1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እንደገና ያገረሸው የሶማሌ እና የአፋር ግጭት

ሰኞ፣ ጥቅምት 10 2012

ባለፈው ሳምንት በጅግጅጋ እና በሰመራ በተካሔዱ የተቃውሞ ሰልፎች የአፋር እና የሶማሌ ክልሎችን የሚወቅሱ መፈክሮች ተደምጠዋል። በአፋምቦ 16 ሰዎች የተገደሉበት ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ ሁለቱ ክልሎች በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች ግጭት አገርሽቷል። እስካሁን የአፋምቦው ጥቃት በማን እንደተፈጸመ የሚታወቅ ነገር የለም።

Karte Äthiopien Ethnien EN

እንደገና ያገረሸው የሶማሌ እና የአፋር ግጭት

This browser does not support the audio element.

በአፋምቦ ጥቃት ከተፈጸመ አስር ቀናት ቢያልፉም ዛሬም ኃላፊነት የወሰደ ወገን የለም። የኢትዮጵያ መንግሥት ጉዳዩን አጣርቶ መረጃ አልሰጠም። ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሶማሌ እና የአፋር ክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮችን አግኝተው ቢያነጋግሩም ስለ ጥቃቱ መንስኤ የተባለ ነገር የለም።

ከኢትዮጵያ እና ከጅቡቲ ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው የአፋምቦ ወረዳ ቅዳሜ ጥቅምት 1 ቀን 2012 ዓ.ም. በተፈጸመው ጥቃት የቆሰሉ ሰዎች በአፋር ክልል በሚገኙ ሶስት ሆስፒታሎች በሕክምና ላይ ናቸው። የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ያሲን ሐቢብ በጥቃቱ አስራ ስድስት መገደላቸውን ተናግረዋል። በጥቃቱ ከቆሰሉ መካከል አንዲት እንስት ወደ ሕክምና ማዕከል ከደረሱ በኋላ ሕይወታቸው አልፏል። 

የአፋር ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ያሲን ሐቢብ ለዶይቼ ቬለ (DW) እንደተናገሩት በኦብኖ ቀበሌ በተፈጸመው ጥቃት ከቆሰሉት መካከል አራት ሕፃናት፣ አምስት ሴቶች እና ማየት የተሳናቸው የዕድሜ ባለጸጋ ጭምር ይገኙበታል። «የጥይት ስለሆነ ቁስላቸው የከፋ ነው። ግማሹ ሰውነታቸው ላይ ያለው የፈንጂ ፍንጣሪ ነው። ወደ አራት አካባቢ ቁስለኞች ለተጨማሪ ሕክምና ተልከዋል። ሌሎቹ እዚሁ ሕክምና ላይ ነው ያሉት። መንገዱ በጣም ረዥም ስለነበረ ከዛ ሆስፒታል እስኪመጡ ድረስ ብዙ ደም ነው የፈሰሳቸው። ከቆሰሉት መካከል ሁለት አይን የሌላቸው የ60 አመት የዕድሜ ባለጸጋ ሁሉ ይገኙበታል። ከአራቱ እና ሆስፒታል ውስጥ ከሞተችው ውጪ ያሉት እዚሁ ሕክምና ላይ ነው የሚገኙት።»

ምክትል ኃላፊው እንደሚሉት በጥቃቱ ሕይወታቸው ያለፈውም ይሁን ቆስለው አሁን በሕክምና ላይ የሚገኙት የአፋምቦ ነዋሪዎች ጭንቅላታቸውን፣ ደረታቸውን እና ከደረታቸው በታች በጥይት የተመቱ ናቸው። «ከአፋር በኩል ለጦርነት ወይም ደግሞ ለውጊያ የተዘጋጁ አይነት ሰዎች አይደሉም። በጣም ትልልቅ ሰዎች፣ ሴቶች እና ሕፃናት አሉበት። እነዚህ ለውጊያ የሚዘጋጁ ሰዎች አይደሉም» ሲሉ አቶ ሐቢብ ያክላሉ። 

ምስል picture-alliance/dpa

የአፋምቦው ጥቃት በማን እንደተፈጸመ እስካሁን በገለልተኛ ወገን የቀረበ መረጃ የለም። ጥቃቱን ለማውገዝ ባለፈው ሳምንት አደባባይ የወጡ በተለያዩ የአፋር ክልሎች የሚኖሩ ዜጎች ግን ድርጊቱን የፈጸሙ የሏቸውን አንድ፣ ሁለት ብለው ዘርዝረው አውግዘዋል። ሰልፈኞቹ ለጥቃቱ ተጠያቂ የሚያደርጉት የኢሳ ጎሳን፣ የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት የልዩ ኃይል አባላት እና የጅቡቲ መንግሥትን ነው። 

ባለፈው ሳምንት ሐሙስ በተካሔደው ሰልፍ «የአፋር ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ ድምጹን አሰምቷል» የሚሉት አቶ አልዛርቃዊ ሐቢብ የተባሉ የሰመራ ነዋሪ በጥቃቱ «የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አባላት፣ የሶማሌላንድ እና የአልሸባብ እጅ አለበት» ሲሉ ይከሳሉ። «የአፋር ሕዝብ የተነሳበት የሶማሌላንድ፣ የአል-ሸባብ እና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አንዳንድ አባላቶች በጥምረት የአፋርን መሬት በግድ ለመውሰድ ብዙ ሕፃናት እና ሴቶች እና ልጆች የጨፈጨፉበት ሁኔታ ነበር» ሲሉ ይናገራሉ። አቶ አልዛርቃዊ «የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስቴር በግልፅ የአፋር [ክልል] በቪዲዮ ያረጋገጠውን መረጃ ውሸት ነው በማለት የዛ ሁሉ ሴቶች እና አዛውንት ደም ዋጋ እንደሌለው አድርገው በማቅረባቸው የአፋር ሕዝብ የመከላከያውን መግለጫ በመቃወም» ሰልፍ ወጥቷል ብለዋል። 

በአፋምቦው ጥቃት የጅቡቲ መንግሥት ጭምር በአፋር ነዋሪዎች በተባባሪነት ቢወነጀልም ይህንን ክስ ግን የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስቴር አስተባብሏል። ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለ24 ሰዓታት ጉብኝት ወደ ጅቡቲ ተጉዘው ከአገሪቱ ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጉሌህ ባደረጉት ውይይት ይኸን የአፋር ነዋሪዎች ክስ የተመለከተ ጉዳይ አንስተው እንደሁ የታወቀ ነገር የለም። 

በመከላከያ ሚኒስቴር የምክትል ኤታማዦር ሹም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኮሎኔል ተስፋዬ አያሌው «የጅቡቲ ጦር የኢትዮጵያን ድንብር ተሻግሮ በአፋር በኩል ዜጎች ላይ ጉዳት አደረሰ የሚለው ወሬ ሐሰት ነው» ሲሉ ባለፈው ሰኞ ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል። የሰመራ ከተማ ነዋሪዎች ግን የመከላከያ ሚኒስቴርን ምላሽ አልተቀበሉም። በሰመራው ሰልፍ የተሳተፉት አቶ አማር ሐቢብ እንደሚሉት የአፋር ክልል ጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ በጉዳዩ ላይ የሰጡት እና ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሐሳብ የሚቃረነው መግለጫ ለሰልፉ ሌላ ገፊ ምክንያት ነበር።

«የክልሉ ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ የተለያዩ መረጃዎችን ይፋ አድርገው ነበር። መከላከያ አሰሳ አድርጊያለሁ፤ እዚህ አካባቢ ምንም አይነት የውጭ ኃይል የለም ብሎ ነበር። የክልሉ መንግሥት ደግሞ የዚያን ማስተባበያ ሰጥቶ ነበር። ያ ምላሽ ታርጋን ጨምሮ የተለያዩ ቁሳቁሶችን በአፋር ሚዲያ ይፋ አድርጎልናል። እኛ ደግሞ የክልላችንን ድምፅ በመደገፍ ነው የወጣነው» ይላሉ አማር። 

በብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ በየቀኑ በአፋርኛ ቋንቋ በሚሰራጨው ክፍለ ጊዜ በተላለፈው ዘገባ የክልሉ ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ የጥቃት ፈፃሚዎቹን ማንነት ያረጋግጣሉ ያሏቸውን ሁለት አይነት ሰንደቅ ዓላማዎች፣ የፊት መሸፈኛ ጭንብል እና መታወቂያ ወረቀቶች አሳይተዋል። በመታወቂያ ወረቀቶቹ ላይ «የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት የጸጥታ አስተዳደር እና ፍትህ ቢሮ የልዩ ፖሊስ አባላት መታወቂያ ካርድ» የሚል ፅሁፍ ይነበባል።  
የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሙስጠፌ መሐመድ የኮምዩንኬሽን ጉዳዮች አማካሪ አቶ መሐመድ ኦላድ ግን ከወደ ሰመራ የሚሰማውን ወቀሳ በሙሉ «ሐሰት»  ሲሉ አጣጥለዋል። 

ምስል DW/J. Jeffrey

አቶ መሐመድ  «እንዲህ አይነት ወሬ እና ዘገባ ሐሰት ነው። የማንኛውንም የጸጥታ አስከባሪ ኃይል መታወቂያዎች ተገኝተው፣ ፎቶዎች ተቀርጸው ማሰራጨት በጣም ቀላል ነው። ሕዝቡን ለማተራመስ የታሰበ ነገር ነው። የሶማሌ ልዩ ኃይል እዚያው ድንበር አካባቢ ጸጥታውን አስከብሮ የሁለቱን ሕዝቦች አብሮ የመኖር እና ለዘመናት የቆየ የባህል እና ማኅበራዊ ትስስሩን ለማስቀጠል የሚሰራ ኃይል ነው እንጂ ወደ ሌላ ክልል ድንበር ተሻግሮ እንደዚህ አይነት የጸረ-ሰላም ድርጊቶች የሚያደርግ ኃይል አይደለም» ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። 

በአፋር የተፈጸመው ጥቃት በመገናኛ ብዙኃን የተዘገበበት መንገድ፤ ከጥቃቱ በኋላ የቀረበው ውንጀላ እና በሶማሌ ክልል የአፋር ታጣቂዎች ይፈፅሙታል የተባለ ግድያ በጅግጅጋ እና በሌሎች የክልሉ ከተሞች ሌላ ሰልፍ ቀስቅሷል። በሶማሌ ክልል፣ ሲቲ ዞን፣ አይሻ ወረዳ የሚኖሩት ሮብሌ መሐመድ የአፋር ክልል ታጣቂዎች በክልሉ አርብቶ አደሮች ላይ ይፈፅሙታል ያሉትን ጥቃት ለማውገዝ ባለፈው አርብ በአይሻ ከተማ ሰልፍ ከወጡ አንዱ ናቸው።

ሮብሌ መሐመድ «የሰልፉ ዋና ዓላማ ንጹሀን የሶማሌ አርብቶ አደሮች፣ በአፋር ክልል ባሉ የታጠቁ ኃይሎች ሁሌ እየተገደሉ ነው። ይባስ ብሎ በተለያዩ የኢትዮጵያ ሚዲያዎች የሶማሌን ስም አሸባሪ እያሉ፤ አሸባሪ ከአገራችን ይውጣ፤ አሸባሪ ወረረን እያሉ ከፍተኛ ፕሮፓጋንዳ እያቀረቡ የሚነዛውን ነገር ለመቃወም ነው። በጣም በርካታ ሰው ወጥቷል፤ በሰላም ተጀምሮ በሰላም ተጠናቅቋል» ብለዋል።

የአፍደም ወረዳ የወጣቶች እና ስፖርት ፅህፈት ቤት ኃላፊ  አቶ ማሕሙድ አደንጌ ዲ የአፋር ክልልን በተስፋፊነት ይከሳሉ። «እኔ ያለሁበት የአፍደም ወረዳ እንኳ የተሳሳተ የእኛ ነች የሚል የረዥም ጊዜ አመለካከት አላቸው» የሚሉት አቶ ማሕሙድ «በአፍደም ከጠዋት 12 ሰዓት ጀምሮ ህዝቡ ወጥቶ፤ መፈክሩን፣ የኢትዮጵያን እና የክልሉን ባንዲራ ይዞ ሴት፣ ሕፃን፣ ልጅ ሳይሉ ወጥተው ሲቃወሙ ነበር። በዚያ አካባቢ የሚፈሰው የሶማሌ ደም ይቁም፤ ህገ መንግስታዊ መብታችን ይከበር፤ ሰላማችንን እናግኝ ሰሚ እናግኝ የሚሉ መፈክሮች ነበሩ። የሚሞቱት እና የሚሰደዱት ሕፃናት እና እናቶች ይቁም የሚል ነው በዋናነት ሲስተጋባ የነበረው» ሲሉ አስረድተዋል። 

