1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማስለቀቂያ ገንዘብ ህይወቱን ያልታደገው ታጋች - በከሚሴ

ቅዳሜ፣ ሰኔ 8 2016

“አጋቾቹ ፍላጎታቸው ምንድን ነው? ብለን ታጋቹ ልጀን ስንጠይቅ፣ ማስለቀቂያ 2 ሚሊዮን ብር እንፈልጋለን ብለዋል አለን፣ ተከራክረን፣ ተከራክረን በ500ሺህ ብር ተስማማን፣ አምቢ ካልክ ልጁን እንገለዋለን ብለው ዛቱ፣ አስፈራሩኝ፣ ልጄን ከምታጠፉ፣ ከምትገድሉ ብዬ 500ሺህ ብሩን አስገባሁላቸው፡፡” የታጋች አባት

ከሚሴ
ከሚሴምስል Seyoum Getu/DW

ታጋቹ ተገደለ

This browser does not support the audio element.

ባለፈው እሁድ ምሽት በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ከሚሴ ከተማ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች አንድ ወጣትን አግተው የማስለቀቂያ ገንዘብ ጠይቀው እንደነበርና አጠቃላይ ሂደቱን  የሟች አባትና የወሎ “አባ ቡኩ” እንደሆኑ የነገሩን አቶ አደም መሐመድ  ተናግረዋል፡፡
“እሁድ ማታ ልጁ ሳይገባ ሲቀር ነው ችግሩን ያወቅሁት፣ ከዚያ በኋላ ስንፈልግ አደርን፣ ፖሊስ ጣቢያም ሄድን ነገሩ አዲስ ሆኖብን እንዴት እናድርግ በሚል ግራ ተጋባን፣ ልጁ ሰኞ ጠዋት ደውሎ በማላውቃቸው ሰዎች ተይዣለሁ አለን፡፡”
አጋቾቹ ስንት እንደሆኑ እንደማያውቁ የተናገሩት አቶ አደም፣ አማርኛም ኦሮምኛም ሲናገሩ የማስለቀቂያ ገንዘብ በጠየቁበት ወቅት መስማታቸውን  ገልፀዋል፤ ለማስለቀቂያ  መጀመሪያ 2 ሚሊዮን ብር መጠየቃቸውንና በኋላ በ500ሺህ ብር መስማማታቸውን አባት ነግረውናል፡፡
“አጋቾቹ ፍላጎታቸው ምንድን ነው? ብለን ታጋቹ ልጀን ስንጠይቅ፣ ማስለቀቂያ 2 ሚሊዮን ብር እንፈልጋለን ብለዋል አለን፣ ተከራክረን፣ ተከራክረን በ500ሺህ ብር ተስማማን፣ አምቢ ካልክ ልጁን እንገለዋለን ብለው ዛቱ፣ አስፈራሩኝ፣ ልጄን ከምታጠፉ፣ ከምትገድሉ ብዬ 500ሺህ ብሩን አስገባሁላቸው፡፡” ሲሉ ሀዘን በተጫጫነው ስሜት አባት ገልፀውልናል፡፡
አጋቾቹ የተስማሙበትን ገንዘብ ከወሰዱ በኋላ ግን ልጃቸውን ባለፈው ረቡዕ ተገድሎ ትናንት አስከሬኑ ከከሚሴ 7 ኪሎሜትር ርቀት ላይ መገኘቱን  ነው አቶ አደም የተናገሩት፡፡
“ ገንዘቡን ከተቀበሉ በኋላ ስልካቸውን ዘጉብኝ፣ እስከዛሬ ልጄ ይመጣል ብየ በር በሩን ሳይ ነበር፣ እንቅልፍም አልተኛ፣ ረቡዕ ማታ እንደገደሉት አወቅን፣ ትናንት አስከሬኑን ከሚሴ አቅራቢያ “ቂሌ” ከምትባል አካባቢ 7 ኪሎሜትር ከከሚሴ እዛ ላይ አስከሬኑን ጥለውት ትናንት አገኘነው፡፡”
ባለሶስት እግር ተሸከርካሪ (ባጃጅ) አሽከርካሪ የነበረውና በ30ዎቹ  የእድሜ ክልል ላይ የነበረው ወጣት የአንድ ልጅ አባት እንደነበረና ህይወትን ለማሻሻል ቀደም ሲል ወደ ሳዑዲ አረቢያ ሄዶ እንደነበረም አባት ያስረዳሉ። አጋቾች ወጣቱን የወሰዱት በኮንትራት ክፍያ ከሆነ ቦታ አድርሰን በሚል ማታለያ እንደነበረም አቶ አደም ይገልፃሉ፡፡
“ልጄ የባጃጅ ሾፌር ነበር፣ ኮንትራት ብለው ነው የወሰዱት፣ አንድ ልጅ አለው፣ በመሐል...ሳዑዲ አረቢያም ለስራ ሄዶ ነበር፡፡”
ጉዳዩን አስመልክተን ተጨማሪ መረጃ ለማካተት ለብሔረሰብ አስተዳደሩ ዋና አስተዳዳሪ በአቶ አህመድ አሊ የእጅ ስልክ ላይ ብንደውልም፣ አጭር የፅሁፍ መልዕክት ብንልክም ምላሽ አላገኘንም፤ በተመሳሳይ የብሔረሰብ አስተዳደሩ ሰላምና ፀጥታ ዘርፍ መምሪያ ኃላፊ ለአቶ አሊ ሞሐመድ ደውለን “ጥቂት ቆይተህ ደውል” ካሉ በኋላ መልሰን ብንደውልም፣ አጭር የጽሁፍ መልዕክት ብንልክም ምላሽ ማግኘት አልቻልንም፡፡
ዓለምነው መኮንን
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW