1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስኢትዮጵያ

እየተባባሰ የመጣው በልጆች ላይ የሚደርስ የሳይበር ጉልበተኞች ጥቃት

ረቡዕ፣ ነሐሴ 1 2016

በቅርቡ በ 44 አገሮች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት የ«ሳይበር ቡሊንግ» መጨመሩን ያሳያል። በጥናቱ መሰረት የሳይበር ጉልበተኞች ጥቃት ከ6 ተማሪዎች አንዱን ይጎዳል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት ችግሩ በዓለም አቀፍ ደረጃም አሳሳቢ ነው።ለመሆኑ ችግሩ በኢትዮጵያ ምን ያህል ነው? ችግሩ ሲያጋጥምስ ምን መደረግ አለበት? እንዴትስ መከላከል ይቻላል?

የሳይበር ቡሊንግ ልጆች በትምህርት ውጤታማ እንዳይሆኑ ያደርጋል።
የሳይበር ቡሊንግ ልጆች በትምህርት ውጤታማ እንዳይሆኑ ያደርጋል።ምስል Julio Pelaez/Maxppp/dpa/picture alliance

እየተባባሰ የመጣው በልጆች ላይ የሚደርስ የሳይበር ጉልበተኞች ጥቃት

This browser does not support the audio element.


በቅርቡ በ 44 አገሮች ላይ የተደረገ ጥናት  የሳይበር ጉልበተኝነት /ሳይበር ቡሊንግ/ መጨመሩን ያሳያል። በጥናቱ መሰረት የሳይበር ጉልበተኝነት ከ6 በትምህርት ላይ ከሚገኙ ልጆች አንዱን ይጎዳል።መረጃዎች እንደሚያሳዩት ጥናቱ በተካሄደባቸው ቦታዎች ብቻ ሳይሆን ችግሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ አሳሳቢ ጉዳይ ነው።ለመሆኑ ችግሩ በኢትዮጵያ ምን ያህል ነው? ችግሩ ሲያጋጥምስ ምን መደረግ አለበት? እንዴትስ መከላከል ይቻላል? የዛሬው የሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ዝግጅት ምላሽ አለው።
የቴክኖሎጂ እያደገ እና እየተሻሻለ መምጣት የሰዎችን የዕለት ተዕለት ኑሮ እና መስተጋብሮችን የማሻሻል  ዕድሎችን ፈጥሯል። የዚያኑ ያህል ደግሞ አሉታዊ የሆኑ ነገሮችንም ይዞ መምጣቱ አልቀረም። በተለይም ለአዳጊዎች እና ለወጣቶች። ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሰፋ ያለ የስክሪን ጊዜ/ማለትም በስማርት ስልኮች ሆነ በኮምፕዩተር የተለያዩ ነገሮችን ረዥም ጊዜ መመልከት/ ከስነ-ልቦና ደህንነት ጋር ይገናኛል። ከፍተኛ የጭንቀት እና የመንፈስ መረበሽንም ያስከትላል። የስክሪን ጊዜ ከሚያመጣው ይህንን መሰል ችግር ባሻገር ልጆች በሳይበር ጉልበተኞች ሲጠቁ ደግሞ ጉዳቱ ከፍ ያለ ይሆናል። 
በቅርቡ በ 44 አገሮች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው ከጎርጎሪያኑ  2018 ዓ/ም ጀምሮ የሳይበር ጉልበተኝነት መጨመሩን ያሳያል። በጥናቱ መሰረት ሳይበር ጉልበተኝነት ከ6  በትምህርት ቤት ከሚገኙ ልጆች አንዱን ይጎዳል። ጥናቱ የወጣቶች የዲጅታል እና የበይነመረብ መስተጋብር እየጨመረ መምጣቱን ለችግሩ ዋና መንስኤ አድርጎ አቅርቧል።
ጥናቱን መሰረት በማድረግ ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው የሳይበር ደህንነት ባለሙያው አቶ ብሩክ ወርቁ በኢትዮጵያም ችግሩ ቢበዛ እንጅ የሚያንስ አይደለም ይላሉ። ምንም እንኳ ችግሩ በኢትዮጵያ በቂ ጥናት ባይደረግበትም ችግሩ ስለመኖሩ እሳቸው የተመለከቷቸውን ሁለት የሀገር ውስጥ ጥናቶችን በዋቢነት ይጠቅሳሉ።

አቶ ብሩክ ወርቁ የሳይበር ደህንነት ከፍተኛ ባለሙያ ምስል Privat

በአውሮፓ፣ እስያ፤ ካናዳ እና ሰሜን አሜሪካን ባካለለው በዚህ ጥናት ተመራማሪዎች የእኩዮች ጥቃት እና የሳይበር ጉልበተኝነት ለትምህርት በደረሱ ልጆች ላይ ዋነኛ ችግሮች መሆናቸውን አረጋግጠዋል። ይህም እየተባባሰ መምጣቱን አመልክተዋል። 
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ጥናቱ በተካሄደባቸው ቦታዎች ብቻ ሳይሆን የሳይበር ጉልበተኞች ጥቃት በዓለም አቀፍ ደረጃ አሳሳቢ ጉዳይ ነው። አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እና ዲጂታል አካባቢን ከመጠቀም ጋር ተያይዞ አሳሳቢነቱ ጨምሯል። በዓለም ላይ  ከ13 እስከ 15 አመት ዕድሜ ያሉ ከ3 ተማሪዎች አንዱ ይህ ያጋጥመዋል።በዚህ መንገድ 130 ሚሊዮን ተማሪዎች የዚህ ችግር ሰለባ መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅትም በልጅነት ዕድሜ የሚያጋጥም የሳይበር ቡሊንግ  እንደ ዋና የኅብረተሰብ የጤና ስጋት ይመለከተዋል።

የሳይበር ጉልበተኞች ጥቃት በየትኛውም ሰው ፣ ዕድሜ እና ፆታ ሊያጋጥም የሚችል ነው። ነገር ግን በልጆች ላይ ሲከሰት አደገኛ የሚሆነው ባልበሰለ እና በማደግ ላይ ባለ እእምሮ እንዲሁም  እየተሰራ ባለ ማንነት ላይ የሚሰነዘር ጥቃት በመሆኑ የሚተወው ጠባሳ ቀለል አይደለም። ተመራማሪዎች እንደሚሉት ይህ ችግር በትምህርት ውጤታማ ከአለመሆን እስከ ራስን ማጥፋት የሚያደርስ ተፅዕኖዎች ይኖሩታል።
ለመሆኑ ሳይበር ቡሊንግ  ምንድነው? መገለጫዎቹስ? አቶ ብሩክ ማብራሪያ አላቸው።የሳይበር ምህዳር ጥቃትና ጥበቃ

በአጠቃላይ የሳይበር ጉልበተኝነት የሚባለው አንድ ሰው ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ በሌላ ሰው ላይ የማዋረድ፣ ጉዳት የማድረስ ወይም ህመም የሚያስከትል ተግባር ሲፈፅም ነው። ይህም በኮምፒዩተር፣ በተንቀሳቃሽ ስልኮች እና በሌሎች የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ሆን ተብሎ የሚፈፀም ተደጋጋሚ ጥቃት ነው። የሳይበር ጉልበተኞች በማኅበበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ፣ በቪዲዮ ወይም በኮምፒውተር ጨዋታዎች፣ በበይነመረብ የውይይት መድረኮች እና የጽሁፍ መልዕክትን ጨምሮ በማንኛውም የኦንላይን  መቼት ውስጥ ተጎጂዎችን ያዋርዳሉ።የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዳፋ
ይህም የስም መጥፋትን፣ ማስፈራራትን፣ የግል ወይም አሳፋሪ ፎቶዎችን ማጋራት ወይም ማግለልን ሊያካትት ይችላል።
አቶ ብሩክ እንደሚሉት በዚህ ሁኔታ የሚፈጸሙ የየራሳቸው ባህሪያት ያሏቸው ቢያንስ ወደ 11 የሚጠጉ «የሳይበር ቡሊንግ» ዓይነቶች አሉ።

የሳይበር ቡሊንግ ራስን እስከማጥፋት ለሚያደርስ የስነልቡና ችግር ይዳርጋል።ምስል Antonio Guillen Fernández/PantherMedia/IMAGO

ማንኛውም ዓይነት የሳይበር ጉልበተኝነት በተጎጂው ደህንነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊያሳድር ይችላል። ልጆች ደግሞ ራሳቸውን እንዴት እንደሚጠብቁ ስለማያውቁ የሳይበር ጉልበተኝነት ሰለባ የመሆን ዕድላቸው እንዲሁም ጉዳታቸው ከአዋቂዎች ይጨምራል።
በተለይ በኢትዮጵያ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በሚደረጉ መስተጋብሮች ልጆችን እንደ ገቢ ማግኛ መጠቀም እየተለመደ በመምጣቱም በልጆች ላይ የሚደርሰው እንዲህ ያለ  ችግር የበረታ ይሆናል። የልጆች አእምሮ ሊሸከመው ከሚችለው በላይ የሚሰነዘሩ አሉታዊ አስተያየቶችም ልጆችን በቀላሉ ለቀውስ ሊዳርጋቸው እንደሚችል ባለሙያው ያስረዳሉ።ለልጆች አደገኛ የሆኑ መተግበሪያዎች የትኞቹ ናቸው?
የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ለወጣቶች ደህንነቱ የተጠበቀ የሳይበር አካባቢዎችን መፍጠርን ቅድሚያ እንደሚሰጡ ይገልጻሉ። አንዳንድ የቴክኖሎጅ ኩባንያዎችም  የምርት ውጤቶቻቸው በልጆች ላይ ምን ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ እና እንዴት ደህንነታቸውን እንደሚጠብቁ በተሻለ ለመረዳት ከባለሙያዎች ጋር የሚሰሩ አሉ። ነገር ግን ይህንን ለማድረግ ተጨማሪ ማይል መሄድ ለቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ትርፋማ ባለመሆኑ አይገፉበትም። ስለሆነም በኦንላይን  የልጆችን እና የአዳጊ ወጣቶችን ፍላጎት መጠበቅ እና ከጉዳት መከላከል በአብዛኛው በግለሰቦች፣ በቤተሰብ  እና በማኅበረሰቦች ትክሻ ላይ የወደቀ ነው።

ከሳይበር ጉልበተኝነት ምርምር ማዕከል የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ተደጋጋሚ ትንኮሳ ሲያጋጥም መልዕክቱን አጥቂዎችን ሙሉ በሙሉ ማገድ፣ ለቴክኖሎጅ ኩባንያዎች ችግሩን ሪፖርት ማድረግ፣ ይመከራል። ምስል Elada Vasilyeva/Zoonar/picture alliance

በተለይ ወላጆች የሳይበር ጉልበተኝነትን እና ተያያዥ ጉዳቶችን ለመከላከል ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ። ይሁን እንጅ፤ በኢትዮጵያ በወላጆች ዘንድ የዲጅታል ቴክኖሎጂ እውቀት አለመኖር ፣ የመፍቻ መንገዶችን እና ሕግ ስለመኖሩ አለማወቅ ጉዳዩን በተመለከተ የሚያማክር አካል አለመኖር እንዲሁም  የወላጅ እና የልጅ መስተጋብር ደካማ መሆን ችግሩን የከፋ እንደሚያደርገው ባለሙያው ይገልፃሉ። ስለሆነም ችግሩ እንዳይከሰት ከተከሰተም  ጉዳቱን ለመቀነስ በወላጆች በኩል መደረግ ያለባቸው ርምጃዎች መኖራቸውን ባለሙያው ያስረዳሉ። ከነዚህም መካከል ጥንቃቄ የመጀመሪያው ነው። ወላጆች በአጠቃቀም ላይ ከሚያደርጉት ቁጥጥር በተጨማሪ በልጆች የበይነመረብ እና የስማርት ስልኮች አጠቃቀም ላይ ገደብ ማድረግ ለጥንቃቄ አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል።ችግሩ ከተከሰተ  ደግሞ የህግ  ከለላ መኖሩን ማወቅ እና  ወደ ህግ አካላት ማመልከት ተገቢ መሆኑን ገልፀዋል። 

ወላጆች በአጠቃቀም ላይ ከሚያደርጉት ቁጥጥር በተጨማሪ በልጆች የበይነመረብ እና የስማርት ስልኮች አጠቃቀም ላይ ገደብ ማድረግ ለጥንቃቄ አስፈላጊ ነው።ምስል Antonio Guillen Fernández/PantherMedia/IMAGO

ከሳይበር ጉልበተኝነት ምርምር ማዕከል የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ደግሞ ተደጋጋሚ ትንኮሳ ሲያጋጥም መልዕክቱን «ስክሪን ሾት» በማድረግ ወይም ፎቶ በማንሳት መያዝ፣ አጥቂዎችን ሙሉ በሙሉ ማገድ፣ ለቴክኖሎጅ ኩባንያዎች ችግሩን ሪፖርት ማድረግ፣ የግላዊነት ቅንብሮችን መጠቀም ይመከራል። ይህንን ለማድረግ ግን በቅድሚያ ግንዛቤ ሊፈጠር እንደሚገባ አቶ ብሩክ ያስረዳሉ።  

በሌላ በኩል ልጆች ተንኳሽ እና ሌሎችን የሚያሸማቅቁ  መልዕክቶችን እንደሚወዱት ሲገልጹ እና ሲያጋሩ ወይም ምንም ነገር ሳያደርጉ ቢመለከቱ የችግሩ አካል ይሆናሉ እና፤ ልጆች የሳይበር ጉልበተኝነት እንቅስቃሴዎችን በጭራሽ እንዳያስተላልፉ፣ እንዳያጋሩ ወይም በቸልታ እንዳይቀበሉ ማስተማር ያስፈልጋል። ችግሩ ሲያጋጥም ወጣቶች አፀፋውን ለመመለስ  ስድቦቹን እና ተመሳሳይ የሆኑ ጸያፍ ፎቶዎችን በመለጠፍ፣ ወይም የበቀል ወሬዎችን በማሰራጨት ላይ እንዳያተኩሩ ወላጆች ማስተማር አለባቸው። ምክንያቱም ሁለት ስህተቶች ትክክለኛ አያደርጉም እና ጉዳዩ ወንጀል ከሆነ ሁለቱንም ልጆች ​​አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል። በሕግ እኩል ተጠያቂነትንም ያመጣል። 

 

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሀይ ጫኔ
ሽዋዬ ለገሠ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW