1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

"እዚህ የአበሻ ቀጠሮ የለም" ኢትዮጵያ ውስጥ ያደገችው ኖርዌያዊት ሀኔ

ልደት አበበ/ Lidet Abebe
ዓርብ፣ ኅዳር 19 2018

ምናልባት ማህበራዊ ሚዲያ የሚከታተሉ ወጣቶች ሀኔን በምትሰራቸው ቪዲዮዎች ያውቋት ይሆናል። የሮርዌይ ዜጋ ስትሆን አማርኛ ትናገራለች። ከእጇ ላይም የቡና ስኒ አይጠፋም።

ኖርዌያዊቷ ሀኔ
ኖርዌያዊቷ ሀኔምስል፦ privat

ኢትዮጵያ ውስጥ ያደገችው ኖርዌያዊት ሀኔ

This browser does not support the audio element.

ብዙዎች ቲክቶክ እና ኢንስታግራም ላይ „desyemil.amharic  „ወይም „ሀኔ “ በሚል ስሟ ያውቋታል። ቲክቶክ ላይ በአጭር ጊዜ ከ 96 ሺ በላይ ተከታዮችን ማፍራት ችላለች። 

ሀኔ 37 ዓመቷ ነው። የዘር ሀረጓ ኖርዌይ ቢሆንም በውስጧ ኢትዮጵያዊነት እንዳለ በምትሰራቸው ቪዲዮዎች ትመሰክራለች። ከኢትዮጵያ ጋር ያስተሳሰራት አጋጣሚ የጀመረው ገና በልጅነቷ ነው።

 "የአባቴ ወላጆች ለተለያዩ ስራዎች ከ40 ዓመታት በላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ኖረዋል። በዚህ ምክንያት አባቴ ያደገው እዛው ነው። ከእናቴ ጋር ከተጋቡ በኋላ ደግሞ አብረው ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ለ10 ዓመት በዲላ ፣ሜጋ፣አዲስ አበባ እና ሀዋሳ ኖረዋል። እኔም ያደኩት እዛ ነው። ወደ ኖርዌይ ስንመለስ የ10 ዓመት ልጅ ስለነበርኩ አማርኛ እረሳሁ።" ስትል ታብራራለች።

ሀኔ በኢትዮጵያ ከጅብ ጋር ምስል፦ privat

ሀኔ አማርኛዋን ለማሻሻል ቆርጣ የተነሳች ይመስላል። በምትሰራቸው ቪዲዮዎች ላይ በተቻላት አቅም በአማርኛ ትናገራለች፤ ምሳሌያዊ አነጋገሮች ሳይቀር በአማርኛ እየፃፈች ታጠናለች። በድምሩ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሰባት ዓመታት ያህል እንደኖረች የምትናገረው ሀኔ ዛሬ ላይ አማርኛ ስታወራ አንዳንድ ሰዎች AI ወይም አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ነሽ ይሏታል።

"አማርኛ ስለምናገር፣ አማርኛ ስለምችል ፤ ባህሉንም ጭምር ። አንቺ AI ነሽ ይላሉ። አያምኑኝም" ትላለች። ያኔም ሀኔ አንድ ነገር ለማድረግ ወሰነች፤ ሙዚቃ ለማዘጋጀት!

AI ነሽ ይሉኛል

«ሙዚቃውን በAI ነው የሰራሁት ለቀልድ ነው። እኔ መዝፈን ስለማልችል ግጥሙን ፃፍኩ እና የቀረውን በAI ነው የሰራሁት። የኢትዮጵያ ባህላዊ ዜማ እና የሴት ድምፅ ብዬ » ስትል ሙዚቃውን እንዴት እንዳዘጋጀች ስትናገር።
"እንደዚህ መዝፈን ብችል ዝነኛ በሆንኩ ነበር" የምትለው ሀኔ  ለሌሎች ካጋራቻቸው ሙዚቃዎች በስተቀር ምንም አይነት AI እንዳልተጠቀመችም ትናገራለች።

ሀኔ በድምሩ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሰባት ዓመታት ያህል ኖራለችምስል፦ Privat


ሀኔ አማርኛዋን ከማዳበር በተጨማሪም በሁለቱ ሀገራት ማለትም ኢትዮጵያ እና ኖርዌይ መካከል የባህል ትስስር መፍጠር ትፈልጋለች። ቢያንስ በምትሰራው ቪዲዮዎች  ሀኔ «ቡናድ» የሚባለውን የኖርዌይ ባህላዊ ልብስ ሌሎች ሰዎች ከሌሎች ባህላዊ አልባሳት ጋር አዋህደው የለበሱትን ስታይ እሷም « ኢትዮጵያዊ ጎኔን ማሳየት የምችልበትን ቡናድ»  ልስፋ ብላ ተነሳሳች።

ከአዲስ አበባ ሽሮ ሜዳ ከገዛችው ጥበብ ጋር አቀናብራ የሰፋችውን ልብስ ለማህበራዊ ሚዲያ ተከታዮቿ ስታሳይም አድናቆት ችረዋታል። ሀኔ በአጠቃላይ ከሰዎች የምታገኛቸው አስተያየቶች ፈገግ ያስብሏታል።

"በጣም ብዙ አለ። ከቀልድ አንስቶ ውሰጂኝ ፣ላግባሽ ፣ውለጅልኝ የመሳሰሉት አይጠፉም። አማርኛ በጣም ጎበዝ ነሽ ። AI ነሽ አለ። ግን ለኔ ትልቁ ነገር ውጭ ሀገር ያደጉ ዲያስፖራ ወጣቶች የሚልኩልኝ መልዕክት ነው። ብዙዎች አማርኛ መናገር በደንብ አይችሉም። እና የእኔን ይዘት አይተው ቋንቋውን ለመማር እንደተነሳሱ ሲነግሩኝ። ደስ ይላል "

በአሁኑ ሰዓት ኖርዌይ የምትኖረው እና ፀሀይ እና ሙቀት እንደናፈቃት የምትናገረው ሀኔ በሙያዋ መምህርት ናት። "ለስደተኞች የኖርዌይን ቋንቋ እና ባህል አስተምራለሁ" ትላለች።  መምህርትነቷ አልፎ አልፎም የምትሰራቸው ቪዲዮዎች ላይ ይንፀባረቃል።

ሀኔ ተሞክሮዋን በማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን ለማጋራት ምን አነሳሳት? 

"ስለ ኢትዮጵያ ብዙ ጊዜ አስባለሁ። ቤተሰብ እዛ አለኝ። ኢትዮጵያ ያሉ ጓደኞች አሉኝ ።አሁን ደግሞ ሶሻል ሚዲያ ቀላል ስለሆነ ቋንቋውን ከመልመድ እና ከእኔ የሚማሩት ነገር ካለ ብዬ ነው።"

ሀኔ «ቡናድ» የሚባለውን የኖርዌይ ባህላዊ ልብስ ሌሎች ጥበብ ጋር ቀላቅላ የተፋችው ቀሚስምስል፦ privat

ሀኔ እግረ መንገዷንም የኢትዮጵያ ምግቦችን ማብሰል እየተለማመደች ነው። ቪዲዮ ቀርፃ የለጠፈችውን አዋዜ ጥብስ ብዙዎች የወደዱላት ሲሆን አንዳንዶች  በሰጧት አስተያየት መሠረት እርሾ ሰርታ ሰሞኑን እንጀራ ለመጋገር ሊጥ ያቦካችበትን ቪዲዮ ለጥፋለች።  ሀኔ ስለሚከብዳትም ነገር ትጠይቃለች። ኢትዮጵያውያን ስለ ኖርዌይ ቢያውቁ  የምትለውም ስለ ቀጠሮ አያያዝ እና  ሰዓት ማክበር ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ነው።
"እዚህ አራት ሰዓት ከተባለ አራት ሰዓት ነው።የአበሻ ቀጠሮ የሚባል ነገር የለም"

ትክክለኛውን ከኢትዮጵያ የመጣ እና የጤፍ እንጀራ ለመግዛት እስከ  40 ደቂቃ በመኪና ነድታ የምትጓዘው ሀኔ ስለምትወዳቸውም የኢትዮጵያ ምግቦችም ነግራናለች።  "ሽሮ፣ ክትፎ፣ ጭቅና ጥብስ፣ጨጨብሳ ፣ ቋንጣ ፍርፍር፣ ዶሮ ወጥ። ከዱለት እና ጥሬ ስጋ ውጪ ሁሉንም እወዳለሁ። ….የኢትዮጵያ ቡናን በተለይ የጀበና ቡና በጣም ነው የምወደው።" 

ሀኔ በኖርዌይ ጭቃ በጭቃ ሆናምስል፦ privat

ሀኔ ለአድናቂዎቿ እና ወጣቶች ማስተላለፍ የምትፈልገው መልዕክት?

 „በማንነታችሁ እና በባህላችሁ መኩራት አለባችሁ“ የሚል ነው። እሷም ያደገችባቸውን ሁለት ባህሎች በኩራት እያቀረበች ትገኛለች። ሀኔ ያቦካችው ሊጥ በርግጥ እንጀራ ሆኖ እንደው ለማወቅ ከፈለጋችሁ „desyemil.amharic  ብላችሁ ኢንስታግራም ወይም ቲክቶክ ላይ ብትፈልጓት ሰሞኑን አዲስ ቪዲዮ መለጠፏ አይቀርም። 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW