ኦክስፋም፤ በዓለም ከፍተኛ ድህነትና ከፍተኛ የሃብት ክምችት ጨምሯል
ሰኞ፣ ጥር 8 2015
ማስታወቂያ
ከ25 ዓመታት ወዲህ በዓለማችን ህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ድህነት ብሎም ከፍተኛ ሃብት ክምችት ለመጀመርያ ጊዜ በእኩል እየጨመረ ሄዷል ሲል ሲል ኦክስፋም የተባለው የብሪታንያ የግብረሰናይ ድርጅት ያደረገዉን ጥናት አያይዞ ገለፀ። ኦክስፋም በመግለጫዉ የኩባንያ ባለቤቶች እና ባለሃብቶች፤ በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት እና የነዳጅ ኃይል ቀውስ በተከሰተበት በአሁኑ ወቅት አሸናፊ ሆነዋል ሲል በሪፖርቱ ገልጿል። ድርጅቱ ጥናቱን ይፋ ያደረገዉ የዳቮሱን የዓለም የኢኮኖሚ መድረክ ተከትሎ ሲሆን ይህ ጥናት በዚሁ የኢኮኖሚ መድረክ ላይ ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል። በኮሮና የዝዉዉር እገዳ እና በነዳጅ ኃይል እጥረት ምክንያት በዓለማችን ቢያንስ 1.7 ቢሊዮን ሠራተኞች የሚኖሩት የዋጋ ግሽበት ከደሞዝ እድገት በላይ በሆነባቸው አገሮች ውስጥ እንደሆነ ኦክስፋም አሳስቧል። እንደ ኦክስፋም በዓለማችን ከአሥር ሰዎች መካከል አንዱ በረሃብ የተጠቃ ነዉ ። ይህ ማለት ደግሞ በዓለማችን 828 ሚልዮን የሚያህል ህዝብ በረሃብ ዉስጥ ነዉ ሲል ኦክፋም በጥናቱ አሳይቷል። ከዚህ ችግር ለመዉጣት ከሁሉም በላይ ሀብታሞች ባለፀጎች ከፍተኛ ቀረጥ እንዲከፍሉ ሲል ኦክስፋም ጥሪ አቅርቧል።
አዜብ ታደሰ
ኂሩት መለሰ