እያሽቆለቆለ ባለው የዓለም ቡና ገቢያ የበለጠ ማን ይጎዳል?
ቅዳሜ፣ የካቲት 28 2018
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ከትናንት በስቲያ ሓሙስ የካቲት 26 ቀን 2018 ዓ.ም. አዲስ አበባ ውስጥ የቡና ገበያ ሁኔታን በማስመልከት በሰጡት መግለጫ እያሽቆለቆለ በመጣው የዓለም የቡና ዋጋ የዘርፉ ተዋናዮች ሊደርስባቸው ከሚችል ከፍተኛ ኪሳራ ራሳቸውን እንዲከላከሉ አሳስበዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ ተከማችቶ የሚገኝ ቡና በወቅታዊው የዓለም ገበያ ዋጋ ሳይሸጥ መቆየቱ ኪሳራን ከማባባስ ባለፈ ለሀገር ሊያስገኝ የሚችለውን የውጭ ምንዛሬም የሚጎዳ በመሆኑ ተዋናዮች ሳይዘገዩ ምርታቸውን ወደ ማዕከላዊ ገበያ እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል።
ዶ/ር አዱኛ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ገለጻ በዓለም ገቢያው ላይ የቡና ዋጋ አቀናነስ አስደንጋጭ ያሉበትን ምክንያት ስያብራሩ፤ “ከሁለት ወራት በላይ ያጋጠመው የዓለማቀፍ የቡና ዋጋ ከአራት ዶላር ወደ 2.8 ዶላር ወርዷል” በማለት በተለይም ባለፈው አንድ ወር አናነሱ እጅግ አስጊና ለኢትዮጵያ ፈታኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ቡናን በስፋት ከሚያመርቱበት ከጅማ አጋሮ በቀጥታ ወደ አውሮፓ ኩባንያዎች የሚልኩት ሙስጠፋ አባገሮ በዘንድሮው የዓለም የቡና ገበያ መዋዠቅ እምብዛም አልተጨነቁም፡፡ ሙስጠፋ ዘንድሮ ያመረቱትን ቡና በሙሉ አስቀድመው ለያዙት ደንበኞቻቸው ለመላክ አሁን ላይ ምርቶቻቸውን በሙሉ ከጅማ ወደ አዲስ አበባ ማስገባታቸውንም ገልጸዋል፡፡
በዓለማቀፍ ገቢያ እያሽቆለቆለ ባለው የቡና ዋጋ አምርተው ለሚልኩት ሙስጠፋ እከስራለሁ የሚል ስጋት ባያሳድርም፤ ቡናን በመግዛት ለላኪዎች የሚያቀርቡ አቅራቢዎች ግን ከፍተኛ አደጋ ላይ ናቸው ይላሉ፡፡ ይሄም ገቢያው በእውቀት አለመመራቱና የነጋዴዎች በግዢው ላይ መሽቀዳደም የፈጠረው እንደሆነ ነው ያስረዱት፡፡
“እኛ እንከስራለን ብለን ባንጠብቅም፤ ነጋዴው ሊከስር ይችላል” የሚሉት የቡና አምራች እና ላኪው ያለ ገቢያ ጥናት ቡናን ከአርሶአደር ሰብስበው የገዙት አቅራቢ ነጋዴዎች “ባሁን ወቅት ጠያቂም የለውም” ያሉት ሰብስበው የያዙት ቡና ለኪሳራ ሊዳርጋቸው ይችላል፡፡
ዋጋው የሚዋዥቀው የዓለም ቡና ገቢያ
ቡና ሁሌም በዓለም ገቢያው የመውጣትና የመውረድ ሁኔታ አለው የሚሉት የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ግዛት ወርቁ ደግሞ አሁን ላይ ዋጋው እየቀነሰ ያለበት ሁኔታ ግን አስደንጋጭ ነው ይላሉ፡፡ አቶ ግዛት፤ “የወረደው አወራረድ በአራት ወር እንኳ በዶላር ወደ 67 ሳንቲም ነውና የቡና ላኪዎች ከባድ ፈተና ውስጥ ነው የገቡት” ብለዋል፡፡
ዘንሮ አቅራቢ የቡና ነጋዴዎች ቀይ እሸት ቡናን ከገበሬው የገዙበት ዋጋ ቀጣይ ሊመጣ የሚችለውን የዓለማቀፍ ዋጋ ከማስላት ይልቅ አምና ከፍ ብሎ የነበረውን የቡና ዋጋ ከግንዛቤ አስገብተው ነው የሚሉት አቶ ግት፤ ዋጋውን ሰቅለው የገዙት ነጋዴዎች አሁን በገቡበት ከፍተኛ ኪሳራ ለላኪዎች ለመሸጥ ተቸግረዋል፡፡
የዓለማቀፍ ቡና ዋጋ መልሶ የማንሰራራት እድል
ከዚህ የተነሳ አሁን ነጋዴው ብቻ ሳይሆኑ የቡና ላኪዎችም ጭምር ፈተና ገጥሞአቸዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ቡና አቅራቢ ነጋዴዎች የገዙበት ዋጋ ከፍተኛ ስለነበር አሁን ገዢ የላቸውም፡፡ ቡና ከአከባቢው ካልመጣ ደግሞ ላኪው ከየት አምጥቶ ቡና ሊልክ ይችላል? አቶ ግዛው “የሚገርመው ደግሞ አሁንም በዚሁም ዋጋ ቢሆን የሚከስሩትን ከስረው ካልሸጡ በወራት በቆዩ ቁጥር የባሰ ይከስራሉ” ይላሉ፡፡
የዓለማቀፍ ቡናዋጋ መልሶ የማንሰራራት እድል አይኖረውምን? የተባሉት የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚው የማይሆን ነው ይላሉ፡፡ “እኛ እንደ ኢትዮጵያ ቡና ማህበር እንደ የጀርመኑ ራቡ ባንክ እና ሌሎችም የቡናን ዋጋ የሚገምቱ ተቋማትን መረጃ ተንተርሰን ለአባሎቻችን ለማሳወቅ ሞክረናል” የሚሉት አቶ ግዛት፤ የዓለም የቡና ምርት ታይቶ በማይታወቅ መጠን የሚጨምር መሆኑና የብራዚል ምርት ከቀጣይ ግንቦት ወር ጀምሮ የሚደርስ መሆኑ አሁን ቡና ዋጋው ሊጨምር ችላል የሚለውን መላምት ዜሮ ያደርገዋልም ነው ያሉት፡፡
የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ተጽእኖ
በተቀዛቀዘው የቡና ዋጋ ላይ በመካከለኛው ምስራቅስ በርካታ አገራትን አሳትፎ የተቀጣጠለው ጦርነትስ የኢትዮጵያ ቡናን ለዓለም ገቢያ መላክ ላይ ሌላው ፈተና ይደቅን ይሆን? አቶ ግዛት ይሄ ለጊዜው እምብዛት ስጋት አይደለም ይላሉ፡፡ “በሱ ረገድ ዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ አንዱ ቡና ገዢያችን ስለሆነች ወደብ ላይ በቀላሉ መድረስ ስለማይቻል ያን ገቢያ የማጣት እድሉ ሰፊ ቢሆንም ሌላው ገቢያ ግን እስካሁን ክፍት ነው” ብለዋል፡፡
ይህ ጦርነት ቄ ባህል ቀጠናን እስካላጠቃ ድረስ ዓለማቀፉ የቡና ዋጋ ዳግም እንዲያንሰራራ በማድረግ የኢትዮጵያ የቡና ገቢያም በዚህ ውስጥ ተጠቃሚ ያደርጋል የሚል ግምትም እንደማይኖራቸው ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት 470 ሺህ ቶን የቡና ምርት ለዓለም ገቢያ በመላክ በታሪክ ከፍተኛ ነው የተባለውን የ2.65 ቢሊየን ዶላር ገቢ ከተላከው ቡና አግኝታለች፡፡
ዘንድሮስ ኢትዮጵያ አምና ያሳካችውን እንኳ ከቡና የወጪ ገቢያ ታሳካ ይሆን? የቡና ላኪዎች ማህበሩ ስራ አስፈጻሚ አቶ ግዛት ወርቁ ምንም እንኳን የቡና ዋጋ በአስደንጋጭ ሁኔታ ብወርድም መሆኑ አይቀርም ባይ ናቸው፡፡
“እኔ ይደረስበታል ብዬ ነው የባስበው” ያሉት ኃላፊው፤ እስካሁን እንኳ ሁለት ቢሊየን ዶላር ያህል የወጪ ንግድ ገቢ ያስገኘው ቡና በቀጣይ ቀሪ ወራት በሚሰራው ስራ ካለፈው ዓመት ያነሰ ገቢ ይገኛል የሚል እምነት የላቸውም፡፡ ይህ እንዲሆን ግን በቀጣይ ሶስት-አራት ወራት ቡና ከአቅራቢ እጅ ወጥቶ ወደ ላኪዎች እጅ መግባት ይኖርበታል፡፡
በኢትዮጵያ እስካሁን ወደ ውጭ ገቢያ መላክ የነበረበት እቅድ የተያዘለት የኢትዮጵያ ቡና ምርት ከ60 በመቶ እንደማይበልጥ የተናገሩት አቶ ግዛት በቀጣይ ቀሪውም ዋጋውን የበለጠ ሳያጣ በተቻለ ፍጥነት እንዲላክ ይመክራሉ፡፡
ሥዩም ጌቱ
እሸቴ በቀለ