1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

"ከሐይሊ ጉቢ የወጣው «አሽ» ውፍረት ያለውና በጣም ብዙ ቦታ እንደሸፈነ ነው"

ልደት አበበ/ Lidet Abebe
ረቡዕ፣ ኅዳር 17 2018

በአፋር ክልል ሐይሊ ጉቢ ያለው የእሳተ ገሞራ እንቅስቃሴ ጋብ ማለቱ ቢገለፅም በአፍዴራ የሚገኙ መንደሮች በአመድ መሸፈናቸውን፤ አመዱም በነዋሪዎች ላይ ሳል ማስከተሉ፤ እንዲሁም እንስሳት የሚበሉት እና የሚጠጡት ነገር እንደሌላቸው ተገልጿል።

ሐይሊ ጉቢ እሳተ ገሞራ ከፍንዳታው በፊት  ጉድጓዳማ ተራራ
ሐይሊ ጉቢ እሳተ ገሞራ ከፍንዳታው በፊትምስል፦ Enqu Mulugeta

የእሳተ ገሞራው እንቅስቃሴ በስድስተኛው ቀን ምን ይመስላል?

This browser does not support the audio element.

በአፋር ክልል ሐይሊ ጉቢ እሳተ ገሞራ ከተከሰተ ስድስተኛ ቀኑን ይዟል። በሰመራ ዮኒቨርሲቲ የሥነ-ምድር ተመራማሪ የሆኑት ኖራ ያኒሚኦ ዛሬ በስፍራው የታዘቡትን ለዶይቸ ቬለ ሲናገሩ እንዳሉት «ቮልካኒክ አሽ» ተብሎ የሚጠራው እና ከእሳተ ጎሞራው የሚወጣው አመድ መጠን ቀንሷል።
« ከበኤርትዓሌ ከ 10 እስከ 13 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው ይኼ  ፍንዳታ የተከሰተው። ዛሬ እንዳየነው ሲወጣ የነበረው «አሽ» ቀንሷል። ኤርትዓሌ ላይ ደግሞ ጭስ ይታያል። በተጨማሪ ደግሞ  በፍንዳታው ምክንያት አንድ ቦታ ላይ ኮላፕስ ያደረጉ እንትኖች [የመሬት አካል] አሉ። ይኼ ከሐይሊ ጉቢ የወጣው «አሽ» ውፍረት ያለው እና በጣም ብዙ ቦታ እንደሸፈነ ነው ዛሬ ያየነው።»   ይላሉ የሥነ-ምድር ተመራማሪ የሆኑት ኖራ።

በኢትዮጵያ ከ12,000 ዓመታት በኋላ የፈነዳው ሐይሊ ጉብ እሳተ ገሞራ በረራ አስተጓጎለ

እሳተ ጎመራው ባስከተለው ፍንዳታ እስከ 14 ኪሎ ሜትር ወደ ሰማይ ከፍታ ያለው አመድ ወይም ባለሙያው እንደሚሉት «ቮልካኒክ አሽ»  አካባቢው ተሸፍኖ እንደነበር የተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች ዘግበዋል።ከዚህ ጋር በተያያዘም የተለያዩ የአየር መንገዶች በረራቸውን ሰርዘዋል። 
የሥነ-ምድር ተመራማሪው  ኖራ ያኒሚኦ ፍንዳታው እንዴት ሊከሰት እና የመሬት ክፍልም ሊደረመስ እንደቻለ አብራርተዋል።« የታፈነ እንፋሎት ነው። የታመቀ ጋዝ ነበር። ልክ ያ ጋዝ ቀዳዳ ነገር ሲያገኝ ነው ይኼ ነገር የተከሰተው። እና ሐይሊ ጉቢ አካባቢ ላይ ያ ነገር ሲተነፍስ ከኤርትዓሌ ደቡባዊ የሆነ ቦታ ላይ የሆነ ቦታ ላይ ሰምጧል። ማለት ነው።  ከዚህ በፊት ላቫ የነበሩበት ድንጋዮች ነበሩ። እና እንዳለ እንደተደረመሰ ነው ዛሬ ማየት የቻልነው። »


የአፋር ክልል ጤና ቢሮ በፍንዳታው ምክንያት የተከሰተው አመድ እና ብናኝ የጤና ጉዳት ስለሚያስከትል ሕብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ማሳሰቢያ ሰጥቷል። የአካባቢውን ባለስልጣናት ዋቢ አድርጎ የዘገበው አሶሺየትድ ፕረስ እንዳለው በአካባቢው የሚገኙ መንደሮች በአመድ በመሸፈናቸው ነዋሪዎች ላይ ሳል አስከትሏል።   እንዲሁም እንስሳት የሚበሉት እና የሚጠጡት ነገር ሙሉ በሙሉ ተሸፍኖባቸዋል።

ሐይሊ ጉቢ እሳተ ገሞራ ሲፈነዳ እስከ 14 ኪሎ ሜትር ወደ ሰማይ የሚትጎለጎል አመድ አስከትሏልምስል፦ Afar Gov. Communication Bureau/Anadolu Agency/IMAGO

ከ12 ሺ አመታት በላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈነዳው እሳተ ጎሞራ ዳግም የሚያገረሽበት አጋጣሚ ይኖር ይሆን? የሥነ-ምድር ተመራማሪ ኖራ  ለቅድመ ትንበያ ያስቸግራል ይላሉ። የተፈጥሮ አደጋ መቼ ይከሰታል የሚለውን በትክክል ለመተንበይ አይቻልም። ግን ኤርትዓሌ ይታወቃል። አመቱን በሙሉ አክቲቭ የሆነ ቦታ ነው። ምናልባት ሊከሰትም ላይከሰትም ይቻላል።»
በአፋር ክልል እሳተ ገሞራው በፈነዳበት 30 ኪሎ ሜትር ክልል ውስጥ 9,000 ሰዎች ገደማ እንደሚኖሩ ይገመታል። 

ልደት አበበ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW