1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እያነጋገረ ያለው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ረቂቅ ማሻሻያ አዋጅ

ሰለሞን ሙጬ
ሐሙስ፣ ኅዳር 12 2017

ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የቀረበው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ረቂቅ ማሻሻያ አዋጅ ውድቅ እንዲደረግ ተጠየቀ። የጋዜጠኞች የሙያ ማህበራት፣ የሰብአዊ መብትና የሲቪክ ድርጅቶች የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ የመገናኛ ብዙኃንን ነፃነት ክፉኛ ይጎዳል፤ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣንም በፖለቲካ ፓርቲ ተጽዕኖ ሥር እንዲወድቅ ያደርጋል ሲሉ ተቃዉመዉታል።

የዘገባ እቃዎች - የጋዜጠኛ መሳርያዎች
የዘገባ እቃዎች - የጋዜጠኛ መሳርያዎች ምስል Solomon Muchie/DW

እያነጋገረ ያለው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ረቂቅ ማሻሻያ አዋጅ

This browser does not support the audio element.

ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ረቂቅ ማሻሻያ አዋጅ የብዙኃን መገናኛ ዘርፍ ምህዳርን እንዳያጠብ ያሰጋል በሚል ማሻሻያው ውድቅ እንዲደረግ ተጠየቀ። በጉዳዩ ላይ ትናንት በተደረገ ሕዝባዊ ዉይይት የጋዜጠኞች የሙያ ማህበራት፣ የሰብአዊ መብት እና የሲቪክ ድርጅቶች የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ የመገናኛ ብዙኃንን ነፃነት ክፉኛ ይጎዳል፤ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣንም በፖለቲካ ፓርቲ ተጽዕኖ ሥር እንዲወድቅ ያደርጋል በሚል ተቃዉሞ አስምተዋል። 

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በበኩላቸው ማሻሻያው በመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ የሚስተዋሉ የሕግ ክፍተቶችን እና የሥነ ምግባር ጥሰቶችን ለማረምና የሕዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ ይረዳል በሚል ማስፈለጉን አስታዉቀዋል። 

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ትናንት ረቡእ ያዘጋጀዉ ሕዝባዊ ውይይት ላይ አዋጅ ቁጥር 1238/2013ን ማሻሻል ያስፈለገው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የዕለት ተዕለት ሥራውን እንዳያከናዉን ለተቋሙ ቦርድ የተሰጠው ሥልጣን የሕግ ክፍተት በመፍጠሩ እና ያንን ለተቋሙ ሥራ አስፈፃሚ መመለስ አስፈላጊ በመሆኑ እንደሆነ ተጠቅሷል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማሻሻያው የሕዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ የተሻለ የቁጥጥር ሥርዓት ለመዘርጋት ታስቦ ስለመዘጋጀቱ አስቀድሞ ገልጿል። ይህንን ማሻሻያ 14 የሙያ ማህበራት ጉዳዩ ይፋ ከሆነ በኃላ በጋራ ባወጡት መግለጫ ተቃውመውት የነበረ ሲሆን ትናንት በውይይቱ የተሳተፉ የዘርፉ ተዋናዮችም ይህ ጉዳይ በጥንቃቄ እንዲታይ ጠይቀዋል።

"ብዙ ችግር ካሳለፈ እና አሁንም ብዙ ችግር እያሳለፈ ካለ አገር ሚዲያው ኃላፊነት በተሞላበት መልኩ እንዲሠራ የሚያደርግ ጠንካራ የዴሞክራሲ ተቋም ሆኖ እንዲቀጥል ስለሚያስፈልግ ይህንን አዋጅ የማሻሻል ሀሳብ ቀርቶ ይልቅ ቦርዱ አሁን ባለው ስብጥር እንዲቀጥል የሚያስደርግ አሰራር ይኑር"..."ሕጉን የማሻሻሉ ሀሳብ፣ ሂደት እና ፍላጎቱ ሙሉ በሙሉ ፖለቲካዊ ጉዳይ ብቻ እንደሆነ ያሳያል" በአዲሱ የማሻሻያ ረቂቅ ላይ የፖለቲካ ፓርቲ አባል የሆኑ ሰዎች የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የቦርድ አባል መሆን አይችሉም በሚል ተደንግጎ የነበረው አንቀጽ መውጣቱ ነው ጉዳዩ ላይ ተቃውሞ ያስነሳው።

የአዋጁ ማሻሻያ አስፈላጊነት ላይ ገለልተኛ ጥናት አልተደረገም፣ በቂ የባለድርሻ አካላት ውይይት አልተካሔደበትም የሚለውም ሌላኛው መከራከርያ ነው። "ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በራሱ መሠረታዊ መብት መሆኑ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች መብቶችም መከበር ቁልፍ መሣሪያ ነው። ስለዚህ እዚህ መብት ላይ የሚደረግ ገደብ እና ዉሳኔ የሌሎች መብቶችንም የሚነካ ነው" በዉይይቱ ማሻሻያዉ ምናልባት የሚዲያ ምህዳሩን የማጥበብ፣ የዲሞክረሲ እና የሰብዓዊ መብት ነፃነቶችንም ችግር ላይ ሊጥል ይችላል የሚል ሀሳብ ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሥራ ኃላፊም ተነስቷል።

የዘገባ እቃ - የጋዜጠኛ መሳርያ ምስል Solomon Muchie/DW

"የዚህ ድንጋጌ መሠረዝ የሥራ አመራር ቦርዱ በፖለቲካ ፓርቲ አባላት ተፅእኖ ሥር እንዲወድቅ የሚያደርግ እና የቦርዱን ገለልተኛነት እና ነፃነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው" በነባሩ አዋጅ ለኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ቦርድ ተሰጥተው የነበሩት የፈቃድ ወይም የምዝገባ ምስክር ወረቀት አለማደስ፣ ማገድ፣ መሰረዝ፣ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ መስጠትን የመሳሰሉት ኃላፊነቶች አሁን ለባለሥልጣኑ ሥራ አስፈፃሚ መሰጠታቸው ሥልጣንን ጠቅልሎ ለአንድ አካል ከመስጠትና በሒደትም ላልተገባ ተፅዕኖ በር ከመክፈቱ በተጨማሪ "የባለሥልጣኑን ገለልተኝነትና ነፃነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ" ነው የሚለው አንዱ መከራከሪያ ነው።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ እድሪስ ሲመልሱ ግን ተቋማቸው በአዋጁ ምክንያት ለመወሰን እና ሥራውን በአግባቡ ለመከውን ተቸግሯል።

"ከቦርዱ [የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን] በታች ፈፃሚ ተብሎ አንድ አካል ከተቋቋመ በኋላ ለመወሰን የሚያስችሉ ጉዳዮችን ዕለት ዕለት ጉዳዮችን አንተ አትወስንም ከተዮለያዩ አካላት የመጡት አካላት ነው የሚሰጡት የሚል ነው"  የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሰጠው አስተያየት አዋጁ የሕዝብ እና የሀገር ጥቅም እንዲከበር ከማድረግ የዘለለ ሌላ አላማ የለውም። ይህ ረቂቅ የማሻሻያ አዋጅ በቀጣይ ለምክር ቤቱ ቀርቦ ዉይይት ይደረግበታል።

ሰለሞን ሙጬ 

አዜብ ታደሰ 

ታምራት ዲንሳ 
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW