1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከሁለት ወራት በላይ ስልክና ኢንተርኔት የተቋረጠበት ካማሺ ዞን

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 11 2015

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሺ ዞን የስልክና ኢንተርኔት አገልግሎት ከኅዳር ወር መጀመሪያ አንስቶ ተቋርጦ እንደሚገኝ ወደ አሶሳ ከተማ የመጡ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ በዞኑ ስር በሚገኙት አምስት ወረዳዎች ውስጥ ከህዳር 1/2015 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎቱ መቋረጡንና የባንክ አገልግሎትም ማግኘት አለመቻላቸውን ነዋሪዎቹ አመልክተዋል፡፡

Karte Äthiopien AM

የስልክ የኢንተርኔት የባንክ አገልግሎት ከተቋረጠ ወራቶች አልፈዋል

This browser does not support the audio element.

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሺ ዞን የስልክና ኢንተርኔት አገልግሎት ከኅዳር ወር መጀመሪያ አንስቶ ተቋርጦ እንደሚገኝ ወደ አሶሳ ከተማ የመጡ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ በዞኑ ስር በሚገኙት አምስት ወረዳዎች ውስጥ  ከህዳር 1/2015 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎቱ መቋረጡንና የባንክ አገልግሎትም ማግኘት አለመቻላቸውን ነዋሪዎቹ አመልክተዋል፡፡ የካማሺ ዞን ኮሙኒኬሽን ጉዳዩች ጽህፈት ቤት በበኩሉ የስልክና ኢንርኔት አገልግሎት ከተቋረጠ ከአንድ ወር በላይ እንደሆነው አመልክተዋል፡፡ የኢትዮ ቴሌኮም ምዕራብ ሪጅን ኃላፊ አቶ ሙላቱ ጉዴታ በብልሽት ምክንያት አገልግሎቱ መቋረጡን ጠቁመዋል፡፡ ወደ ካማሺ የሚወስደው መስመር ላይ የነበረው የጀነረተር ሞተር ብልሽትና ትራንስፎርመር መቃጠል ምክንያት እንደሆነ ጠቁሟል፡፡

የስልክ አገልግሎትምስል picture alliance/Joker

በካማሺ ዞን ሴዳልና እና ሚዥጋ በሚባሉ ወረዳዎች የስልክ ኢንተርኔት አገልግሎት ከተቋረጠ ከ2 ወራት በላይ እንደሆነው ቅሬታቸውን ለማቅረብ ወደ አሶሳ  የመጡ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ ከህዳር  ወር መጀመሪያ አንስቶ ደግሞ በዞኑ አምስት ወረዳዎች ውስጥ ሙሉ በመሉ አገልግሎቱ መቋረጡ የተነገረ ሲሆን በኢንተርኔት አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ስራ ማቆማቸውን አክለዋል፡፡ ህብረተሰቡ ከባንክ ገንዘብ መውሰድ አለመቻሉን እንዲሁም በባንክ ክፍያ የሚፈጽምላቸው  የመንግስት ሰራተኞች ወደ አሶሳ እና አጎራባች የምስራቅ ወለጋ ወረዳዎች በመሄድ ለተጨማሪ ወጪ እየተዳረጉ እንደሚገኙም አብራርተዋል፡፡

የዞኑ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ጀርሞሳ ተገኜ ብልሽቱ እንዲጠገን በተደጋጋሚ ጥያቄዎች ቢያቀርቡም ከተቋሙ ምላሽ መስጠት እንዳልተቻለ ገልጸዋል፡፡ ሳስጋ በተባለ የምስራቅ ወለጋ ወረዳ ውስጥ ብልሽት እንዳጋጠመው የተገለጹ ሲሆን ተቋሙ ከሁለት ሳምንት በፊት በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሄ እንደሚያበጅ መግለጹንም አክለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የዞኑ ከተማ ካማሺን ጨምሮ አምስት በሚደርሱ ወረዳዎች ላይ አገልግሎቱ ተቋርጦ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡ በመስከረም ወር 2015 ዓ.ም እንደዚሁ አገልግሎቱ ለተወሰነ ቀናት ተቋርጦ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፤ አሶሳምስል Negassa Desalegn/DW

በምስራቅ ወለጋ ዞን ዋና ከተማ ነቀምቴ ውስጥ የሚገኘው የኢትዮ ቴሌኮም ምዕራብ ሪጅን በበኩሉ ብልሽቱን ለመጠገን እና አገልግሎትን ለመመለስ እየሰራ እንደሚገኝ ለዶቼቨለ ተናግረዋል፡፡ የሪጅኑ ኃላፊ አቶ ሙላቱ ጉዴታ በመስመሩ ላይ በደረሰው ብልሽት ምክንያት አገልግሎቱ መቋረጡን ገልጸው ለጥገናው የሚሆኑ የመለዋወጫ ዕቃዎች እንደ ሐይል አስተላላፊ(ትራንስፎርመር) እና ጀነረተር እጥረት ምክንያት ረጅም ጊዜ እንደወሰደ ጠቁመዋል፡፡ ጥገናው በዛሬው ዕለትም ሊጠናቀቅ እንደሚችል አክለዋል፡፡

"ለመስመሩ የተቀመጠው ጀረተር ሞተሩ ተበላሽቶ ቆይቷል፡፡ የቴክኒክ ብልሽት ነው ያጋጠመው፡፡ የተገጠመለት ትራንስፎርመርም በመቃጠሉ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት ተቋርጦ ቆይተዋል፡፡  አገልግሎቱን  ለማስጀመር ጀነረተርና የሚያስልጉ ቁሳቁሶች ተሟልተው ባለሙያዎች በመስራት ላይ ይገኛሉ" ብለዋል፡፡

ነጋሳ ደሳለኝ

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW