1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ከሰላም ስምምነቱ መደናቀፍ በኋላ የቀጠለው የኦሮሚያ ግጭት

ሰኞ፣ ኅዳር 17 2016

በኢትዮጵያ መንግስት እና (ኦነግ-ኦነሰ) ብሎ በሚጠራው ታጣቂ ቡድን መካከል በታንዛንያ ዳረሰላም ሲካሄድ የቆየው የሰላም ስምምነት መክሸፉን ተከትሎ በኦሮሚያ የሚታየዉ ግጭት መቀጠሉን ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ ነዋሪዎች እንዳሉት ተስፋ የተጣለበት የሰላም ድርድር ከተደናቀፈ ወዲህ ግጭት አለመረጋጋቱ ቀጥሏል፡፡

በኦሮምያ ክልል የቀጠለዉ ግጭት
ኦሮምያ ክልል ምስል፦ Seyoum Getu/DW

የሁለቱ ተፋላሚዎች ውጊያ ህብረተሰቡን ለከፋ የኑሮ መቃወስ ዳርጎታል

This browser does not support the audio element.

በኢትዮጵያ መንግስት እና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር-ኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነግ-ኦነሰ) ብሎ በሚጠራው ታጣቂ ቡድን መካከል በታንዛንያ ዳረሰላም ሲካሄድ የቆየው የሰላም ስምምነት መክሸፉን ተከትሎ በኦሮሚያ የግጭት ይዞታው መቀጠሉን ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ አስተያየታቸውን ከተለያዩ አከባቢዎች ለዶቼ ቬለ የሰጡት ነዋሪዎች እንዳሉት ተስፋ የተጣለበት የሰላም ድርድር ከተደናቀፈ ወዲህ ግጭት አለመረጋጋቱ ቀጥሏል፡፡

ከምስራቅ ወለጋ ነቀምቴ ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡን ለደህንነታቸው ሲባል ግን ስሜ አይጠቀስ ያሉን አስተያየት ሰጪ በአከባቢያቸው ጊዳ አያናን አልፎ በሚገኝ ኢቤንቱ በሚባል ወረዳ በመንግስት እና ታጣቂዎች መካከል የሚደረግ ውጊያ ቀጥሏል፡፡ “የባሰ ነገር ነው እንጂ የተረጋጋ ይዞታ አይስተዋልም፡፡ አሁን ይሄው ኢቤንቱ በሚባል ወረዳ በአንድ ቀን 11 ገደማ ሲቪል ዜጎች ጭምር የተገደሉበት ውጊያ በሁለቱ ተፋላሚዎች መካከል ተደርጓል፡፡ በዘህ በሆሮ ጉዱሩ በኩልም በአባይ ጮመን ወረዳ ፊንጫ አከባቢ በዚህ ሶስት አራት ቀናት የተረጋጋ ይዞታ ያለ ብመስልም ከፍተኛ ጦርነት ሲካሄድ ነበር፡፡ ለሰላም ስምምነቱ እንኳ ሁለቱ አካላት በተቀመጡበት ወቅት ሳይቀር በዚህ አከባቢ ውጊያ ነበር” ይላሉ፡፡

ያልሰመረው የመንግስት እና የኦነግ-ኦነሰ ድርድር

ሌላዋ ሃሳባቸውን ያጋሩን አስተያየት ሰጪ ከምስራቅ ሸዋ ዞን ቦሰት ወረዳ ነው፡፡ “አሁንም የተስተዋለ ሰላም የለም፡፡ የጸጥታ ይዞታው ነገር ሁሉ እንደከበደ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ በአከባቢው አርሶ አደሩ ያመረቱትን እንዴት እንደሚሰበስቡ እንኳ መገመት ከባድ ነው፡፡ ሰው በሚስተዋለው የጸጥታ ሁኔታ አሁንም እየተሸበረ ነው የሚኖረው፡፡ በርግጥ በዚህ አከባቢ በይፋ የሚደረግ የተኩስ ልውውጥ የሚስተዋልበት ውጊያ ሳይሆን አንዱ ሌላውን በሚያድንበት ወቅት ህብረተሰቡ በመሃል የሚሰቃበት ሁኔታ ነው የሚስተዋለው፡፡ ከዚህ የተነሳ በቀየው መቀመጥ የተሳነው አርሶ አደር አሁንም እየተነሳ ወደ መንገድ ዳር እየተጠጋ ሸራ ሰርቶ ህይወት እየገፋ ነው የሚታየው” ብለዋል፡፡

ኦሮምያ ክልልምስል፦ Seyoum Getu/DW

ከደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ቱሉ ቦሎ ወረዳ አስተያየታቸውን የሰጡን ነዋሪ ደግሞ በዞናቸው አለመረጋጋቱ የሚስተዋልባቸው አከባቢዎች ሰፊ ስለመሆናቸው ነው የሚገልጹት፡፡ አስተያየት ሰጪው ህብረተሰቡን ለከፋ የኑሮ መቃወስ ዳርጎታል ያሉት የሁለቱ ተፋላሚዎች ውጊያ በተለይም ማንነታቸው በውል አይታወቅም ባሉት በሌሊት በሚንቀሳቀሱ በዝርፊያ ላይ በተሰማሩም ጭምር አሳዛኝ ያሉት የጸጥታ ይዞታ መስተዋሉንም አመልክተዋል፡፡ “ግጭቱ በአስከፊነቱ ቀጥሏል፡፡ ለአብነትም ባነሳልህ አመያ በሚባል በዚሁ ቅርባችን ባለው አጎራባች ወረዳ የከፋ የጸጥታ ኁነታ ነው የሚስተዋለው፡፡ ከዚህ በፊት ከነበረውም ነው በነዚህ አከባቢዎቨች የጸጥታ ሁኔታው ደፍርሶ የተስተዋለው፡፡ እኔ ካለሁበት ቱሉ ቦሎ ወይም በቾ ወረዳ በተጨማሪ ቶሌ፣ ኢሉ እና ሰደን ሶዶ ወረዳዎች በተለይ መረጋጋቱ የለም፡፡ ይህን እንደ መረጃ ሳሆን ያለሁበትን ነው የማነሳልህ” ሲሉም የጸጥታ መደፍረስ ስፋቱን ያስረዳሉ፡፡

ስለ ታንዛንያው ድርድር የኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች ተስፋ

እንደ እኚህ አስተያየት ሰጪ ማብራሪያም በሁለቱ ተፋላሚዎች መካከል በይፋ የሚደረግ የተውክስ ልውውጥ ጎልቶ አይስተዋልም፡፡ የመንግስት ጦር በቀን እየተንቀሳቀሰ ሸነ ያለውን ሸማቂ ቡድን ሲያድን እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነግ-ኦነሰ) ያለው የታጠቀ ቡድን በበኩሉ በሽምቅ ውጊያ የተለያዩ ጉዳቶችን ሲያደርስ ይስተዋላል ብለዋል፡፡ በኦሮሚያው ግጭት ክፉኛ ከተጎዱ ዞኖች መካከል አንደኛው ከሆነው ከቀሌም ወለጋ ዞን ደምቢ ዶሎ ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡን ነዋሪ ደግሞ በአንጻሩ ከሰሞኑ መረጋጋት ተስተውሏል ይላሉ፡፡ “በዚህ ሰሞን ያለው ሁኔታ ሰላማዊ ነው፡፡ ምናልባት በገጠር አከባቢ ያለውን ሁኔታ እምብዛም በጥልቀት ባላውቅም ደምቢዶሎ አሁን ሰላም ነው፡፡ በዚህ ሰሞን ማለትም ከሰላም ስምምነቱ መደናቀፍ በኋላ ያየነው አዲስ ክስተት የለም፡፡ በሁለቱም ተፋላሚዎች በኩል እስካሁን ጸጥ የማለት ሁኔታ ነው ያለው” ብለዋል፡፡

ኦሮምያ ክልልምስል፦ Seyoum Getu/DW

እኚህ አስተያየት ሰጪ አክለው እንዳብራሩት ግን የስምምነቱ መደናቀፍ በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ስብራት የፈጠረ ሆኖ ነው ያለፈው፡፡ “ታውቃለህ ሰው አንድ ነገር ላይ ይደርሳሉ በሚል በትልቅ ተስፋ ነበር የጠበቀው፡፡ ስምምነት ወርዶ ሰላም ስሰፍን ህዝቡ ከእንግዲህ በተረጋጋ መንፈስ መኀሩን የሚሰበስብበትም እድል ይኖራል ተብሎ ነበር የታመነው፡፡ በስምምነቱ መፋረስ ሰው ሁሉ ትልቅ ሀዘን ተሰምቶታል” ሲሉም ነው አስተያየታቸውን የሰጡት፡፡ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ መረጃዎችን ለመጠየቅና ስለቀጣይ የመንግስት ውጥን ለማወቅ ለኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ብንደውልላቸውም ስልካቸውን ስለማይመልሱ ዶቼ ቬለ አስተያየታቸውን ማካተት አልቻለም፡፡

የሰላም ንግግሩ ተስፋ እና የሀገሪቱ መጻኢ ዕጣ ፈንታ

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ምንግስት መከላከያ ሰራዊት ከሰሞኑ በተደጋጋሚ በይፋዊ የማህበራዊ መገናኛ ገጹ ላይ በሚለቃቸው መረጃዎች ላይ ግን “አሸባሪው የሸኔ ቡድን”  ያለው የታጠቀ ሸማቂ ቡድን ላይ ተከታታይ ወታደራዊ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን አስረድቷል፡፡ ምዕራብ ሸዋ ዞን ጀልዱ ወረዳ፣ ምእራብ ወለጋ ዞን ቆንዳላ ወረዳ፣ እንዲሁም ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ሰበታ ሃዋዝና ቀርሳ ማሊማ ወረዳዎች የአገር መከላከያ ሰራዊቱ ከሰሞኑ ታጣቂዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን ከጠቃቀሳቸው አከባቢዎች ይገኛሉ፡፡ መንግስት በሽብርተኝነት የፈረጀውና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን በፊናው ከሰላም ስምምነቱ መክሸፍ በኋላ መንግስት መጠነሰፊ ጥቃት እንደከፈተበት አሳውቆ ለቀጣይ ሰላማዊ ድርድር ግን አሁንም በራቸው ክፍት መሆኑን ማሳወቁም ይታወሳል፡፡

 

ሥዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW