1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሙዚቃ

እያንሰራራ ያለው የ«ሪሚክስ» ባህል

እሑድ፣ ሚያዝያ 7 2010

አዲስም ሆነ ቆየት ያሉ ዘፈኖችን በተለየ ስልት አሊያም አቀራረብ መልሶ ማቀናበር (ሪሚክስ) በውጪው ዓለም የተለመደ ነው፡፡በኢትዮጵያም ይህ አካሄድ እየተዘወተረ መጥቶ በዚህ መልክ የተቀናበሩ የዘፈን ስብስቦች በአልበም ተሰባስበው እስከመውጣት የደረሰቡት ወቅት ነበር፡፡ ቀዝቀዞ የነበረው ይህ አካሄድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መነቃቃት አየታየበት ይመስላል፡፡

Symbolbild Tanzen Club Pop Musik Disko Plattenteller Turntables ausgehen
ምስል Fotolia/Valery Sibrikov

እያንሰራራ ያለው የ«ሪሚክስ» ባህል

This browser does not support the audio element.

በኢትዮጵያ ከሪሚክስ ጋር ስሙ ተደጋግሞ የሚነሳው ዲጄ መንጌ ነው፡፡ ተቀማጭነቱን በኒውዮርክ አሜሪካ ያደረገው ዴጄ መንጌ “ማሲንቆ” በሚል ስያሜ ተከታታይ አልበሞችን አስደምጧል፡፡ ዴጄ መንጌ በእነዚህ አልበሞቹ ቀደም ሲል የሚታወቁ ዘፈኖችን ፈጠን ባለ ስልት መልሶ አቀናብሮ ለአድማጭ ጆሮ ደርሷል፡፡ የእርሱን ፈለግ የተከተሉ ሌሎች ዴጂዎችም በየጊዜው ተመሳሳይ ሙከራዎች ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ዲጂ ዊሽ በተሰኘ የመድረክ ስሙ ይበልጥ የሚታወቀው ምኞትም ኃይሉ ከእነዚህ ውስጥ ይመደባል፡፡ ዲጄ ዊሽ መልሶ ካቀናበራቸው ዜማዎች ውስጥ ይበልጥ ተደማጭ የነበረው “አላምን አለና” የተሰኘው የቴዲ አፍሮ ዜማ ነው፡፡ ዘፈኖችን  መልሶ ማቀናበር (ሪሚክስ) ስላለው ጥቅም ይናገራል፡፡

ምስል dpa/picture-alliance

ህዝብ ዘንድ የደረሱ ሙዚቃዎችን መልሰው በተለየ ስልት የሚያቀናብሩ ዴጄዎች የተለያዩ መንገዶችን ይከተላሉ፡፡ አንዳንዶች የአቀንቃኙን ድምጽ ብቻ (አካፔላ) ነጥለው ወስደው ራሳቸው በሚፈልጉት ስልት ቀይረው እንደገና ይሰሩታል፡፡ ሌሎች ደግሞ አዲስ ሙዚቃ ሳይሰሩ ከሌሎች ዘፋኞች ስራ ጋር ቀይጠው መልሰው ያቀናብሩታል፡፡ ዴጂ ዊሽ የሁለቱን አሰራሮች ልዩነት በምሳሌ አስደግፎ ያብራራል፡፡    

ከአቀንቃኙ ወይም ከሙዚቃው ባለቤት ጋር ይፋዊ ግንኙነት ፈጥረው ሙዚቃዎችን በድጋሚ የሚያቀናብሩ ዲጄዎች እንዳሉ ሁሉ ደስ ያላቸውን ዘፈን ያለፍቃድ ወስደው በሚመቻቸው መልክ የሚያበጃጁም ሞልተዋል፡፡ ጥራቱን የጠበቀ፣ ፈጠራ የታከለበት እና ጥንቅቅ ያለ ስራ ለመስራት ከተፈለገ ከዘፋኙ ጋር ተነጋግሮ እና ይፋዊ አካሄድን ተከትሎ ማድረጉ እንደሚያወጣ የሙዚቃ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡ ዲጄ ዊሽም ይህን አመለካከት ይጋራል፡፡ 

