እንደ ኢሬቻ ያሉ ህዝባዊ በዓላት አገራዊ ፋይዳቸው
ሰኞ፣ መስከረም 26 2018
ደማቅ በሆነው የኢሬቻ ሆራ-ሀርሰዲ ከትናንት በስቲያው የዋዜማው ጀምሮ ከተለያዩ አቅጣጫዎች በመጡ እንግዶች ተጨናንቃ አምሽታና ውላ ያሳለፈችው ቢሾፍቱ ከተማ እንደ ወትሮው በኢሬቻ ለት እጅግ በርካታ እንግዶችን አስተናግዳለች፡፡
ትናንት ማለዳውን በቱለማ አባገዳዎች የተከፈተው የኢሬቻ ስነስርዓት በሆራ-ሀርሰዲ ኃይቅ ተዳሚዎችን አስተናግዶ ስከበር ስፍራው ከተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ዞኖች በመጡ በርካታ ተሳታፊዎች እና ከክልሉ ውጪ ከተለያዩ የአገሪቱ አከባቢዎች ብሎም በተወሰነ መልኩ በዓሉ ላይ በታደሙት የውጭ አገር ጎብኚዎች ደምቆም ነው ያለፈው፡፡
ህዝባዊ በዓሉን ለአንድነት ግንባታ
ለመሆኑ መሰል የኢትዮጵያ በዓላት ህዝቦችን ከማሰባሰብና ውበታቸው ባሻገር ለአገር ግንብታ እና የህዝቦች አነድነት ፋይዳቸው ምን ያህል ጠንካራ ነው? አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የኢሬቻ ሆራ-ሀርሰዲ ተሳታፊዎች እያደገ የመጣ ያሉት አከባበሩ በዚህ ዓመት በኢሬቻ ስፍራ ላይ በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ መስዕብነቱ መጨመሩን በመግለጽ ለበዓሉ አከባበር ከዚህም የላቀ ትሩፋቶች እንደሚጠበቁ አስረድተዋል፡፡
ከምዕራብ አርሲ ዞን ሻሸመነ ከተማ መጥተው በትናንቱ የቢሾፍቱው ሆራሀርሰዲ ኢሬቻ ላይ የተሳተፉት ጥላሁን ጋቢሶ ኢሬቻ ከበዓልነቱም ባሻገር የአንድነትን ስሜት የሚፈጥር ይሉታል፡፡ “ስለኢሬቻ ውቤት ተናግሮ መጨረስ ከባድ ነው፤ ታሪካዊም ነው፡፡ አንድነትን የሚያጠነክርም ነው” ሲሉ ነው አስተያየታቸውን የሰጡት፡፡
ጌታቸው ሽብሮ የተባሉ ሌላው አስተያየት ሰጪ የቢሾፍቱ ከተማ ነዋሪ ላለፉት 41 ዓመታት ከኢሬቻ ቀርተው አያውቁም፤ “ኢሬቻ መምጣት የጀመርኩት ከ1977 ዓ.ም. ጀምሮ ነው፤ አከባበሩ ላይም ቀሪቼ አላውቅም፤ በዚህም የሚያጓጓኝ የበዓሉ እየሰፋ እያደገ መምጣትና የተሳታፊዎች አንድነት ነው” በማለት በዚህ በዓል ፍቅር፣ አንድነት እና የህዝቦች አብሮነት መሰበኩ ፋይዳው ጉልህ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ታዳሚያኑ አከባበሩን ይበልጥ ትኩረት በመስጠት ለቱሪዝም መስዕብነት እና ባህልን ለማስተዋወቅ እንደሚረዳም አመልክተዋል፡፡ ከዚህም ባለፈ ለመሰል ህዝባዊ በዓላት የበለጠ ትኩረት በመስጠት ለቱሪዝም ግብዓትነት በማዋል አከባበሩን ለቱሪስቶች መሸጥ እንደሚገባም መክረዋል፡፡
የበዓሉ አከባበር ከውቤቱስ ባሻገር
አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ ከወንዶገነት እና አሰላ የመጡ ታዳሚያን በፊናቸው ባዩት ነገር መገረማቸውና በዓሉን አከባበር ውበት ለአንድነት መገንቢያ ማዋል እንደሚቻል ነው አስተያየታቸውን የሰጡበት፡፡
ከአዲስ አበባ በመሄድ ከጓደኞቹ ጋር ሁሌም የተለየ የሚለውን ቀን የሚያሳልፈውወጣት ፍቅሩ ሽፈራው በበኩሉ በኢሬቻ አንድነትና ወንድማማችነት ይሰበካል ይላል፡፡
በዚህ በርካቶች በሚሰበሰቡበት ክብረበዓሉ አንድነትና ሰላምን ብሎም ፍቅርን በህዝብ መሃል መስራት የሚያስችል እድል በመኖሩ ለዚህም ትኩረት እንዲሰጥ አስተያየታቸውን አክለዋል፡፡
ሥዩም ጌቱ
እሸቴ በቀለ
ፀሀይ ጫኔ