ከመሬት የገነፈለው የደቡብ ወሎ ዞን የነዳጅ ሀብት
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 2 2018
የነዳጅ ሀብቱ በ2005 በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ፋልከን ፔትሮ ኢንተርናሽናል በተሰኘ የእንግሊዝ ኩባንያ የተጠናና ውጤቱ የታወቀ ቢሆንም እስካሁን ድረስ መልማት አለመቻሉ ነው የተነገረው። የደቡብ ወሎ ዞን መዐድን ቢሮ በበኩሉ በአካባቢዉ የነዳጅ ዘይት መኖሩን ገልፆ በመንግሥት በኩል ተጨማሪ ጥናቶች እየተሠሩ ነው ብሏል ።
ባለፉት 52 ዓመታት ከ1966 ዓ.ም. ጀምሮ የነዳጅ ዘይት ሀብት በቀድሞው ወረኢሉ ወረዳ እና በአሁኑ የለገሂዳ ወረዳ የተመረጡ ስፍራዎች መኖሩ ይታወቃል የሚሉት አቶ ሰይድ አህመድ ነዳጅ ቋጥኙን ከፍሎ እየወጣም በመቸላ ወንዝ ላይ ሲፈስ ዓመታት ማስቆጠሩን ይናገራሉ። የአካባቢው ማኅበረሰብም በኩራዝ ለመብራትነት ሲጠቀምበት ቆይቷል ሲሉ ነው የተናገሩት።
ቋጥኝ ዘልቆ የወጣዉ ነዳጅ
«ውኃው ይፈሳል ወንዙ ላይ ነዳጁን በእንጨት በተለያየ ነገር እያነሳን እየቆፈርን በተለያየ መያዣ ቤት እያመጣን ኩራዝ ይባላል ዱሮ ለመብራትነት ማኅበረሰቡ ይጠቀምበታል።»
የእንግሊዙ ፋልከን ፔትሮ ኢንተርናሽናል በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር በ2005 ዓ.ም. በአካባቢው ሰፊ ጥናት አጥንቶ የነዳጅ ዘይት ሀብቱ መኖሩን አረጋግጧል የሚሉት አቶ ዮሐንስ እሸቴ ድርጅቱ በሰጠው አቅጣጫ መሠረትም የነዳጅ ሀብቱ ባለበት አካባቢ የሚኖሩ የማኅበሰብ ክፍሎችን ወደ ሌላ ስፍራ ለማስፈር የአካባቢ ግምገማ ጥናት ተከናውኗል ይላሉ፡፡
‹‹ደጋ ላይ በመሣሪያ ሲፈልጉ ለገሂዳ ወረዳ ጉራና ትምህርት ቤት ጋር መቶ ፐርሰንት አገኘነው አሉ። ተደሰቱ። በቅርብ ቀን እንመጣለን ብለው ሄዱ ተመልሰው መጡ ሰብስበውም አወያዩን። ከዚያም ከነዳጅ በተገኘበት አካባቢ ያለው ማኅበረሰብ ይለቃል አሉን ጥናት አጠኑ በዚያው ጠፉ ይመጣሉ ብለን ስንጠብቅ።››
ነዳጅ ይወጣል የሚል ተስፋ ያላቸዉ የአካባቢዉ ማኅበረሰብ
አሁን ላይ ለ52 ዓመታት ነዳጅ ይወጣል በሚል ተስፋ ሲጠብቁ የቆዩ የአካባቢው ነዋሪዎች ሁኔታው ተስፋ አስቆራጭ ሆኖብናል ይላሉ።
‹‹በየጊዜው ይወጣል ተባልን 52 ዓመታት ሳይወጣ ተደብቆ ቀረ የአካባቢው ማኅበረሰብም ለማይወጣ ነገር ለምን ደጋግመው ይጠይቁናል እያለ ነው።»
በወቅቱ ፋልከም ፔትሮ ኢንተርናሽናል በለገሂዳ ወረዳ ጎናና አካባቢ አጥንቶ ሲወጣ ተጨማሪ ሀብት አሰባስቦ ወደ ሥራ ሊገባ ነበር የሚሉት የለገሂዳ ወረዳ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ በላይ አያሌው ጥናቱ ከዚህ ቀደም በተገቢው መንገድ በመሠራቱ እሱን መመልከት በቂ ነው ይላሉ።
«ሌላ ሀብት አሰባስቦ ሊመጣ ነው እንጂ የወጣው ፋልከን የተሰኘው ድርጅት ከአሁን በፊት አጥንቶ ጨርሷል ወረኢሉም ለገሂዳም ቦናና ት/ቤት እንዳይሠራ አግዷል። ፌዴራል መንግሥትም የወጣበትን ሁኔታ ሲያስረዳ ጠፍቶ እንደሄደ ነው በትክክል ጥናቱን ጨርሶ ነው የሄደው።››
ጥናቱን ያጠናዉ ፋልከን ፔትሮ ተመልሶ አልመጣም
በአካባቢው ከሰሞኑ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በስፋት ሲያነጋግር የነበረው የለገሂዳ ወረዳ የነዳጅ ዘይነት ሀብትን ለመመልከት ከማዕድን ሚኒስቴር፣ ከአማራ ክልል ማዕድን ቢሮ፣ ከጂኦሎጂካል ሰርቬይ፣ ከወሎና አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ባለሙያዎች በስፍራው ተገኝተው ሀብቱ ያለበትን ሁኔታ ተመልክተዋል። ይሁን እንጂ በነዳጅ ዘይት ሀብት ዙሪያ ምንም ማለት አልፈለጉም። የወሎ ዩኒቨርስቲ ግን በፈረንጆቹ የጊዜ ቀመር በ2019 በስፍራው ተገኝተው የሥራውን ጥናት ይፋ ሲያደርግ በአካባቢው የነዳጅ ዘይት መኖሩን አረጋግጫለሁ ብሏል።
‹‹ናሙና ወስዶ ወሎ ዩኒቨርስቲ በሰኔ 2019 በፈረንጆቹ አቆጣጠር ነዳጅ ነው አይደለም በሚል ዙሪያ ሲምፒዚየም ነበረው፤ እኛም ተገኝተን ነበር፤ ነዳጅ መሆኑን ታውቋል።››
የደቡብ ወሎ ዞን ማዕድን ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ አበባው የነዳጅ ሀብቱ በአካባቢው መኖሩ ቀድሞም የሚታወቅ ቢሆንም ዘርፉ ተደጋጋሚ ጥናት የሚጠይቅ በመሆኑ ሰፊ ሥራዎች በመንግሥት በኩል እየተሠራ ነው ሲሉ ይገልፃሉ።
‹‹በፊትም ማዕድን መኖሩ ይታወቃል። አሁን እኛ የምንፈልገውሥራ ነው፤ ማዕድን መኖሩ ዱሮም ይታወቃል፤ ተጠንቷል። አሁን መንግሥት የራሱን ሥራ እየሠራ ነው። ውጤቱን ቀስ ብለን የሆነ ውጤት ላይ ስንደርስ የምናሳውቀው ይሆናል።››
ኢሳያስ ገላው
ሸዋዬ ለገሠ
አዜብ ታደሰ