ዲጄ ዊሽ በምሳሌነት ያነሳው ሳሚ ዳን “ኃይል” የተሰኘው ዘፈኑ ብቻ አይደለም ይፋዊ መልሶ የመቀናበር ዕድል የገጠመው፡፡ በግንቦት 2008 ዓ.ም ከተለቀቀው “ከራስ ጋር ንግግር” ከተሰኘው አልበሙ ውስጥ ሁለቱ ከእርሱ ፍቃድ ተሰጥቷቸው “ሪሚክስ” ተደርገዋል፡፡ “ጠፋ የሚለየን” የተሰኘውን ዘፈኑን “ቦሌ ቦሌ” በሚለው ቅንብር የሚታወቀው “ቲኬ ስኖ” በ“ትሮፒካል ሀውስ” የሙዚቃ ስልት መልሶ አቀናብሮታል፡፡ በኢትዮጵያ ዘፈኖችን “በኤሌክትሮኒክስ ዳንስ ሙዚቃ” ስልት ሪሚክስ በማድረግ ስማቸው ከሚጠሩ ወጣቶች መካከል አንዱ የሆነው ዲጂ ሮፊ ደግሞ “ሆያ ሆዬ” የተሰኘውን የሳሚ ዳንን ዘፈን እንደገና ሰርቶታል፡፡  እነዚህ ሙዚቃዎች ከባለሙያዎች ጋር በመተባበር እንደተሰሩ ሳሚ ዳን ያስረዳል፡፡ በይፋዊ ዕውቅና የተሰሩትን ይፋዊ ካልሆኑት ጋር በማነጻጸር ያብራራል፡፡   

ምስል Fotolia/U.P.images

ለአንድ አቀንቃኝ ዘፈኖቹ መልሰው የመቀናበራቸው ጥቅሙ ምንድነው? ሳሚ ዳን ምላሽ አለው፡፡ የሪሚክስ ጥቅሞች ቢዘርዘሩም የተወሰኑ የሙዚቃ አፍቃሪያን ግን ዘፈኖችን መልሶ የማቀናበር ሀሳብ አይዋጥላቸውም፡፡ በተለይ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ወርቃማ ዘመን በሚባለው በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ የተሰሩ ሙዚቃዎች እንደገና ባይነኩ ይመርጣሉ፡፡ የዚያን ዘመን ሙዚቃዎችን መልሶ መስራት “እንደማበላሸት” ይቆጠሩታል፡፡ ዲጂ ዊሽ የእዚህ ሀሳብ አራማጆችን መከራከሪያ ይረዳል፡፡ እርሱም ቢሆን ሪሚክስ ለማድረግ የቅርቦቹን እንጂ “የድሮዎቹን ሙዚቃዎች በጣም ስለምወዳቸው አልደፍራቸውም” ይላል፡፡ 

በኢትዮጵያ ሪሚክስ የሚደረጉ ዘፈኖች እየጨመሩ መምጣታቸውን የታዘበው ዲጄ ዊሽ ከዚህ በኋላ ቁጥሩ ይበልጥ ይመነደጋል ብሎ ተስፋ ያደርጋል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ወጣት የሙያ አጋሮቹ እንደሆኑ ያስረዳል፡፡  ለእነዚህ ወጣት ዲጄዎች እንደ እነ ሳሚ ዳን ያሉ የዕድሜ እኩያዎቻቸው የተመቻቸ ነገር እየፈጠሩላቸው ይመስላል፡፡ ሁለተኛ አልበሙን ሰርቶ መጨረሱን የሚናገረው ሳሚ ዳን ለሪሚክስ ይሆናሉ ብሎ የሚያስባቸውን ዘፈኖች በድምጽ ብቻ (አካፔላ)በኦንላይን ለመልቀቅ እቅድ እንዳለው ገልጿል፡፡ መልሶ ማቀናበር የሚፈልግ ሰው ያንን ወስዶ መጠቀም ይችላል ይላል፡፡ 

ተስፋለም ወልደየስ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW