1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

«ከሁሉ ነገር ሀገሬ ትቀድምብኛለች»ድምፃዊት ራሄል ጌቱ

እሑድ፣ መስከረም 30 2014

ለሀገሯ ኢትዮጵያ ያላት ፍቅር ከልጅነቷ ጀምሮ አብሯት ያደገ መሆኑን የምትገልጸው ራሄል፤ ኢትዮጵያዬ የሚለውን ሙዚቃም ይሁን የሙዚቃው ቪዲዮ ከሁሉ ነገር በላይ ሀገር ይቀደማል በሚል ስሜት በመስራቱ ይህ ስሜት ወደ አድማጩ መጋባቱን ገልፃለች።  

Rahel Getu | äthiopische Musikerin
ምስል፦ Privat

«ከሁሉ ነገር ሀገሬ ትቀድምብኛለች»ድምፃዊት ራሄል ጌቱ

This browser does not support the audio element.


ድምፃዊት ራሄል ጌቱ ሙዚቃን የጀመረችው ቀደም ሲል «የኛ» ቆይቶም «እንደኛ» በሚለው የታዳጊ ሴቶች የሙዚቃ ቡድን ውስጥ በልጅነት ዕድሜዋ ነው። በግሏም ጥሎብኝ፣ ያገሬ ሰው ፣አልጓጓምን የመሳሰሉ ተወዳጅ  ነጠላ ዜማዎችን ለአድማጭ አድርሳለች።በቅርቡ ደግሞ «እቴ እሜቴ» የሚል የሙዚቃ አልበም እንካችሁ ብላለች።ከአዲሱ የሙዚቃ ስራዋ ውስጥ በተለይ  ቅድስት ይልማ በዳይሬክተርነት የመራችው ኢትዮጵያዬ የሚዚቃ ቪዲዬ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከአራት ሚሊዮን በላይ ሰዎች የተመለከቱት እጅግ  ተወዳጅ ዜማ ሆኗል።
አንጋፋና ወጣት የሙዚቃ ባለሙያዎች የተሳተፉበት  አዲሱ  የሙዚቃ አልበም «እቴ እሜቴ»የሚለው መጠሪያ የተሰጠው፤ ራሄል እንደምትለው የሁሉንም ሙዚቃዎቿን ሀሳብ አጠቃሎ የሚይዝ፣ በትልቁም በትንሹም በጋራ የሚታወቅ እና ለጀሮ እንግዳ ያልሆነ ሀገርኛ ቃል በመሆኑ ነው።
ለአዳዲስ የሙዚቃ ሰዎች ዕድል በመስጠት አምናለሁ የምትለው ራሄል የአንጋፋዎቹ የሙዚቃ ሰዎች ልምድና ተሞክሮ የአዳዲሶቹ ባለሙያዎች  ሙሉ ጊዜና አቅም ጋር ተዳምሮ የሙዚቃ ስራዋን በጋራ የተዋጣለት እንዲሆን በማድረጋቸው ደስተኛ መሆኗን ተናግራለች።እንደ ራሄል ይህ ጥረታቸው አልበሙን በሙዚቃ ታዳሚያን ዘንድ ከጠበቀችውና ካሰበችው በላይ ጥሩ ተቀባይነት እንዲያገኝ አድርጎታል ።
ለሀገሯ ኢትዮጵያ ያላት ፍቅር  ከልጅነቷ ጀምሮ አብሯት ያደገ መሆኑን የምትገልጸው ራሄል፤ ከሁሉ ነገር በላይ ሀገር ይቀደማል በሚል ስሜት ኢትዮጵያዬ የሚለውን ሙዚቃም ይሁን የሙዚቃውን ቪዲዮ በመስራቷ ይህ የእሷ ስሜት ወደ አድማጩ  መጋባቱን ተናግራለች። 
«ከሁሉ ነገር በላይ ሀገር ይቀድማል ብዬ አስባለሁ ።ለማዘንም ለመደሰትም ለማልቀስም ሀገር ያስፈልጋል የሚል አመለካከት አለኝ።ሁሉ ነገር የሚኖረው ሀገር ሲኖር ነው።ከሁሉ በፊት ይቀድማልና ፤ለኔ ሀገሬ ትቀድምብናለች።ሰላም ሆና ማየት እፈልጋለሁ።የሆነ ጊዜ የነበረችው ኢትዮጵያ እንድትመለስ እፈልጋለሁ ተስፋም አለኝ።በታናናሾቻችን በአዲሶቹ ትውልዶች። ኢትዮጵያዬ የሙዚቃ ቪዲዬ ይህ ሁሉ ስሜት ስለተካተተበት ይመስለኛል እንደተመልካችም እያለቀስኩ የማይበት ሁኔታ አለ ።»ስትል ለሙዚቃው ያላትን ጥልቅ ስሜት ገልፃለች።
 ሙዚቃው «ሀገሩን የሚወድ ሁሉ የሚወደው ሙዚቃ ነው» የምትለው ራሄል፤ለዚህም በሙዚቃው ላይ  የተሳተፉ ባለሙያዎች ድርሻ ከፍኛ መሆኑን አብራርታለች።
ራሄል ሁሉምንም የሙዚቃ ስራዎቿን እንደምትወዳቸው፤ ነገር ግን «ትረፊ»የሚለው ሙዚቃ ለእሷ ህይወትና አመለካከት የቀረበ መሆኑንም አጫውታናለች።

ምስል፦ Privat
ምስል፦ Privat

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

 

ፀሀይ ጫኔ 
ሽዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW