ከሕጋዊ የዋጋ ተመን በላይ የሚሸጠው ነዳጅ ያስከተለው ፈተና
ሰኞ፣ ነሐሴ 5 2017
“አሁን ከዚሁ ከአዲስ አበባ በበርሜል ለጭነት ተሸከርካሪ ደርሶ-መልስ የሚሆነን ነዳጅ እየቀዳን ጭነን መውጣት ጀምረናል” የሚሉት የአገር አቋራጭ አሽከርካሪ ባለንብረት በኢትዮጵያ በሁሉም አቅጣጫ የሚጠየቅ ነዳጅን ከታሪፍ ጭማሪ የመሸጥ ፍላጎት የእለት ለእለት ስራቸውን በብርቱ መፈተኑን አስረድተዋል፡፡ አሁን ላይ መንግስት በይፋው ካወጣው የ121ብር ግድም የናፍጣ ዋጋ ከ130 እስከ 250 ብር በሕገ-ወጥ መንገድ የሚሸጥባቸው ከማደያ ጀምሮ እስከ የሰፈር ውስጥ ችርቻሮ መኖሩንም የገለጹት በጉዳዩ የተማረሩት አስተያየት ሰጪ፤ “አሁን ትናንት ያበሎ አከባቢ ለከባድ ተሸከርካሪ አንቀዳም ብለውን ተጉላላን” የሚሉት አስተያየት ሰጪው፤ ወራቤ፣ ባላክ የሚባል አከባቢ ከ140-150 በታች አይሸጡም ሲሉም ነዳጅ ከማደያ በተተመነ ዋጋ ማግኘት ቀላል አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በፊት መሰል የአሽከርካሪዎችን ሪፖርት መቀበሉን እና ባደረጋቸው የመስክ ክትትል የተለያዩ እርምጃዎች መወሰዳቸውን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እንዲሁም የነዳጅ ባለስልጣን በተደጋጋሚ ማብራሪያ ሰጥተውበታል፡፡ ይህ መንግስት በማደያዎች እና ነዳጅን በጥቁር ገቢያ በሚቸበችቡት ላይ ወሰድኩ ያለው እርምጃ ለውጥ አምጥቶ ይሆን? አስተያየት ሰጪ አሽከርካሪና የተሸከርካሪ ባለንብረት ግን ይህን ብለዋል፡፡ “አሁን ቡሌ ሆራ ያጋጠመን 140 ካልሆነ አንሸጥም ብለውን ስንትቦታ ሪፖርት አድርገን ነው ያስለቀቅነው” ያሉን ተገልጋዩ በማደያዎች ነዳጅ ከ130-160 የሚቸበቸብበትም አጋጣሚ ሰፊ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
ከማደያ ውጪ ወጥተው በሚቸበቸብ የነዳጅ ችርቻሮ ላይ ደግሞ ከ200 በር በላቀ ዋጋ ነዳጅ እንደሚሸጥ የገለጹት ተጠቃሚው፤ “አሁን ባለፈው ሳምንት አማራጭ ሳጣ አዋሽ ለማን አከባቢ ለመኪና አንዱን ጄሪካን ነዳጅ በ7000 ብር ማለትም አንዷን ሊትር ከ200ብር በላይ ሂሳብ ሞልቼ አልፌያለሁ” ብለዋልም፡፡ በሁሉም መስመሮች ነዳጅን ከታሪፍ በላይ የመሸጥ ችግር እንደሚስተዋልም ገልጸው፤ “ፖሊስ እና የንግድ ቁጥጥር ሰራተኞች በቆሙበትም ነዳጅ በ140 ስሸጥ ይታያል” ነው የሚሉት፡፡
የችግሩን መኖር ለዶይቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት ያረጋገጡት የኢትዮጵያ ነዳጅ ባለስልጣን ዋና ስራ አስከያጅ ደስታ መኳንንት መስሪያ ቤታቸው ከክልሎች ጋር ጉዳዩን በእየለቱ በመከታተል ላይ መሆኑን ገልጸውልናል፡፡ “በህግ ከሳችሁ ቅጡ ብለናል፤ አዋጁ በሚያዘው መሰረት” በማት በየእለቱ ምን እርምጃ እንደተወሰደ ከክልሎች ተወካዮች ጋር እየገመገሙ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ሰው ባገኘው አጋጣሚ ነዳጅ እየሰረቀ ነው ለዚህም መረጃ ከተገኘ ከተጠያቂነት የሚመልጥበት መንገድ የለም ነው ያሉት፡፡
በሂደቱ ተወስዷል የሚባለው እርምጃ በተጨባጭነት በየትኞቹ ተቋማት ላይ ነው የተወሰደ በሚልም ተጠይቀው፤ “ስድስት ኩባንያ እኮ አሁን ለሁለት ወር አግደናል፤ በስራቸው የሚገኙ ማደያዎች በሙሉ ለሁለት ወር ነዳጅ አያገኙም፡፡ ለሰባት ኩባንያዎች ደግሞ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጥተናል” ብለዋል፡፡ ሆኖም የኩባንያዎቹን ማንነት ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡ ለሁለት ወራት ከነዳጅ ስርጭት ከታቀቡት ድርጅቶች በተጨማሪ በማስጠንቀቂያ ላይ ያሉት የሰባቶቹ ኩባንያዎች ጉዳይም ታይቶ ጠበቅ ያለ እርምጃ እንደሚጠብቃቸው አስረድተዋል፡፡
ወረድ ሲልም ቅጣቱ ከዚህም እንደምልቅ የገለጹት ኃላፊው፤ “254 ቦቲ በተባለበት ቀን ባለመድረሱ በ116 ሚሊየን ብር ተቀጥተዋል፡፡ በማስጠንቀቂያ ላይ ያሉ ሰባት ኩባንያዎችም በቀጣይ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ቅጣት ነው የሚጠብቃቸው፡፡ በማደያዎችም ተመሳሳይ ችግር የተገኘባቸው እስር ቤትም የገቡ አሉ፡፡ ቀደም ሲል የሕግ ክፍተትም የነበረ በመሆኑ አሁን ግን በአዲሱ አዋጅ መሠረት ጠበቅ ያለ እርምጃ ነው የሚወሰደው” ብለዋልም፡፡ በዚህ ዓመት ብቻ ከ1.5 ሚሊየን ሊትር የሚልቅ ነዳጅ በህገወጥ መንገድ ስዘዋወር ታይዞ መወረሱንም ያስረዱት ኃላፊው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተዘረጋው የጂ.ፒ.ኤስ ክትትል የነዳጅ ኮንትሮባንድ ወንጅል መሻሻል ማሳየቱንም ገልጸዋል፡፡
ስዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