እግርን ለሚያሳብጠው ህመም የጀርመናዊቱ ነርስ መፍትሄ
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 5 2014
ኦፋን ኦሮሞን በደንብ አማርኛን ደግሞ በመጠኑ ይናገራሉ። ክርስትል አነርስ ከወንጌላዊነታቸው ሌላ ነርስ እና አዋላጅ ሀኪም ናቸው። ጀርመናዊቱ የማኅበረሰብ ጤና ባለሙያ ኢትዮጵያ ውስጥ ለ34 ዓመታት በመኖር በጤናው ዘርፍ ያበረከቱት አስተዋጽኦ በተለይ በቂ የህክምና አገልግሎት ለማያገኘው በገጠር ለሚኖረው ወገን ትርጉም ያለው ነው።
ከሰሜኑ የጀርመን ግዛት አካባቢ እንደተገኙ የሚናገሩት ክርስትል አነርስ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የሄዱት በጎርጎሪዮሳዊው 1988 ዓ,ም እንደነበር ይናገራሉ። በማኅበረሰብ ጤና ዘርፍ የተማሩት አነርስ ለረዥም ዘመን አገልግሎት አንደኛቸውን ከመሄዳቸው አስቀድመው በዚሁ የዘመን አቆጣጠር በ1981 ዓም ወደ ኢትዮጵያ የመጓዝ ዕድል እንደነበራቸው አጫውተውኛል። ነርስ እና አዋላጅ ሃኪም የሆኑት አህነር በሙያቸው በተለይ በገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍል በርካቶችን የመርዳት አጋጣሚውን አግኝተዋል። ባለፉት 12 ዓመታት ደግሞ በተለይ በባዶ እግራቸው የሚሄዱ ሰዎችን የሚያጠቃውን ዝሆኔ የሚባለው ሳይሆን እሱን መሰል የእግር ህመም ለመከላከል የሚያስችል አስተዋጽኦ በማበርከት ሠርተዋል። ክርስትል አነርስ እንደሚሉት በህክምናው ፖዶኮሊዮሲስ በመባል የሚታወቀው ይኽ እግርን የሚሳብጠው ህመም በተለይ ከመሬት ወለል በጣም ከፍ ባሉት የኢትዮጵያ አካባቢዎች በብዛት የሚከሰትና የተንሰራፋ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የህክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ ሳሉ ያስተዋሉት ሁሉም ህመም የግድ መድኃኒት በመዋጥ ሊድን እንደማይችል ነው ይላሉ።
«አዎ እኔ በተጓዝኩበት የህክምና ሂደት ያስተዋልኩትን ልንገርሽ፤ በምሠራበት የህክምናው ዘርፍ ከጥቂት ዓመታት በኋላ በዘመናዊው መንገድ ማለትም እኛ ምዕራባውያን ባመጣነው መድኃኒት በመውሰድ ሰዎች ከተለያዩ በሽታዎች ሊድኑ እንዳልቻሉ ተገነዘብኩ። በዚያም ላይ የህክምናው ዘርፍ በወጉ ያልደረሰባቸው በህዝቡ ውስጥ የተንሰራፉ የህመም አይነቶች መኖራቸውንም ተረዳሁ። ከእነዚህ አንዱ ለምሳሌ እንቅርት ነው፤ ሌላው የእግር ማበጥም እንዲሁ በብዛት ሰዎችን የሚያጠቃ ነው።»
ከበርካታ ዓመታት ቆይታ በኋላም የህክምናው አገልግሎት በተስፋፋባቸው ሃገራት ችግር ሆነው ለማይታወቁት እንዲህ ላሉት በሽታዎችን ትኩረት ለመስጠት ወሰኑ። እሳቸው እንደሚሉት ኢትዮጵያ ውስጥ በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች ጤና ላይ ተጽዕኖ ያሳደሩት ሁለቱ የጤና እክሎች በቀላሉ መታከም እና መዳን ይችላሉ። ለእንቅርትም ሆነ እግርን ለሚያሳብጠው በህክምናው ፖዶኮሊዮሲስ በመባል ለሚታወቀው ህመም ሕንድ ውስጥ ከሚገኙ የካቶሊክ ነርስ የመፍትሄ ሃሳብ አገኙ። ለዚህም ከሁሉ አስቀድሞ ወደ ስፍራው በመሄድ የአብዛኞቹ ድሆች መሠረታዊ ችግር ምንድነው? የሚለውን አጣርቶ ማወቅ ተገቢ መሆኑንም ተረዱ።
«እነዚህን ደረጃዎች ነው የተከተልኩት። ለእንቅርቱ ችግር የአዮዲን እጥረት ላይ ሳተኩር እንደውም ያበጠው እግር ሁሉ የሚድንበትን አጋጣሚ አስተዋልኩ። በህክምናው መጽሐፍት ውስጥ ለዚህ የጤና ችግር ግልጽ መፍትሄ እንኳን የለም። እንደውም በአነስተኛ ተሐዋሲ ከሚመጣ በሽታ ጋር አያይዞ ነው የሚገለጸው። እንደውም እኔም በዚሁ መመሪያ መሠረት የማይሆን ህክምና አደርግ ነበር። ህክምናው መፍትሄ ስላልሰጣቸውም ታማሚዎቹ ተመልሰው የማይመጡበት አጋጣሚ ሁሉ ነበር። ሆኖም ግን ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወደ ምዕራብ አካባቢ ሄጄ ያገኘኋቸው ነርሶች ታማሚዎቹን ረድተው ማዳን መቻላቸውን ስመለከት ማመን አልቻልኩም። እንደውም እንዴት ነው ሌሎች ሀኪሞች ይኽን ማድረግ ያልቻሉት ስል ጠየኩ።»
በዚህ ጊዜም ክርስቲል አነርስ ከአንድ ውሳኔ ላይ ደረሱ። ከተለመደው የህክምና ስልት ወጣ ብለው ታማሚዎቹ ወደሚገኙበት አካባቢ በመሄድ በዚያው አስፈላጊውን የህክምና አገልግሎት መስጠት። እሳቸው እንደሚሉት እነዚህ ታማሚዎች ያለምንም መድኃኒት ከእግራቸው እብጠት ይድናሉ።
«ይኽ በሽታ ያለመድኃኒት ታክሞ ሊድን ይችላል። ለዚህም ነው የህክምና ሰዎች እጅግም ያላተኮሩበት። ለእኔ ደግሞ በጣም ተስማማኝ። እኔ አቅም የሌላቸውን ሰዎች ወደ አካባቢያቸው በመሄድ ማገልገል እፈልጋለሁ፤ በዝቅተኛ ወጪ ለውጥ ማምጣት ይፈልጋል ይኽ በሽታ እኛም በዚህ መልኩ ነው የምናክማቸው። በዚህም ደግሞ በጣም ደስተኛ ነኝ።»
የህክምና አገልግሎቱም ሆነ የመድኃኒት አቅርቦት እንደልብ በማይገኝበት ስፍራ በቀላል መንገድ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን እግርን ከሚያሳብጠው የጤና ችግር መታደግ ተችሏል። ኅብረተሰቡም በሚሰጡት የህክምና አገልግሎት እምነት አሳድሯል። በፖዶኮሊዮሲስ በሚባለው እግር የሚያሳብጥ የጤና ችግር የተጠቁን ለመርዳትም መዳን የቻሉትን ሰዎች ተጠቅመው በማኅበረሰቡ ውስጥ ግንዛቤ እንዲኖር እንደሚሠሩም ነው አነርስ የገለጹልን። ለህክምናው የሚያስፈልገው ምን ይኾን?
«ለህክምናው የሚያስፈልጉንን ሁሉ የምንሠራው ራሳችን ነን። መድኃኒትነት ያለው ሳሙና፣ መድኃኒትነት ያለው ቅባት እንዲሁም ጫማ እራሳችን እዚያው በሀገር ውስጥ እናመርታለን። ለማጓጓዝ ታዲያ በጣም ትንሽ ወጪ ነው። ይኽ ደግሞ የአካባቢውን ማኅበረሰብ የሚያጠናክርና ራሱን እንዲችል የሚያደርግ ነው። የግል ገቢ ማግኘት ደግሞ በጣም የሚፈለግ ነገር ነው። የማምረቻ ወጪያችንም ከፍ ያለ አይደለም።»
እንዲህ በቀላሉ ብዙዎችን መርዳት የሚቻል ከሆነ የህክምናው ዘርፍ ብዙም መድኃኒት አያስፈልገውም በተባለው በዚህ እግርን የሚያሳብጥ የጤና ችግር ላይ ማተኮር ለምን ተሳነው የሚለው ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። ክርስቲል አነርስ እንዲህ ነው የሚሉት።
«ቀዳሚው በመጽሐፍት ባለሙጣቱ ይመስለኛል። በሽታው ከመቶ ዓመታት በፊትም የታወቀ ነው። ግን ዘመናዊው መድኃኒት እና ረቂቅ ተሐዋስያን የሚባለው ነገር መጣ እናም ሁሉም በሽታ በአንቲባዮቲክ እና በመሳሰሉት መድኃኒቶች መታከም ጀመረ። ይኽ ደግሞ ትልቅ ለውጥ ነው። በዚህ የማይታከሙ ሌሎች በሽታዎች ወደጎን ችላ ተባሉ። ይኽ ነው አንዱ፤ ብዙ ሰዎች ስለዚህ በሽታ አያውቁም። እኔም አላውቅም ነበር። አሁን ይኽ ተቀይሯል፤ ትልቅ ለውጥ ነው። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ ባለሙያዎች በግንባር ቀደምትነት ይገኙበታል። ፕራይስ የሚባል ሰው በ70ዎቹ እና 80ዎቹ ኢትዮጵያ ውስጥ ነበር። ስለዚህ በሽታ በስፋት ጥናት አካሂዷል። ፖዶኮሊዮሲስ የሚለውን ስም የሰጠው እሱ ነው። በሽታውን ለመከላከል የግል ንጽሕናን መጠበቅ እና ጫማ እንደሚያስፈልግም ገልጿል። ግን በፖለቲካው መስመር ከፍ ወዳሉት አልደረሰም።»
ከብሪታንያ በጎርጎሪዮሳዊው 2000ዓ,ም ወደኢትዮጵያ በመምጣት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ሳይንስ ያስተምሩ የነበሩት ዶክተር ጌ ጌቢ እንዳጋጣሚ ሆኑ ይኽን ጥናት የመመልከት ዕድል ማግኘታቸውን እና ይኽ በሽታ መኖሩን ሲረዱ መደነቃቸውንም አክለው ገልጸውልናል። እናም በእርሳቸው ግፊት በዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት አማካኝነት በርካታ ምርምሮች መሠራት ቻለም ነው የሚሉት።
«ይኽ ደግሞ በጣም አስገራሚ ነው፤ ምክንያቱም ይኽ የቆየ በሽታ አሁን ታውቋል፤ ኢትዮጵያ ደግሞ በበሽታው ከተጎዱት ቀዳሚዋ ሀገር ናት፤ በዚያም ላይ የበሽታው መፍትሄም የሚገኘው እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። እኛም በብዙ አካባቢዎች ይኽን በሽታ መከላከል እንደሚቻል እንዲሁም በተወሰነ መጠንም እንደሚድን አሳይተናል።»
በአሁኑ ጊዜም አንዳንድ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በሽታውን ለመከላከል ተመሳሳይ አገልግሎትን በተለያዩ አካባቢዎች እየሰጡ እንደሆነም ነው የገለጹት። በዚህም ላይ ለ10 ዓመታት ገደማ ልዩ ልዩ ጥናት እና ምርምሮች ከተካሄዱ በኋላ መንግሥትም ለበሽታው እውቅና ሰጥቶ አስፈላጊ የመከላከያ ርምጃዎችን ሥራ ላይ እያዋለ መሆኑን እና ለሕዝቡም እንዴት መከላከል እንደሚቻል እያሳወቀ እንደሆነ አመልክተዋል። በሽታውን ለመከላከል የሚያስችሉ መረጃዎችን ለማግኘትም ሌሎች ሃገራት ወደ ኢትዮጵያ እየተመለከቱ ነውም ይላሉ።
ይኽ እግር የሚያሳብጠው የጤና ችግር በረቂቅ ተሐዋሲያን የሚመጣ አይደለም ነው የሚሉት ክርስቲል አነርስ። መነሻው ሌላ ነው።
«የሚመጣው በማዕድኖች ምክንያት ነው። እንደ ሲልኬት፤ ብረት እና ማግኒዚየም የመሳሰሉት ማዕድኖች እሳተ ጎሞራ በሚከሰትበት አፈር ውስጥ በብዛት ይገኛሉ። ኢትዮጵያ ደግሞ በርካታ ቀይ የእሳተ ጎሞራ አፈር አላት። በዚያም ላይ ኢትዮጵያ ብዙ ዝናብ እና ሙቀትም ያለባት ሀገር ናት። እነዚህ ማዕድኖች ደግሞ በጣም ረቂቅ ሲሆኑ ለዚህ የሚጋለጡት ባዶ እግራቸውን የሚሄዱ ሰዎች ናቸው። ምክንያቱም ጫማ ለመግዣ ገንዘብ የላቸውም። በዚያ ላይ ደግሞ ብዙዎች አዘውትሮ እግራቸውን በሳሙና የመታጠብ ልማድ የላቸውም። ሦስተኛው ደግሞ ወደደቡብ ኢትዮጵያ ስትሄጂ በዘረመል ምክንያት ለዚህ መጋለጥ አለ። »
ከዘረመል ጋር የተገናኘውን በተመለከተ ብዙዎች ስለማይረዱት እንደውም አንዳንዶች እንዲህ ካሉ ቤተሰቦች ጋር በጋብቻ መተሳሰር እንደማይፈልጉ በመረዳታቸውም ስለዚህ ጉዳይ ብዙም ከማኅበረሰቡ ጋር እንደማይነጋገሩበትም ነው ያመለከቱት። ይኽ የእግር እብጠት ህመም በብዛት ተንሰራፍቶ የሚገኝባቸውን የኢትዮጵያን ክፍሎች የሚሳይ ካርታ መሠራቱን የሚናገሩት ክርስቲል አህነር በተለይ በወላይታ ሶዶና አካባቢው፣ ኢሉባቡር፣ ወለጋ፣ እንዲሁም በአማራ እና ትግራይ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች መኖሩን ገልጸዋል።
«እንደማንኛውም የውጪ ዜጋ ወደ ኢትዮጵያ ስትሄጂ» አሉ አህነር «በምትኖሪበት አካባቢ ኅብረተሰቡ የሚናገረውን ቋንቋ የማመማር ዕድሉን ታገኛለሽ።» እሳቸውም በቤተክርስቲያን አማካኝነት ወደ ኢትዮጵያ ሄደው የሠሩት አፋን ኦሮሞ ተናጋሪ ወገኖች መካከል በመሆኑ ጊዜ ቢወስድባቸውን ቋንቋውን መልመድ መቻላቸውን አጫውተውኛል። ቀለል ያለ ሕይወት እንደሚመርጡ የሚናገሩት አህነር እሳቸው ከጀርመን ትልቅ ከተማ የወጡ ባለመሆኑ አካባቢው ተስማምቷቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ለገጠሩ ማኅበረሰብ አንዳች አገልግሎት ማበርከት መቻላቸው ደስታን ሰጥቷቸዋል። ኅብረተሰቡም «ጥሩ፣ እንግዳ ተቀባይ እና ሁሉን አቃፊ በመሆኑ ብዙ ተምሬያለሁ፤ የራሴንም አጋርቻለሁ።» ይላሉ።
የ58 ዓመቷ ጀርመናዊት የኅብረተሰብ ጤና ባለሙያ ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዓመታት ላበረከቱት አስተዋጽኦ የሀገራቸው መንግሥት በያዝነው ሳምንት ማለቂያ ላይ ሊሸልማቸው ተዘጋጅቷል። እሳቸው ግን ለጉዳዩ እንግዳ ነበሩ፤
«አዎ እኔም ብዙም አላወቅኩም ነበር፤ ጥቂት ጓደኞቹ ያነሳሱት ጉዳይ ነው። እኔ ይኽን ጠብቄ አልነበረም፤ ሆኖም ለሰዎች የተባበረ ሥራ ማለትም ለእኔ እና እዚህ ያሉ ተባባሪዎቼ እንዲሁም ኢትዮጵያ ውስጥ ላሉት ይኽን ታላቅ ሥራ ለሚሠሩ ሰዎች እውቅና እንደመስጠት አድርጌ ነው የወሰድኩት። እስካሁን ከ20 ሺህ በላይ ሰዎችን ማከም ችለናል።»
እንዲያም ሆኖ አህነር በበኩላቸው ያበረከቱትን ያን ያህል አጉልተው ከማውራት መቆጠባቸውን አስተውያለሁ። ኢትዮጵያ ውስጥ በነበራቸው ቆይታ ከቋንቋው ሌላ ሴቶች በማኅበረሰቡ ውስጥ እንደባህሉ የሚስተናገዱበት መንገድ እሳቸው ከለመዱት በጣም መለየቱ ፈታኝ ሆኖባቸው ነበር። እናም በበኩላቸው ሴቶች በማኅበረሰቡ ውስጥ የተሻለ ተሳትፎ እንዲኖራቸው አቅማቸውን የማጠናከር አስተዋጽኦ ለማድረግ መሞከራቸውን ገልጸውልኛል። ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዓመታት በጤናው ዘርፍ የበኩቸውን አስተዋጽኦ ያበረከቱትን ጀርመናዊት ለነበረን ጊዜ እናመሰግናለን።
ሸዋዬ ለገሠ
እሸቴ በቀለ