1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርትኢትዮጵያ

«እንደ ትምህርት ቤት በጣም ነው የተሰማን»

ዓርብ፣ ጥቅምት 9 2016

ኢትዮጵያ ውስጥ በ2015 የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተናን ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል 50 በመቶ እና ከዛ በላይ ያመጡት ተማሪዎች 3,2 በመቶ ያህሉ ብቻ እንደሆኑ ትምህርት ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል። በዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት በዚሁ ጉዳይ ላይ ተማሪዎችን፣ መምህራንን እና የትምህርት ምዘና እና ፈተና አገልግሎትን ጠይቀናል።

ተማሪዎች እና መምህር
በትግራይ ክልል ከሦስት ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ሀገራዊ የ12ኛ ክፍል ፈተና ዘንድሮ ተሰጥቷልምስል Million Haileselasie/DW

የ12ኛ ክፍል ውጤት እና የትምህርት ምዘና እና ፈተና አገልግሎት ምላሽ

This browser does not support the audio element.

ወጣት ፌኔት እና ሊድያ የዘንድሮውን የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ካለፉ ወይም ከ 50 በመቶ በላይ ውጤት ካስመዘገቡ 27 ሺ 267 ተማሪዎች መካከል ናቸው። ሊዲያ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ስትሆን ፌኔት ደግሞ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ትምህርቷን የተከታተለችው ጅማ ከተማ ነው። 378 ነጥብ አምጥታ በማለፏ ደስተኛ ብትሆንም ከዚህ የተሻለ ውጤት ፌኔት ጠብቃ ነበር። « ከዚህ በፊት 400 ቤት ማምጣት በጣም ቀላል ነበር። ስለዚህ 500 ቤት ለማምጣት ነበር አቅደን ስናጠና የነበረው።» ትላለች። ፌኔት የጠበቀችውን ውጤት ላለማምጣቷ ሌላም ምክንያት አለ። « 12ኛ ክፍል እያለሁ ወደ ጀርመን መሄድ ነበረብኝ።  ቪዛ ለአጭር ጊዜ ነው የሚሰጠው እና ያንን ለማስተካከል እዚህ መጥቼ ሶስት ወር ቆይቻለሁ። 9ኛ ክፍል ከአራት ወር ውጪ ምንም አልተማርንም ፣10ኛ ክፍል አንድ ቀን ክፍት አንድ ቀን ዝግ ነበር። እና ብዙው ትምህርት የሸፈነው 12ኛ ክፍል ነው። እና ጀርመን በነበርኩበት ጊዜ ብዙ ነገር አምልጦኛል።» እንደዛም ሆኖ ፌኔት ፈተናውን ለማለፍ ችላለች። ከፈተናዋ በኋላ በስራ ምክንያት ጀርመን ከሚገኙ ቤተሰቦቿ ጋር ዳግም የተቀላቀለችው ወጣት በአሁኑ ሰዓት ጀርመን ሀገር ዮንቨርስቲ ገብታ የምትማርበትን መንገድ እያጣራች ትገኛለች። በቅድሚያ ቋንቋ መማር ግን ግድ ብሏታል።


ሌላዋ የዘንድሮውን የ12ኛ ክፍል ፈተና ያለፈችው እና የ 18 ዓመት ወጣት የሆነችው ሊዲያ « እንደማልፍ ርግጠኛ ነበርኩ» ትላለች ። ራሷን መካከለኛ ተማሪ ነኝ » ስትል ነው የምትገልፀው። የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዋ  ከከፍተኛው 600 ነጥብ 326 በማምጣት ማለፍ ችላለች። ውጤቷ እሷም የጠበቀችው አልነበረም። « ፈተናው ትንሽ ጠጠር ይል ነበር። ከብዶኝ ነበር።  የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች 28 ነበርን። ከኛ መካከል ያለፍነው ስድስት ነን» የምትለው ሊዲያ ብዙ ተማሪዎች ፈተናውን አለማለፋቸው አላስገረማትም። እንደ ሀገር ደረጃ ባይሆንም እንደ ክፍል ደረጃ ትረዳዋለች። «  እናውቀው ነበር። ገና ሳንፈተን ማን ያልፋል እያልን ስናስብ። 8 ወይም 9 ልጆች ነበር የቆጠርነው።  ሁለት ልጆች ከእኛ እኩል አጥንተው የወደቁ አሉ። የእነሱ ነው ያሳዘነኝ እንጂ የ20ው ተማሪዎችን መውደቅ እረዳለሁ።»
አንዳንድ የዘንድሮ የ 12ኛ ክፍል ተማሪዎች ከፈተና በኋላ እንደገለፁልን ወደ ከፍተኛ ተቋም ሄደው በተፈተኑበት ወቅት ስለገጠሟቸው ችግሮች እና እነዚህም በፈተናቸው ውጤት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊፈጥር እንደሚችል ገልፀውልን ነበር። ከጀርመን ተመልሳ በጅማ ከተማ የተፈተነችው ፌኔትስ ትዝብት ምን ይመስላል? « እዛ ያለው ሁኔታ ብዙ ነገሩ አይመችም ነበር። ሌሊት መነሳቱ፤ በዛ ላይ ማታ ተማሪ በቂ እንቅልፍ አያገኝም። የዩንቨርስቲ ንፅህናው፤ ታመው እንኳን መድኃኒት ማግኘት ይከብድ ነበር እና ብዙ እዛ (ዮንቨርስቲ) የነበሩት ነገሮች ፈታኝ ነበሩ» 

የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና እንደተጠናቀቀ ዶይቸ ቬለ በተለያዩ አራት ተቋማት ፈተናቸውን የወሰዱ ተማሪዎችን አነጋግሮ ዘገባ ሰርቶ ነበር። በጎንደር ከተማ ፈተናውን ከወሰደው ተማሪዎች አንዱ አበበ ብላችሁ ጥሩኝ ያለን ተፈታኝ ይገኝበታል። በፈተናዉ ወቅት በፋኖ ታጣቂዎች እና በመከላከያ ሰራዊት መካከል በነበረ ውጊያ ሙሉ ፈተናውን መውሰድ እንዳልቻለ እንዲሁም የተኩስ ድምፅ እየተሰማ ፈተና እንደተፈተነ በወቅቱ ገልፆልን ነበር። ወጣቱ 297 ነጥብ በማግኘት ፈተናውን ሳያልፍ ቀርቷል።  አቶ መንግሥት ታከለ አበበ የተማርበት  የአዞዞ ድማዛ 2ኛ ደረጃ የመንግሥት  ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ናቸው። በጎንደር ከተማ በነበረው ውጊያ ምክንያት ፈተናውን ያልወሰዱ ተማሪዎች ፈተናውን ወስደው እንደው እና ውጤታቸውን በተመለከተ ጠይቀናቸዋል። « ሁለት ተማሪዎች በራሳቸው ፍላጎት ዝግጁ አይደለንም ብለው ፈተናውን አልወሰዱም።  260 ተማሪዎች ግን ለፈተና ተቀምጠው 16 ተማሪዎች ከግማሽ በመቶ በላይ አምጥተዋል። » ይህም ከወደቁት ተማሪዎች አንፃር አንፃራዊ እና ጥሩ የሚባል እንደሆነ ርዕሰ መምህሩ ይናገራሉ።
የዘንድውን ብሔራዊ ፈተና ውጤት በተመለከተ ትምህርት ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው መግለጫ መሠረት በ 2014 ዓ.ም ከ 50 በመቶ እና ከዚያ በላይ ያገኙት ተማሪዎች 3.3 በመቶ ብቻ ነበር። ዘንድሮ ያለፉት ተማሪዎች ቁጥር መጠነኛ ቢሆንም በ0.1 ቀንሷል። ወጣት መለሰ አምናም ዘንድሮም ፈተናውን ወስዷል። ነገር ግን አሁንም ዉጤት አላመጣም። « ባለፈው ዓመት በጣም ተነሳሽነት ነበረኝ። ነገር ግን አልተሳካም። ዘንድሮ የጎን ስራ እየሰራሁ ብዙም ዝግጅት አልነበረኝም። እንደ አጋጣሚ ሄጄ ተፈተንኩኝ። ውጤቱ ግን የወረደ ነበር» ይላል። ተስፋ መቁረጥ መለሰ ላይ ብቻ አይደለም የሚታየው።  የ12ኛ ክፍል የኬሚስትሪ መምህር የሆኑት ዘነበ ኃይሉ ቢያንስ ዘንድሮ ከአምና የተሻለ ነገር ጠብቀው ነበር። ይሁንና እሷቸው ከሚያስተምሩበት እና ኮንሶ ውስጥ  ከሚገኘው አይሎታ ዶጋቱ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አንድም ተማሪ ዘንድሮ አላለፈም። « እንደ ትምህርት ቤት በጣም ነው የተሰማን። የተሻለ ጥረት ሲደረግ ነበር። የካሊኩለም ለውጥም ነበር። ውጤቱ ይኼ መሆኑ ሞራላችን ተነክቷል። ውስጣችንም አዝኗል። መምህር ዘነበ ከሚያስተምሩበት ትምህርት ቤት የተመዘገበው ትልቁ ነጥብ 348 ነው። ይህም አንድ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ ያስመዘገበው ሲሆን ከማለፍ ሁለት ነብጥ ጎድሎታል። ይህንን ትምህርት ቤት ጨምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ ዘንድሮ  ከ1328 ትምህርት ቤቶች አንድም ተማሪ አላለፈም።  ታድያ የተማሪዎች ሞራል እንዳይዳከም ምን ሊሰራ ታቅዷል? መምህር ዘነበ ሰሞኑን ውይይት እና ስልጠና ነበር ይላሉ።  « አዲስ በተመሰረተችው ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ላይ የመምህራን ስልጠና ነበር። የመፅሀፍ ትውውቅ አሉ። ይኼ ግን መጀመሪያ ነበር መካሄድ የነበረበት። ጥያቄዎችንም አንስተን ነበር።» የሚሉት የኬሚስትሪ መምህር  ለተከታታይ ሁለት አመታት ተማሪዎች በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ካለፉ ምንም አይነት ለውጥ ይኖራል ብለው አይጠብቁም። ስለሆነም መፅሀፍ እና መምህራን መሟላት እንዳለባቸው ያሳስባልሉ።
ዶክተር እሸቱ ከበደ የትምህርት ምዘና እና ፈተና አገልግሎት ዋና ዳሬክተር ናቸው።  የሚሰሩበት ተቋም በዋናነት የትምህርት ምዘና ምርምር ይሰራል፣ ሀገር አቀፍ ፈተናዎችን ይፈትናል እንዲሁም ውጤቱን የማሳወቅ ኃላፊነት እንዳለው ዋና ዳሬክተሩ ለዶይቸ ቬለ አስቀድመው አስረድተዋል። የ12ኛ ክፍል ውጤት ይፋ ከሆነ በኋላ ቅሬታ ያለቸው  እስከ ጥቅምት 5 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ ቅሬታቸውን ማቅረብ እንደሚችሉ ተቋማቸው ይፋ አድርጎ ነበር። በዚህም መሠረት የተለያዩ ቅሬታዎች እንደቀረቡ ዶክተር እሸቱ ለአብነት ያህል የተወሰኑትን ጠቅሰውልናል። « የፎቶ ጥራት ችግር ያጋጠማቸው ቅሬታ ያቀረቡ አሉ። የተሻለውን ፎቶ እናደርግላቸዋለን ማለት ነው። ሌላው ስማቸው ላይ ስፔሊንግ የተሳሳቱ እንዲሻሻልላቸው ያቀረቡ አሉ።  ውጤት አነሰኝ ብለው ቅሬታም ያቀረቡ አሉ» ብለዋል። እነዚህ እና ሌሎች ተቋሙን የሚመለከቱ እና የማይመለከቱ ቅሬታዎች ደርሷቸው እንደነበር ያብራሩልን ዶክተር እሸቱን ከአሁን በኋላም ቅሬታ ማቅረብ ይቻል እንደው ጠይቀናቸዋል።  « በዚህ ፈተና ዙሪያ ላይ የሚያቀርቡበት ጊዜ አብቅቷል። ነገር ግን እኛ የመንግሥት ተቋም ነን እና አመቱን ሙሉ በሰጠነው አገልግሎት ላይ ቅሬታ አለኝ የሚል ካለ ማንኛውንም ቅሬታ ማቅረብ ይቻላል» ሲሉ መልሰዋል።
ዶክተር እሸቱ የተወሰነ ቡድን በኃይማኖት በብሔር ወይም በፓለቲካ የሚጠቀም ወይም የሚጎዳ እንዳይሆን ተቋሙ በፈተና አወጣጡ እና አፈታተኑ ላይ በፍታህዊተት ላይ ተመርኩዞ መስራቱን ያስረዳሉ። « ሌላው ኢትዮጵያ ውስጥ ፈተና የሚዘጋጀው የተማሪዎችን ስርዓተ ትምህርት መሠረት ያደረገ ነው። እነዛን ተማሪዎች እጅ ላይ ካለው መፅሀፍ ጋር ሄደን እናዛምዳቸዋለን። ተማሪው በእጁ የሚሰጠው መፅሀፍ ላይ የሌለን ወደ ፈተና አናመጣም።» ይላሉ። አንድም ተማሪ እንዳላለፉባቸው የተገለፁት 1328 ትምህርት ቤቶች ምን አይነት ትምህርት ቤቶች ናቸው?  የመንግሥት? የግል? አካባቢያቸውስ? በዚህ ላይ ጥናት ተደርጎ ይሆን? ዶክተር እሸቱ ሁሉም አይነት ትምህርት ቤቶች እና በሁሉም ክልሎች ምንም ተማሪ ያላለፏባቸው ትምህርት ቤቶች አሉ ይላሉ።« ነገር ግን በእናንዳንዱ ክልል ምን ያህል ነው ከተባለ በአንዳንዶቹ ክልል ብዙ ቁጥር በሌሎቹ ደግሞ በጣም ትንሽ ቁጥር ያለባቸው ትምህርት ቤቶች አሉ» ይላሉ።ይህንንም ትምህርት ሚኒስቴር  ኮሚቴ አደራጅቶ እና ለይቶ ጥናት የሚያደርግበት እንደሆነ መረጃው እንዳላቸው ዶክተር እሸቱ ለዶይቸ ቬለ ገልፀዋል። በዚህም ጥናት መሠረት ትምህርት ቤቶቹ የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ መሰረታዊ ችግራቸውን ለማወቅ ይቻላል» ይላሉ  የትምህርት ምዘና እና ፈተና አገልግሎት ዋና ዳሬክተር ዶክተር እሸቱ ከበደ ።  

ልደት አበበ

አዜብ ታደሰ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW