ከሀማስ ጥቃት በኋላ የአውሮጳ ኅብረትና የእሥራኤል ግንኙነት ይዞታ
ማክሰኞ፣ መስከረም 28 2017የዛሬ ዓመት መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም. እሥራኤልን ጨምሮ ዩናይትድ ስቴትስ ፣ጀርመን ፣ብሪታንያ የአውሮጳና ኅብረትና ሌሎችም ሀገራት አሸባሪ የሚሉት ታጣቂው ቡድን ሀማስ በእሥራኤል ላይ ጥቃት ከፈጸመ በኋላ የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት አቋም ግልጽ ነበር። አባል ሀገራቱ በኅብረት ጥቃቱን በጽኑ አውግዘው ከእስራኤል ጎን ቆመዋል። እሥራኤል ከዚህን መሰሉ የዘፈቀደ ጥቃት ራሷን የመከላከል መብትም እንዳላትም እውቅናም ሰጥተው ነበር። የአውሮጳ ኅብረት የውጭ ጉዳዮች ሃላፊ የጆሴፕ ቦሬል ቃል አቀባይ እንዳሉት ኅብረቱ የእሥራኤልን ራሷን ከአሸባሪዎች የመከላከል መብት ይደግፋል። ሆኖም አሁንም አጋሩ እሥራኤል የጋዛው ጦርነት የሚያስከትላቸውን ሰብዓዊ መዘዞች እንድታጤን ጥሪ ማቅረቡን ቀጥሏል። ሀማስ በእሥራኤል ላይ በጣለው ጥቃት ቁጥራቸው 1200 የሚጠጋ ሰዎችን ሲገድል ከ250 በላይ ሰዎችን ደግሞ ጋዛ ሰርጥ ወስዶ አግቷል። የፍልስጤም ምንጮች ደግሞ በእስራኤል ጦር የምድር ውጊያ ከ40 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል ይላሉ።
የተባባሰው የእስራኤል ሀማስ ጦርነትና የአውሮጳውያን አቋም
የኅብረቱን አባል ሀገራት ያወዛገበው የተኩስ አቁም ጥያቄ
ካልተጠበቀው የሀማስ የሽብር ጥቃት በኋላ የኅብረቱ አባል ሀገራት አንድ ላይ ቢቆሙም አንድነቱ ከዚያ በኋላ ግን እንደበፊቱ አልዘለቀም። ለምሳሌ አባል ሀገራት ረዘም ያለ የተኩስ አቁም ይደረግ ወይስ ለአጭር ጊዜ ብቻ የሚቆይ ይሁን በሚለው ጉዳይ ላይ የተካሄደው ክርክር አንዱ የልዩነታቸው ማሳያ ነበር።በወቅቱ እንደ ጀርመንና ቼክ ሪፐብሊክ ያሉ ሀገራት የተኩስ አቁም ጥሪው የእስራኤልን ራሷን የመከላከል መብት እንደነፈገ የሚቆጠር ነው ሲሉ ተከራክረው ነበር። ከኅብረቱ መቀመጫ ብራስልስ ሂደቱን በቅርብ የሚከታተለው የብራሰልሱ ዘጋቢያችን ገበያው ንጉሴ እንዳስታወሰው በእስራኤል ጉዳይ ላይ የኅብረቱ አባል ሀገራት ልዩነት መታየት የጀመረው እሥራኤል በሀማስ ላይ ጦርነት ከከፈተች በኋላ ብዙም ሳይቆይ ነበር።
የአውሮጳ ኅብረት የሰብዓዊ መተላለፊያና ፋታ ጥሪ
በተደጋጋሚ ጊዜያት እሥራኤል ሰብዓዊ መተላለፊያዎችን እንድትከፍት አባል ሀገራት ጥሪ ሲያቀርቡ ነበር። በመጋቢት 2024 ለዘላቂ የተኩስ አቁም አስቸኳይ ሰብዓዊ ፋታ እንዲደረግም ኅብረቱ ጠይቆ ነበር። ከዚሁ ጋርም የታገቱ እንዲለቀቁና የጋዛ ሰርጡ ሰብዓዊ ቀውስ እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል።ባለፈው ሰኔም ኅብረቱ ፍጹም ተቀባይነት የሌለውን በበርካታ ሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመውን ግድያ አሳሳቢነት አንስቶ ሁለቱም ወገኖች በግጭቱ ለሰላማዊ ሰዎች ጥበቃ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል። ምንም እንኳን ኅብረቱ ግጭቱ እንዲበርድ ሰብዓዊው ቀውስም እንዲቆም ጥሪ ቢያቀርብም የሚሰማው ግን አላገኘም። ለዚህም ብዙ ምክንያቶች አሉ።
በጋዛ እና ዩክሬይን ጉዳይ የመከሩት የአዉሮጳ ኅብረት የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች
በኅብረቱ መካከል ልዩነቱን ካሰፉት ምክንያቶች ውስጥ የኅብረቱ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርዙላ ፎን ዴር ላየን ጥቃቱ ከደረሰ በኋላ በእስራኤል ያደረጉት ጉብኝት አንዱ ነበር። የፎን ዴር ላየን ጉብኝት ኅብረቱ ለአንድ ወገን ብቻ ያደላ መስሎ እንዲታይ አድርጎታል የሚል ትችት አስከትሏል። እንደገበያው አገላለጽ የኅብረቱ ኮሚሽን ባለስልጣናት በእሥራኤልና ሀማስ ጦርነት ላይ በሚሰጧቸው አስተያየቶችም ላይ ልዩነቶች ተስተውለዋል። ይህ አባል ሀገራቱ በመካከለኛው ምሥራቅ ላይ የሚከተሉት ፖሊሲ ልዩነት ነጸብራቅም ተደርጎ ነው የሚወሰደው።
ኂሩት መለሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