ምስል picture-alliance/AP Photo/E. Meseret

አፋር እና ሶማሌ ለረዥም አመታት የተፈጥሮ ሐብቶችን ለመቆጣጠር በሚደረግ ፉክክር፣ በግዛት ይገባኛል ውዝግብ፣ እና መደበኛ ባልሆነውን የንግድ ልውውጥ የበላይነት ለማግኘት በሚደረግ ፍትጊያ በተደጋጋሚ ሲጋጩ የኖሩ መሆናቸውን በጉዳዩ ላይ የተሰሩ ጥናቶች ይጠቁማሉ። የሁለቱ ክልሎች ወሰን በቅጡ ያልተለየ አብዛኛውን ጊዜው ውጥረት የማይጠፋበት ነው። በግለሰቦች መካከል የሚቀሰቀስ አነስተኛ ጠብ በአፋር እና በሶማሌ ብሔሮች መካከል የከፋ ኹከት መንስዔ ሲሆን መታዘባቸውን በአካባቢው ለረዥም ዘመናት የኖሩ ይናገራሉ። 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላም እና ጸጥታ ጥናት ማዕከል ዳይሬተር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) እንደሚሉት በአፋር እና በሶማሌ መካከል ለረዥም አመታት የዘለቀው ግጭት የተፈጥሮ ሐብት አጠቃቀም ላይ መሰረት ያደረገ ይሁን እንጂ ታሪክ፤ የወሰን አከላለል እና ፖለቲካ የራሳቸው ድርሻ አላቸው።

የግጭቶቹ መንስኤዎች «በዋናነት የተፈጥሮ ሐብት እና ፖለቲካ ናቸው። የዛሬ አስር አመት ወደ ቦታው ሔደን ታሪካዊ የሆኑ ያልተመለሱ ጥያቄዎች እንዳሉ አይተናል። የግዛት ይገባኛል ወይም ደግሞ የድንበሮች አካባቢ ችግርም አለ። ታሪካዊም የሆነ ከፖለቲካው የመገፋት እና በኤኮኖሚው ተሳትፎ ያለማድረግ ችግር አለ» የሚሉት ዶ/ር ዮናስ አዳሌ ጉዳዩ ውስብስብ መሆኑን አስረድተዋል። 

የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የሶማሌ እና አፋር ክልሎች በተለያዩ ወቅቶች እያደር የሚያገረሸውን ግጭት በዘለቄታው ለመፍታት ይበጃሉ ያሏቸውን ውይይቶች እና ስምምነቶች ቢያካሒዱም ጉዳዩ ይበልጥ እየተወሳሰበ መጥቷል። የአፋር እና የሶማሌ ክልሎች በታኅሳስ 2007 ዓ.ም. በደረሱበት ስምምነት መሰረት በተደጋጋሚ የግጭት መንስኤ የነበሩትን ገዳማይቱ፣ እንዱፎ እና አዳይቱ የተባሉት ቀበሌዎች በአፋር ክልል ስር እንዲካተቱ በፊርማ ጭምር ተረካክበው ነበር። ከውሳኔውም በኋላ ቦታው ግን ግጭት እና ግድያ አልራቀውም።

ከስድስት ወራት ገደማ በፊት በአካባቢው የአፋር ክልል ታጣቂዎች ፈፅመውታል በተባለ ጥቃት አስራ አንድ ሰዎች  ከተገደሉ በኋላ የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ከስምምነቱ ራሱን አግልሏል። በወቅቱ «ሶስቱ አዋሳኝ ቀበሌዎች በአፋር ክልል እንዲካተቱ መደረጉ ሕገ-መንግሥታዊ አይደለም» ያለው የሶማሌ ክልል «በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች መብት አልተጠበቀም» የሚል ቅሬታ ጭምር ነበረው። በአካባቢዎቹ በተከሰቱ ተደጋጋሚ ግጭቶች የበርካታ ሰዎች ሕይወት አልፏል። የጸጥታ ጥናት ባለሙያው ዶ/ር ዮናስ ይኸ በአፋር እና በሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች የሚቀሰቀስ ግጭት ዳፋው ድንበር ተሻግሮ ለጅቡቲ እና ለሶማሊያ የሚተርፍ ሊሆን እንደሚችል ያስጠነቅቃሉ። ባለሙያው እንደሚሉት ጉዳዩ ፖለቲካዊ እና ማኅበረሰባዊ መፍትሔ ይሻል።  «አንድም የለውጡን ኃይል ሊያደናቅፍ ይችላል። የገንዘብ ዝውውር ይኖራል። የመሳሪያ ዝውውር እስከ አዲስ አበባ ድረስ ሊደርስ ይችላል። ያ ራሱን የቻለ የጸጥታ ሥጋት ይፈጥራል። በሶማሌ እና በአፋር ክልል የሚፈጠር ግጭት በኢትዮጵያ ልማት እና ዕድገት ላይ፤ በሰላም እና በደህንነት ላይ ከፍተኛ ችግር ሊያስከትል ይችላል» ሲሉ ያስጠነቅቃሉ። 

ምስል picture-alliance/dpa

ከዘገየ ሌላ መልክ ሊይዝ ይችላል የሚል ሥጋት ያላቸው የጸጥታ የጥናት ባለሙያው  «የጅቡቲ፣ የሶማሊያ እና የኢትዮጵያ አገሮች ቶሎ ብለው ተነጋግረው መፍትሔ መስጠት አለባቸው። መፍትሔው አንደኛ - ከፍ ብሎ ባለው ፖለቲካ፤ ሁለተኛ በማኅበረሰብ ደረጃ ተነጋግረው ችግሩን በአፍሪካዊ መንገድ መፍትሔ መፍጠር አለባቸው። አለዚያ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ቀንድ ራሱ ሌላ ችግር ሊያስከትል ስለሚችል አጣዳፊ መፍትሔ ያስፈልጋል ብዬ አስባለሁ» ብለዋል። 

ባለፈው ሳምንት የአፋር ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አወል አርባ እና የሶማሌ ክልል አቻቸው አቶ ሙስጠፋ መሐመድ በጉዳዩ ላይ ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የመከላከያ ሰራዊት መኮንኖች ባለበት ውይይት አድርገዋል። ከውይይቱ በኋላ የበርካቶችን ሕይወት እየቀጠፈ ያለው ግጭት «በዚሁ መቀጠል» የለበትም ያሉት የአፋር ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አወል አርባ ከፌደራል መንግሥት እና ከሶማሌ ክልል ጋር በመሆን መፍትሔ እንሻለን ብለዋል። 

የሶማሌ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ሙስጠፋ መሀመድ በበኩላቸው «ጸጥታውን በተመለከ የፌድራል አካላት ከእኛ ጋር የሚሰሩት ሥራ አለ። ያንን ሁለቱም ክልል ተባብረው እንዲሰሩ መመሪያ ተቀምጧል። ያንን መመሪያ መፈጸም ነው። ያንን አካባቢ ከግጭት ነጻ የማድረግ ሥራ መሰራት አለበት። ሁለተኛ የሕዝብ ጥያቄ እና የመሬት ይገባኛል ጉዳዮች በሕግ አግባብ እና በሕገ-መንግሥቱ መሰረት እንዲፈቱ» ውሳኔዎች ተላልፈዋል ሲሉ ተናግረዋል። 

የሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ «በሶማሌና በአፋር ክልሎች አዋሳኝ አከባቢዎች አገራዊውን ለውጥ ለማዳናቀፍ ሌት ተቀን በሚጥሩ አካላት ህቡዕ እንቅስቃሴ የተፈጠረውን ችግር በህገ-መንግስቱ መሰረት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቁርጠኛ መሆኑን» ገልጿል።

እሸቴ በቀለ
ተስፋለም ወልደየስ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW