እንዳይንቀሳቀስ ማዕቀብ የተጣለበትን የሩሲያ ገንዘብ አውሮፓ ከትራምፕ ማስቆም ትችል ይሆን?
ዓርብ፣ ኅዳር 19 2018
ትልቅ ክርክር ያስነሳው በምዕራባውያን መንግሥታት እንዳይንቀሳቀስ ማዕቀብ የተጣለበት ፤ የሩሲያ በቢሊዮኖች የሚቆጠር የአሜሪካን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ነው።
ሩሲያ እንዳንታቀሳቅስ የተያዘባት ጥሪቷ ምን ያህል ነው የትስ ይገኛል?
እ.ጎ.አ. በ2022 ሩሲያ ዩክሬንን ስትወር፣ ወደ 300 ቢሊዮን ዩሮ (347 ቢሊዮን ዶላር) የሚጠጋ ከሩሲያ ውጭ የነበረ ጥሪቷን እንዳታንቀሳቅስ ምዕራባውያን መንግሥታት ማዕቀብ ጥለውባታል። ከእነዚህ ንብረቶች መካከል ለምሳሌ ያህል በባንክ የተቀመጡ ገንዘቦች፣ የመኖሪያ ቤቶች ፣ እንደ ጀልባ እና አይሮፕላን የመሳሰሉ መጓጓዣዎች ይገኙበታል።
በርካታ እንደ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ካናዳ፣ ብሪታንያ እና ጃፓንን ጨምሮ፣ በርካታ የአውሮፓ ህብረት አባል አገሮች እነዚህን የሩሲያ ንብረቶች እንዳይንቀሳቀሱ ይዘው የሚገኙ ሲሆን ከሁሉም ትልቁ ሐብት የሚገኘው ቤልጂግ ውስጥ ነው።
ኦይሮክሊር የተሰኘው እና ብራስልስ ውስጥ በሚገኘው የፋይናንስ ማከማቻ ብቻ 180 ቢሊዮን ዩሮ የሚጠጋ ማዕቀብ የተጣለበት የሩሲያ ጥሪት ይገኛል።
ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ፣ ሩሲያ የጀመረችውን ጦርነት በተያዘባት ሐብት እንድትከፍል አውሮፓውያን ገንዘቡን መጠቀም ሥለሚችሉበት ሁኔታ ሲወያዩ ቆይተዋል። ለመጨረሻ ጊዜ እንዲህ ዓይነት ውይይት ያካሄዱት ባለፈው ጥቅምት ወር ሲሆን ቤልጅግም ጥያቄውን ውድቅ አድርጋ ሳትፈርም ቀርታለች። ይህም የሆነ ጊዜ ቤልጂግ ገንዘቧን እንድትመልስላት ሩሲያ በህግ ትጠይቃት ይሆናል የሚል ስጋት ስላደረባት ነው። የአውሮፓ ህብረት በታህሳስ አጋማሽ በሚካሄደው ጉባኤ ላይ ቤልጂግን ለማሳመን አቅዶ የነበረ ቢሆንም የትራምፕ አዲስ ምክረ ሀሳብ ይህንን እቅድ አጨናግፏል። በአውሮፓ የውጭ ግንኙነት ምክር ቤት (ECFR) የጂኦኢኮኖሚክስ ባልደረባ አጋቴ ዴማራይስ እንደሚሉት ይልቁንስ አዲሱ የትራምፕ የሰላም ምክረ ሐሳብ "በአውሮፓ ያለውን የሩሲያ ሀብት ለመውሰድ" ያለመ ነው።
አሜሪካ በአውሮፓ የሚገኙ የሩሲያ ንብረቶችን ለአሜሪካ ኩባንያዎች ጥቅም ማዋል ትችል ይሆን?
በአውሮፓ የውጭ ግንኙነት ምክር ቤት (ECFR) የአውሮፓ ደህንነት ፕሮግራም ተባባሪ ዳይሬክተር ያና ኮብዞቫ እንደሚሉት አሜሪካ " እንዳይንቀሳቀስ ይዛ የምትገኘው የሩሲያ ኃብት 5 ቢሊዮን ዶላር ብቻ" ሲሆን በአውሮፓ አገራት የተያዙ ንብረቶችን እንዴት መጠቀም እንደሚገባ መወሰን አትችልም። ይሁንና "አሜሪካ በራሷ ግዛት ስለሚገኙ የሩሲያ ንብረቶች መወሰን ትችላለች" ብለዋል።
የአውሮፓ መሪዎች በትራምፕ እቅድ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ በግልጽ አሳይተዋል።
የጀርመን መራሄ መንግሥት ፍሪድሪሽ ሜርስ ለDW በሰጡት ቃለ መጠይቅ "በብራስልስ የሚገኙ የሩሲያ ንብረቶች ለአሜሪካውያን ሊከፈሉ አይችሉም፤ ይህ የማይታሰብ ነው" ብለዋል። ሜርስ ትናንት በጀርመን ፓርላማ ቡንደስታግ ባሰሙትም ንግግር ጉዳዩ የአውሮፓውያንን ውሳኔ የሚሻ እንደሆነ ተናግረዋል።« ለዩክሬይን፣ ለአውሮፓ እና አጋራችን ለሆነችው ዩናይትድ ስቴትስም ጭምር በግልፅ ማለት የምፈልገው ነገር አውሮፓን በሚመለከት ጉዳይ ከአውሮፓ ጋር ብቻ ነው ውሳኔ መወሰን የሚቻለው። ሩሲያ ህገ ወጥ ወረራዋን የምታቆም እና ወታደሮቿን ከውጭ መሬት ላይ የምታስወጣ ከሆነ ጦርነቱ ነገ ሊያበቃ ይችላል። »
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮ ለፈረንሳይ የሬዲዮ ጣቢያ RTL እንደተናገሩት «አውሮፓውያን እንዳይንቀሳቀስ ባገዱት ንብረት ላይ ምን ማድረግ እንዳለባቸው መወሰን የሚችሉት አውሮፓውያን ብቻ ናቸው» ብለዋል።
ለመሆኑ የትራምፕ ምክረ ሀሳብ እንዳይንቀሳቀስ ስለታቀደው የሩሲያ ጥሪት ምን ይላል?
ሩሲያ በምዕራባውያን መንግሥታት እንዳይንቀሳቀስ ማዕቀብ ከተጣለበት ጥሪቷ ውስጥ 100 ቢሊዮን ዶላር ዩክሬንን መልሶ ለመገንባት እንዲውል መስማማት አለባት። ዩክሬንም ሆነች ሩሲያ እንዳይንቀሳቀስ የተደረገውን ጥሪት ለመጠቀም ሙሉ ቁጥጥር አይኖራቸውም።
እንደ በአውሮፓ የውጭ ግንኙነት ምክር ቤት (ECFR) የጂኦኢኮኖሚክስ ባልደረባ አጋቴ ዴማራይስ ከሆነ ትራምፕ እያደረጉ ያሉት በአውሮፓ እንዳይንቀሳቀስ ታግዶ የሚገኘውን የሩሲያ የመጀመሪያዎቹን 100 ቢሊዮን ዶላር ወይም 86 ቢሊዮን ዩሮ ለመውሰድ ነው።
በዚህ ደግሞ የአሜሪካ መንግሥት እና የአሜሪካ ኩባንያዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ። ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የዩክሬን ባለ 28 ነጥብ የሰላም ዕቅድ እንዲፈረም ያስቀመጡት ቀነ-ገደብ ዛሬ ሀሙስ ነበር። ለትራምፕ ነገሮች እንዳሰቡት ባይሄዱም እቅዳቸው እንደሚሳካ አይጠራጠሩም። «ከስምምነት ለመድረስ ተቃርበናል ብዬ አስባለሁ። እናያለን። ፈጣሪ ይመስገን። ስምምነቱን ጨርሰናል። በፍጥነት ያልቃል ብዬ አስቤ ነበር፣ ግን ለውጥ አለ። ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ፣ አብዛኛዎቹ ሌሎች አስተዳደሮች በስምንት ዓመታት ውስጥ ካከናወኑት በላይ አከናውነናል። እናም ይህ በጣም ልዩ የሆነ ታንክስ ጊቪንግ ወይም የምስጋና በዓል ነው። ለብዙ በረከቶቹ እና ለታላቅ ስኬቱ እግዚአብሔርን እናመሰግናለን።»
ባለሙያዎች እንደሚሉት የአውሮፓ ህብረት ቤልጂየምን በፍጥነት ማሳመን እና እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል። የጂኦኢኮኖሚክስ ባልደረባ አጋቴ ዴማራይስ እንደሚሉት "አውሮፓ ህብረት የሩሲያን ንብረት ከተቆጣጠረ እና ለዩክሬን ብድር ከሰጠ „ትራምፕ 300 ቢሊዮን ዩሮ ማግኘት አይችሉም"
Vohra, Anchal / ልደት አበበ