1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ትምህርት

ኦሮሚያ ክልል ለትምህርት ተሰጥቷል ያለው ትኩረት

ሰኞ፣ ግንቦት 1 2014

የኦሮሚያ ክልል በሚቀጥለው አንድ ዓመት 6 ሺህ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ማቀዱን አስታወቀ፡፡ ክልሉ ባለፈው ዓመት በህዝብና ባለሃብቶች ተሳትፎ ከ3 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች መገንባቱን በማሳወቅ በሂደቱ ለተሳተፉት ባለድርሻ አካላት እውቅና ሰጥቷል፡፡ ክልሉ አምና የ12ኛ ክፍል አጠናቀው ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎችንም ሸልሟል፡፡

Äthiopien- Auszeichnungen Programm
ምስል፦ S.Getu/DW

This browser does not support the audio element.

አስተያየቱን ያጋራን ተማሪ በ2013 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ትምህርቱን ተከታትሎ ዘንድሮ በመፈተን የከፍተኛ ትምህርት ተቋም በከፍተኛ ውጤት የተቀላቀለው ተማሪ ሁንዴ ተፈሪ ይባላል፡፡ እንደ ሁንዴ ሁሉ የሲቪክስ ትምህርትን ሳያካትት ከ600 548 ውጤት በማስመዝገብ ከኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበው ኮኬት ተስፋዬ ነው፡፡ ይህ ተማሪ ደግሞ በፊዚክስ የትምህርት አይነት ከ100 100 ማስመዝገብም የቻለ ነው፡፡ ኮኬት አብሮት ሲያጠና ከነበረው ጓደኛው ሁነዴ ጋር አጠቃላይ ውጤቱን እኩል እና ከፍተኛ ማምጣታቸውንም ይናገራል፡፡ 

እነዚህ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ሁለት ተማሪዎችን ጨምሮ በህሳብ የትምህርት አይነት ከ100 100 ያስመዘገበች እና በአጠቃላይ ውጤት የሶስተኝነት ደረጃን የያዘች ተማሪ ሲፋን ፊጣ ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ በአዳማ ገልማ አባገዳ ባዘጋጀው የሽልማትና እውቅና መርሃግብር ላይ የሜዳሊያ እና እያንዳንዳቸው የ120 ሺህ ብር ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ ይህ እውቅና የላቀ የሞራል ስንቅ እንደሚሆናቸውም ተማሪዎቹ ይናገራሉ፡፡ 

ምስል፦ S.Getu/DW

እነዚህን ሶስት ተማሪዎች ሃራምቤ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ እያንዳንዳቸውን 100 ሺህ ብር ሽልማት ሲያበረክትላቸው ቀሪውን 20 ሺህ ብር ደግሞ በሁለቱም ጾታ እስከ ሶስት ለወጡ ተማሪዎች የሸለመው የክልሉ መስተዳድር ነው፡፡ ክልሉ የስነዜጋ ትምህርትን ሳያካትት ከ600 በታየው ውጤት ከ500 በላይ ላስመዘገቡ 226 ተማሪዎችም የ15 ሺህ ብር የገንዘብ ማበረታቻ ሸልሟል፡፡ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ቶላ በሪሶ በመድረኩ እንዳሉት የትምህርት ተደራሽነትን ለማሻሻል ባለፈው ዓመት 3000 ትምህርት ቤቶች ለመገንባት መቻሉን በመግለጽ፤ ከዚህ ጎን ለጎን ለትምህርት ጥራት ዋነኛ ትኩረት ሰጥተው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ 

በሽልማትና እውቅና መርሃ ግብሩ ላይ ተግኘው ሽልማትና እውቅናውን ለተማሪዎቹ እና ለባለድርሻ አካላቱ የሰጡት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት አቶ ሽመለስ አብዲሳ በበኩላቸው በቀጣይም አስተዳደራቸው በትምህረት ላይ ማተከሩን እንደሚቀጥል አብራርተዋል፡፡ 

ዘንድሮ በኦሮሚያ ከ600 ሲሰላ ከ500 በላይ ካስመዘገቡ 226 ተማሪዎች 101 ያህሉ በኦሮሚያ ልማት ማህበር ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት የሚማሩ ናቸው፡፡ የ8ኛ ክፍል የሚኒስትሪ ውጤት ማዕክል በማድረግ እና ፈተና በማዘጋጀት ከማላው ክልሉ ተማሪዎችን አወዳድሮ የሚያስገባው ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቱ አንድም ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሳያልፉ የቀሩ ተማሪዎች የሉትም ተብሏል፡፡ የልማት ማህበሩ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ አዱኛ ለዶይቼ ቬለ እንደገለጹትም ልዩ ክትትል እና እንክብካቤ ለሚደረግላቸው ከነዚህ ተማሪዎች 2ቱ ብቻ ከ500 በታች ውጤት አስመዝግበዋል፡፡

ሥዩም ጌቱ 

ልደት አበበ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW