1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ከእህቴ ልጅ ሞት በኋላ አቅም ያጡን እየለመንኩ አሳክማለሁ ብዬ ቃል ገባሁ»

ልደት አበበ
ዓርብ፣ መስከረም 17 2017

እንግዳወርቅ ጌታቸው እስካለፈው ወር ድረስ አረብ ሀገር ሆና ከውጭ ሀገር ገንዘብ እና የሰው ኃይል በማስተባበር ድጋፍ የሚሹ ሰዎች ርዳታ እንዲያገኙ ስታስተባበር ቆይታለች። አሁን ደግሞ በቦታው ላይ ሆና ታግዛለች።

Äthiopien -  Hilfe an Bedürftige
ምስል privat

«ከእህቴ ልጅ ሞት በኋላ አቅም ያጡን እየለመንኩ አሳክማለሁ ብዬ ቃል ገባሁ»

This browser does not support the audio element.

እንግዳወርቅ ጌታቸው ትባላለች። ወይም ደግሞ በቅፅል ስሟ እንግዱ  ዲፖ!  ተወልዳ ያደገቸው ጅማ ከተማ ሲሆን ዲፖ ያደገችበት ሰፈር ነው። «ዲፖ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች የሚኖሩባት ትንሽ ሰፈር ነች። ግን በጣም ብዙ ፍቅር፣ ብዙ መተሳሰብ፣ ብዙ አንድነት ያለበት ማህበራዊ ህይወቱ ለየት ያለ ሰፈር ነው»  
እንግዳወርቅን ያደገችበት ሰፈር ብቻ አይደለም ሰውን ለመተባበር ምክንያት የሆናት።  የእንግዳወርቅ ታላቅ እህት እና የእህቷ ልጅ ዋናውን ሚና ይጫወታሉ። ገና በልጅነቷ ወላጆቿን በሞት ያጣችው እንግዳወርቅን ያሳደገቻት ታላቅ እህቷ ናት።   በትንሽ ገንዘብ መስተንግዶ ተቀጥራ ትሰራ እና አምስት የቤተሰቡን አባላት ታስተዳድርም ነበር ትላለች እንግዳወርቅ ስለ እህቷ እና እንዴት ወደ በጎ አድራጎት ስራው እንደገባች ስትናገር፤ « አንድ ዳቦ አምጥታ አምስት ቦታ ከፋፍላ ነበር የምታበላን። ጠግበን፤ በፍቅር ነበር የምንኖረው። ሰው አጥቶ ማየት አልችልም። ሰው ራበኝ ሲል አልችልም። ለመጀመሪያ ጊዜ በማህበራዊ ሚዲያ ገንዘብ ያሰባሰብኩት ለእህቴ ልጅ ነበር። ምንም እንኳን የሚያስፈልገውን ገንዘብ ማሰባሰብ ብንችልም እሷ ግን ታክማም በህይወት ሳትቆይ ቀረች። እኔ ም ያኔ ለእንደሷ አይነት ወገን ሳላዳላ ከጎን እቆማለሁ ስል ቃል ገባሁ ። ከዛን ጊዜ በኋላ በጣም ብዙ ሰው አሳክሜያለሁ  » 

« ባልታከም እግርህ ይቆረጣል የተባልኩ ሰው ነኝ»

እንግዳወርቅ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ከተባበረቻቸው ሰዎች አንዱ አቶ መሪሰው ይባላሉ ።  ከ 12 ዓመት በፊት የመኪና አደጋ ደርሶባቸው የታከሙ ቢሆንም ህመሙ ዳግም አገርሽቶባቸው መራመድ ሁሉ አቅቷቸው  እንደነበር እና እግራቸውም በሰዎች ድጋፍ ከመቆረጥ እንደዳነ አጫውተውናል።  «የግል ሆስፒታሉ የጠየቀኝ ከፍተኛ ገንዘብ ነበር። ያንን ገንዘብ መክፈል ስላልቻልኩኝ ያማከርኩት እንግዱን ነበር። እሷም እኛ እያለን ምንም አትሆንም እናሳክምሀለን አለች።  ዶክተር ባርናባስ ደግሞ ሙያው በእኔ ነው እናንተ ደግሞ መድኃኒቱን ቻሉ ብሎ እሱ ነው ቀዶ ህክምናውን ያደረገልኝ።»
ስሙ ተደጋግሞ የተጠቀሰው ዶክተር ባርናባስ ወንድሙ የአጥንት ፣ መገጣጠሚያ እና የአደጋ ህክምና ዘርፍ ባለሙያ ነው። የ 33 ዓመቱ ወጣት ሀኪምስ ለአቶ መሪሰው በወቅቱ የተደረገውን ህክምና በተመለከተ ምን ይላል?« እግሩ ላይ በደረሰበት ጉዳት ለተወሰኑ አመታት ሲቸገር ቆይቷል።  እና ወደድሮው ሁኔታ እንዲመለስ በተቻለን መጠን አግዘንዋል። ይኼ እኔ ብቻ ሳይሆን የስራ ባልደረቦቼም ጭምር በቡድን አግዘነው ነው አሁን ደህና ደረጃ ላይ ያለው። »

ዶክተር ባርናባስ ወንድሙ የአጥንት ፣ መገጣጠሚያ እና የአደጋ ህክምና ዘርፍ ባለሙያምስል Privat

ቅንነት

ሌሎችንም ድጋፍ የሚሹ ሰዎች ደህና ደረጃ ላይ ለማድረስ ስራዬ ብላ የተያያዘችው እንግዳወርቅ ዶክተር ባርናባስን ጨምሮ ከጎኗ የቆሙ በርካታ የህክምና ባለሙያዎችን ሳታደንቅ እና ሳታመሰግን አላለፈችም። «ዶክተር ባርናባስ የተጠራበት ቦታ እየሄደ ስንት መራመድ ያቃታቸውን ሰዎች ቀና ያደረገ ነው።  ሀኪሞቹን በአካል አላቃቸውም ነበር። በሙያ የሚመለከታቸውን በስልክ ነው ደውዬ የምለምናቸው። የሰዎቹን ታሪክ ስነግራቸው ልባቸው ተነክቶ ነው ይህንን በቅንነት የሚያደርጉት»
«ቅንነት» ወጣቱ የህክምና ባለሙያ ባርናባስም ሊኖረን ያስፈልጋል የሚለው ነው። በተለይ እንደሱ ያሉ ሙያዊ ችሎታቸውን ተጠቅመው  በበጎ ፍቃደኝነት ሌሎችን መርዳት ለሚፈልጉ ሰዎች የሚመክረው። « የተቸገረ ሰው በየቤቱ፣ በየሆስፒታሉ ይገኛል። ቅን ልብ ነው ዋናው። አንድ ሰው ቅን ልብ ካለው የሰው ችግር ችግሬ ነው ብሎ ካሰበ ያንን ርዳታ በቀላሉ ማድረግ ይችላል።»

በተለያዩ ሀገራት ያሉ ኢትዮጵያውያን ሚና

እንግዳወርቅ ወይም በቅፅል ስሟ እንግዱ  ዲፖን የሚተባበሩዋት ሰዎች  የጅማ ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆኑ በተለያዩ ሀገራት ያሉ ኢትዮጵያውያን እንደሆኑ ነግራናለች።  ከእነሱም በተሰበሰበ የገንዘብ ድጋፍ ከፍተኛ ወጪ የሚያስወጣ ቀዶ ህክምናን ጨምሮ አቅመ ደካሞች የገንዘብ እና የቁሳ ቁስ ድጋፍ እንዲያገኙ ታደርጋለች። «የኃላእሸት የሚባል ልጅ አለ። 28 እናቶችን ለብቻው የሚረዳ።  ያንን ገንዘብ እሱ ሲሰጠን ነው። የወር አስቤዛ ገዝተን የምንሰጠው። በወር በወር ለ28ቱም እናቶች ከ4000  እስከ 5000 ብር ድረስ ለእያንዳንዳቸው ይልካል። »

እንግዳወርቅ ጌታቸው እና የሚያግዟት ወጣቶች ለአቅመ ደካማ ሰው ዘይት ሲያስረክቡምስል privat

ዛሬ አቶ መሪሰውም የተቸገሩ ሰዎችን ከእንግዳወርቅ ጋር ሆነው በአካል ከሚያግዙ ሰዎች አንዱ ናቸው። «እንዳግዝ ይበልጥ የገፋፋኝ ነገር ያኔ የተደረገልኝ ነገር ነው »ይላሉ።  
« ባልታከም እግርህ ይቆረጣል የተባልኩ ሰው ነኝ ። ዛሬ በሙሉ አካሌ ከተማ ውስጥ እየተንቀሳቀስኩ አለሁ። ሰው ነው ለእኔ የደረሰልኝ። አረብ ያሉ እህቶቻችን ለቤተሰቦቻቸው ነው ዋጋ እየከፈሉ የሚኖሩት። እሷ ደግሞ የሰው ቤት ውስጥ እየሰራች ከቤተሰብ አልፋ ለሌሎች ለተቸገሩ ሰዎችም የምታለቅስ ናት።»
ይላሉ አቶ መሪሰው ለሌሎች ኢትዮጵያውያንም አርዓያ መሆን ስለምትችለው በጎ አድራጊ ወጣት እንግዳወርቅ ጌታቸው ሲናገሩ። እንግዳወርቅ ለስራ ከነበረችበት ዮርዳኖስ ሆና ያግዟት የነበሩ ወጣቶችን በማህበር አቅፋ 35 ያህል ወጣቶች አሁን አብረዋት እየሰሩ እንደሆነም ነግራናለች።  


ልደት አበበ
ታምራት ዲንሳ  


 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW