የሆሮጉድሩ ተፈናቃዮች ሮሮ
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 20 2016ከኦሮሚያ ክልል፤ ሆሮ ጉደሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ ገጠራማ ስፋራዎች በፀጥታ ችግር የተነሳ ከ2 ዓመት በፊት ተፈናቅለው አጋምሳ ከተማ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሰብአዊ ድጋፍ ባለማግኘታችን ለችግር ተጋለጥን አሉ ። ከአሙሩ ወረዳ ተፈናቅለው በሆሮ ጉዱሮ ወለጋ ዞን ዋና ከተማ ሻምቡ ተጠልለው የነበሩ ዜጎችም ነሔሴ 24 ቀን፣ 2015 ዓ.ም ወደ ወረዳው ቢመለሱም ድጋፍ አለማግኘታቸውን ዐስታውቀዋል ። የወረዳው የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ጽ/ቤት በበኩሉ ሰብአዊ ድጋፍ ለተፈናቀሉ ዜጎች ሙሉ በሙሉ ባይዳረስም፤ በተለያዩ ዙሮች መሰጠቱን ገልጸዋል ።
በአሙሩ ወረዳ ሉማ ዋሊ ከተባለ የገጠር መንደር በኅዳር ወር 2014 ዓ.ም በስፍራው በነበረው ግጭት ተፈናቅለው አጋምሳ በተባለ ከተማ እንደሚገኙ የነገሩን ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ነዋሪ ሰብአዊ ድጋፍ ባለማግኘታቸው መቸገራቸውን ገልጸዋል ። ሰብአዊ ድጋፍ የዛሬ 3 ወር ገደማ 15 ኪ.ሎ ስንዴ መውሰዳቸውን ጠቁመው በከተማው ከ8 በላይ ከሚሆኑ ቀበሌዎች የተፈናቀሉ ዜጎች ተጠልለው እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
«አጋምሳ ከተማ ነው የምገኘው ። ቤታችን ከተቃጠለና ንብረታችን ከተዘረፈ በኋላ መኖሪያችንን ለቅቀን ወደዚህ ከተማ መጥተን መኖር ከጀመርን ሁለት ዓመት አልፎናል ። 18 የሚሆኑ ፍየሎች እና 27 ከብቶች ተወስዶብኛል ። ሰብአዊ ድጋፍ በተደጋጋሚ ጠይቀናል፤ እየመጣልን ግን አይደለም ።»
ሌላው አሙሩ ወረዳ አጋምሳ ከተማ ተጠልለው እንደሚገኙ የነገሩን ነዋሪም በአካባቢው ለረዥም ጊዜ በዘለቀው ፀጥታ ችግር ነዋሪው ለዘርፈ ብዙ ችግር መጋለጡን ተናግረዋል ። በስፍራው የነበረው የሰላም እጦት ከሰብአዊ ድጋፍ በተጨማሪም አርሶ አደሩ እንዳያመርት እንቅፋት ሆኖ መቀጠሉን አመልክተዋል ። በአካባቢው የሚስተዋለውን የፀጥታ ችግር በዘላቂነት በመፍታት መንግሥት ወደ ቀዬያቸው እንዲመልሳቸው ጠይቀዋል ።
«በ2014 በተደጋጋሚ በአጋምሳ ከተማና ገጠር ቀበሌዎች ላይ ጥቃት ደርሶ ነበር ። በአጋምሳ ከተማ 01 ቀበሌ ውስጥ ሱቅ ሳይቀር ንብረታችን ተዘርፎ፣ ቤታችን ተቃጥሎ እያለ ከከተማ የተፈናቀሉ ከገጠር የተፈናሉ እየተባለ ምንም ድጋፍ ሳይሰጠን በመቆየቱ ለችግር ተጋልጠናል ። ህጻናትም እየተጎዱ ነው ። አቤቱታችንን ብዙ ጊዜ ቢናቀርብም ምንም መፍትሄ አላገኘንም ።»
ከአሙሩ ወረዳ ተፈናቅለው በዞኑ ዋና ከተማ ሻምቡ ውስጥ አንድ ዓመት ከቆዩ በኋላ በነሐሴ 24 ቀን፣ 2015 ዓ.ም ወደ አሙሩ ተመልሰው ኦቦራ የተባለ ከተማ እንደሚገኙ የነገሩን ሌላው ነዋሪም ለ3 ወራት ያህል ድጋፍ አለማግኘታቸውን ገልጸዋል ።
የአሙሩ ወረዳ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ጽ/ቤት (የቡሳ ጎኖፋ ጽ/ቤት) ኃላፊ አቶ ጂረኛ ረጋሳ በጉዳዩ ላይ በሰጡን ሀሳብ 45 ሺ 3 መቶ 5 የተፈናቀሉ ሰዎች በወረዳቸው እንደሚገኙ ገልጸዋል ። በሁሉም ስፍራ ለሚገኙ የተፈናቀሉ ዜጎች በቂ በሆነ መልኩ ባይደረስም በመንግስትም በግል ተቋማትም ድጋፎች እየተሰጠ እንደሚገኙ ተናግረዋል ።
«የተፈናቀሉ ተብሎ ለተለዩ ዜጎች በ3 ዙር ድጋፍ ለማደረስ ችለናል ። በመንግስትም በግል ተቋማት ሰብአዊ ድጋፍ ወደ ወረዳችን መጥተዋል ። ከ45ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎችም እርሻ ካለማረሳቸው የተነሳ በቂ ላይሆን ይችላል ። ነገር ግን ሰብአዊ ድጋፍ ነጋዴዎችን ሳይጨምር ከገጠር ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ ተሰጥተዋል ።»
በሆሮ ጉደሩ ወለጋ ዞንና ምስራቅ ለወጋ ዞን ስር በሚገኙ ወረዳዎች በተለያዩ ጊዜ በሚከሰቱት ግጭቶች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ተፈናቅለዋል ። የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዩች ማስተባበሪያ ቢሮ (OCHA) መረጃ እንደሚያመለክተው ከአራቱም የወለጋ ዞኖች ከ7 መቶ ሺ በላይ ዜጎች ከዚህ ቀደም በልዩ ልዩ ምክንያቶች ተፈናቅለው ይገኛሉ ።
ነጋሣ ደሳለኝ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ኂሩት መለሠ