እውን የሱዳን ጦር ከሲቪሉ ጋር ቀጥተኛ ውይይት?
ሐሙስ፣ ሰኔ 2 2014
ለፉት ስምንት ወራት በፖለቲካዊ ምስቅልቅል እና አለመረጋጋት የምትታመሰው ሱዳን የፖለቲካ ልኂቃን ትናንት ቀጥተኛ ንግግር መጀመራቸው ተዘግቧል። በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ያግዛል በሚል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባዘጋጀው የውይይት መድረክ የሱዳን ጦርን ጨምሮ ተቀናቃኝ ኃይላት ተሳታፊ ይኾናሉ ተብሏል። ይህ አዲስ የውይይት ሐሳብ የመጣው የሱዳን ጦር መሪ ጄኔራል አብደል ፋታኅ ኧል ቡራን በሀገሪቱ የጣሉት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባለፈው ወር መነሳቱ ይፋ ከተደረገ በኋላ ነው። ጄኔራል አብደል ፋታኅ ጥቅምት 15 ቀን 2014 ዓ.ም በመፈንቅለ-መንግሥት በትረ-ሥልጣኑን ከጨበጡ በኋላ በመላ ሱዳን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተጥሎ ቆይቷል። በሱዳን ፖለቲካ ጉልኅ ሥፍራ የሚሰጣቸው አንዳንድ የሲቪል ማኅበረሰብ አባላት በውይይቱ ተሳታፊ ላለመሆን ወስነዋል። ዋና ከተማዪቱ ካርቱም ውስጥ ነዋሪ የኾኑት ሱዳናዊ የመብት አራማጅ ሞሐመድ ዮሲፍ አልሙስጠፋ እንደሚሉት ውይይቱ ይበልጥ የሚጠቅመው ጦሩን ነው።
«ቡርሃን ከእሳቸው ጋር ካበረው ጦር ጋር በመኾን ሀገሪቱ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉ የአብዮቱ ኃይላትን ይኸው አሁን በቂ ነጻነት እየሰጠናችሁ ነው፤ እስረኞችንም በመላ እየለቀቅን ነውና ለመደራደር መጥታችሁ ተወያዩን በማለት ውዥንብር ለመፍጠር እየሞከሩ ነው። ከጦሩ ጋር የሚደረግ ማንኛውም አይነት ንግግር የመጨረሻው ግብ ዳግም ከእነሱ ጋር ትብብር መፍጠር ነው። ያም ለፈጸሙት ወንጀል እንዳይጠየቁ ዋስትና መስጠት ነው።»
ጄኔራል አብደል ፋታኅ ኧል ቡራን በቅርቡ 125 የተቃውሞ ሰልፈኞችን ከእስር ፈትተዋል። ይህን ርምጃም፦ «በሽግግር ሒደቱ መረጋጋትን የሚያመጣ ፍሬያማ እና ትርጉም ያለው ውይይት» ሲሉ ገልጠውታል ጄነራሉ። ከ70 በላይ የመብት አራማጆች ግን አሁንም የሱዳን እስር ቤቶች ውስጥ ይገኛሉ።
ሱዳን ጦሩ መፈንቅለ መንግሥት ከፈጸመበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን አልተረጋጋችም። በየሳምንቱ ማለት በሚቻል መልኩ በተቃውሞ ስትናጥም ቆይታለች። የሱዳን ጦር ያልታጠቁ የተቃውሞ ሰልፈኞች ላይ ባለፈው ሳምንት በከፈተው ተኩስ አንድ ሰው በጥይት ተገድሏል። ይህም ግድያ የተቃውሞ ሰልፎችን ለመቀልበስ የሱዳን የፀጥታ ኃይላት በወሰዷቸው ርምጃዎች የተገደሉ ሰዎች ቁጥርን 100 እንዳደረሰው የሱዳን የሐኪሞች ኮሚቴ ገልጧል።
የሀገሪቱ ምጣኔ-ሐብትም ተሽመድምዷል። እንግሊዝ ለንደን ውስጥ ነዋሪ የኾኑት ሰዳናዊው የመብት አራማጅ ሱዳናውያን የሚፈልጉትን በግልጽ እና በጉልኅ አስተጋብተዋል ባይ ናቸው።
«አብዛኞቹ ሱዳናውያን በመፈክሮቻቸውም እንደሚያስተጋቡት ሁሉ ከጦሩ ጋር አንዳችም ትብብር፤ ወይንም ማቻቻል አለያም ለጦሩ እጅ መስጠት እንደማያስፈልግ ግልጽ የኾኑ ይመስለኛል። ጦሩ ሱዳንን በአንዳች አይነት ሒደት ወደፊት ማራመድ ከፈለገ ግን፤ ያኔ ጦሩ በዋናነት ሁለት ጉዳዮችን እንደውም ሦስት ጉዳዮችን አጽንዖት ሊሰጥባቸው ይገባል።»
ሰዳናዊው የመብት አራማጅ እነዚህን ሦስት ጉዳዮች ሲያብራሩም፦ በዋናነት ጦሩ በሱዳን ምጣኔ ሐብት ላይ ያለውን የበላይነት ለሕዝቡ ማስረከብ ይገባዋል ብለዋል። በሁለተኛ ደረጃም ጦሩ፣ የፈጣን ድጋፍ ኃይላት እና በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ፖሊሶች ፈጸሟቸው ያሏቸው «ታሪካዊ ወንጀሎች» ላይ ምርመራ ሊካኼድ እና ተጠያቂ የሚኾኑበት መንገድም ሊመቻች ይገባል ብለዋል። የእውነት እና እርቅ ኮሚሽን እንዲመሠረትም ጠይቀዋል። በሦስተኛ ደረጃ ጦሩ ከፖለቲካው ወጥቶ ሀገሪቱ ወደ ዴሞክራሲያዊ መንገድ የምታቀናበት ጥረት ሊደረግ እንደሚገባ ሱዳናዊው አራማጅ አጽንዖት ሰጥተዋል። ጦሩ እነዚህን ጉዳዮች ስለመፈለጉ ግን በርካቶች ጥርጣሬ እንደገባቸውም ለዶይቸ ቬለ (DW)አክለዋል። «አብዛኛው ሰው በተለይም የመብት አራማጆች ጉዳዩ እጅግ አሳስቧቸዋል ጥርጣሬም ገብቷቸዋል። ምክንያቱም በተለይ ደግሞ መፈንቅለ መንግሥት ከፈጸሙት ጋር ውይይት እንዲደረግ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግፊት እያደረጉ ይመስላሉ ብሎ ነው ሰዉ የሚረዳው። በአጠቃላይ ደግሞ የጦሩ ማንኛውንም አይነት ውይይት የማከናወን አቅሙን የመተማመን እና ተገቢነቱ ላይ በሰዉ ዘንድ ያለው አመለካከት በጣም ዝቅ ያለ ነው። ምክንያቱም ያ የጦሩ ተግባር አይደለምና።»
ሱዳን በጠቅላይ ሚንሥትር አብዳላ ሐምዶክ ይመራ የነበረው ጊዜያዊ መንግሥት በጦሩ ከተወገደበት ጊዜ አንስቶ በጦሩ፣ በፖለቲካ ልሒቃኑ እና በሲቪሉ ማኅበረሰብ ዘንድ መግባባት ላይ አልተደረሰም። ሱዳን ውስጥ ለ100 ሰልፈኞች ሞት እና ከ5,000 በላይ ሰዎች የመቁሰል አደጋ እስካሁን ተጠያቂ የተባለ አካልም የለም። እናስ ሱዳን አሁን የጀመረችው ውይይት ገዳዮችን፣ ተጠያቂ አድርጎ ተጎጂዎችንስ ይክስ ይሆን ወይንስ የመብት አራማጆች እንደፈሩት በእጅ አዙር ጦሩን እንደገና ያጠናክር በሒደት የሚታይ ነው።
ማንተጋፍቶት ስለሺ/ ጄኒፈር ሆላይስ/ ኬርስተን ክኒፕ
ኂሩት መለሰ