከሲዳማ-ወላይታ ዞኖች እስከ ቡራዩ የሺዎችን ሕይወት ያጠፋዉ፣ ሚሊዮኖችን ያፈናቀለዉ ጎሳ-ለበስ የፖለቲካ ግጭት የሽግግር ወቅት ፈተና መሆን-አለመሆኑ አስገምግሞ ሳያበቃ ትግራይ ላይ የተለኮሰዉ አደገኛ ጦርነት ራሱ ትግራይን፣ ከፊል አማራንና አፋር ክልሎችን አንድዷል።ኤርትራን የሞጀረዉ ጦርነት በሁለት ዓመታት ዉስጥ በብዙዎች ግምት በትንሹ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ፈጅቷል።ሚሊዮኖችን አፈናቅሏል።ሴቶች ተደፍረዋል።ሕፃናት፣አቅመ ደካሞች ለረሐብ ተጋልጠዋል።
ዘግናኙ ጦርነት በሰላም ስምምነት ከቆመ ሁለት ዓመት አለፈዉ።ይሁንና የጠመንጃዉ ላንቃ ቢዘጋም የትግራይ ፖለቲከኞች እርስበርስና ከኢትዮጵያ ፌደራዊ መንግሥት ጋር የገጠሙት ሽኩቻ፣ መጠላለፍና መጎነታተል አሁንም እንደቀጠለ ነዉ።
የአማራና የኦሮሚያ ክልሎችን የሚያብጠዉ የመንግሥትና የአማፂያን ግጭቶች፣ በየአካባቢዉ የተንሠራፋዉ ሥርዓተ አልበኝነት፣ እገታ፣ ዘረፋ፣ መፈናቃል፣ የኑሮ ዉድነት ብዙዎች እንደሚሉት ሕዝቡን ለመከራ፣ ሐገሪቱን ደግሞ ለሕልዉና አደጋ ዳርጓቸዋል።የኢትዮጵያ ፈርጀ ብዙ ምስቅልቅሎችን እየጠቃቀስን ምክንያትና መፍትሔዉን ላይ ባጭሩ እንወያያለን።ሶስት እንግዶች አሉን።
- አቶ ባይሳ ዋቅወያ----የሕግ ባለሙያና የቀድሞ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለሙያ
- አቶ ያሬድ ጥበቡ---የቀድሞ የኢሕአፓ ታጋይ፣ የኢሕድን መስራችና የፖለቲካ ተንታኝ።
- ዶክተር አደም ካሴ----የሕገ-መንግሥታዊ ዴሞክራሲ እና የአስተዳደር ጉዳዮች አማካሪ ናቸዉ
ነጋሽ መሐመድ