1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ2 ዓመት ህጻን በአጋቶች ተገድላለች

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 28 2016

ትናንት እገታንና ግድያን በመቃወም በብስጭት ሰላማዊ ሰልፍ የወጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ከመንግስት የፀጥታ ኃይል ጋር ተጋጭተው የሞቱና የቆሰሉ ሰዎች መኖራቸውን አስረድተዋል፡፡ በነበረው አለመግባባት የፀጥታ ኃይሉ በወሰደው እርምጃ 4 ሰዎች መገደላቸውንና ሌሎች መቁሰላቸውን ማረጋገጣቸውን አመልክተዋል፡፡

ጎንደር ከተማ ዉስጥ አንዲት ሕፃን ታግታ መገደሏ ተቃዉሞ ሰልፍ ቀስቅሷል
የጎንደር ከተማ በተደረገ የተቃዉሞ ሰልፍ ቢያንስ 4 ሰዎች ተገደሉምስል Alemnew Mekonnen/DW

የ2 ዓመት ህጻን በአጋቶች ተገድላለች

This browser does not support the audio element.

በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች እየተፈፀመ ያለው እገታና ግድያእንዳማረራቸው ነዋሪዎች እየተናገሩ ነው። ትናንት የአንዲት ህፃንን ታግታ መገደል ተከትሎ በጎንደር ከተማ  በተካሄደ ሰላማዊ ሰልፍ የሰው ህይወት መትጥፋቱን አስተያየት ሰጪዎች አመልክተዋል፡፡
በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች እገታዎች ይፈፀማሉ፣ ለማስለቀቅ ደግሞ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ይጠየቃል፣ አንዳንድ አጋቾች ገንዘብ ከተቀበሉ በኋላ ሳይቀር ግድያ ይፈፅማሉ፡፡
ነሐሴ 24/2016 ዓ ም በጎንደር ከተማ የተደረገውም ይኽው ነው፡፡ ህፃን ኖላዊት ዘገየ የእናቷን ጡት ጠብታ ያልጠገበች የ2 ዓመት ህፃን ነበረች በአሳዛኝና ባልታሰበ ሁኔታ አጋቾች እጅ ገባች፡፡
የሟች የቅርብ ዘመድ ሁኔታውን በተመለከተ ለዶቼ እንዳስረዱት አጋቾች የእናትና የአባት ወደ ስራ መሄድን መነሻ በማድረግ ከአያቷ ጋር የነበረችን ህፃን ነሐሴ 24/2016 ዓ ም ጠዋት ሶስት ሰዓት ከሰረቁ በኋላ “አግተናታል ማስለቀቂያ አንድ ሚሊዮን ብር አምጡ” የሚል ፅሁፍ ግቢ ውስጥ ጥለው ሄደዋል ይላሉ፡፡
እኚህ የቅርብ ዘመድ በዝርዝር እንዳስረዱን አጋቾች የጠየቁትን ገንዘብ ከተቀበሉ በኋላ ግን የህፃነዋን አስከሬን ግምብ አጥር ላይ አስተኝተው ተሰውረዋል፡፡
ገንዘብ ከዘመድ አዝማድ ተሰብስቦ 200ሺህ ብር ከተገኘ በኋላ ከአጋጮች ጋር በተደረገ ድርድር 300ሺህ ብር ስምምነት ከተደረሰ በኋላ ተጨማሪ ብር ማግኘት ባለመቻሉ “ያላችሁን አምጡ በማለታቸው 200ሺህ ብር ከወሰዱ በኋላ የህፃኗን አስከሬን  ግምብ አጥር ላይ አስተኘተው ሄደዋል ብለዋል፡፡
አስተያየት ሰጪው በጎንደር ያለው እገታና ግድያ አይን ያወጣና ከልካይ የሌለው ወንጀል ሆኗል ነው ያሉት፡፡
ካህናት ከቤተመቅደስ ታግቶ ተወስዷል፣ እናትና ልጅና በወቅቱ ቆስላ የነበረች ሰራተኛ በአጋቾች ተገድለዋል ሲሉ ያለውን ሰቆቃ አስረድተዋል፡፡
ሌላ የጎንደር ከተማ ነዋሪ በበኩላቸው ከጥቂት ቀናት በፊት ከእገታ ጋር በተያያዘ አናት ልጅ ህይወታቸው ማለፉን ገልጠዋል፣ በእገታው ወቅት ሟች እናት ከመሞታቸው በፊት አንደኛውን አጋች ተኩሰው ሲገድሉ ሌላውን አቁስለዋል፣ ሆኖም በተኩስ ልውውጡ ልጅና እናት ህይወታቸው ማለፉን አስረድቷል፡፡
የህፃን ኖላዊት ቅርብ ዘመድ ለዶቼ ቬሌ እንደገለፁት ትናንት እገታንና ግድያን በመቃወም በብስጭት ሰላማዊ ሰልፍ የወጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ከመንግስት የፀጥታ ኃይል ጋር ተጋጭተው የሞቱና የቆሰሉ ሰዎች መኖራቸውን አስረድተዋል፡፡ በነበረው አለመግባባት የፀጥታ ኃይሉ በወሰደው እርምጃ 4 ሰዎች መገደላቸውንና ሌሎች መቁሰላቸውን ማረጋገጣቸውን አመልክተዋል፡፡
ሌለው አስተያየት ሰጪም በበኩላቸው በትናንትናው ሰልፍ 4 ሰዎች ተተኩሶ ሲገደሉ በዓይናቸው ማየታቸውን ለዶይቼ ቬሌ አገልጠዋል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ አስተያየት ለማካተት ለክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊና ለጎንደር ተማ አስተዳደር  የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ ያደረግነው የስልክ ጥሪ አልተሳካም፡፡
በአማራ ክልል በየጊዜውና በየቦታው የሚደረገው እገታና ግድያ የክልሉን ነዋሪዎች ኑሮ ፋታ የነሳ መሆኑን ብዙዎች በተስፋ መቁረጥ ስሜት ይገልፃሉ። አንዳንዶቹ ከሚኖሩባቸው አካባቢዎች ሳይቀር  እየለቀቁ ወደ ሌሎች ከተሞች እየሄዱ እንደሆነም በስፋት ይነገራል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW