1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ከምርጫ በፊት ሰላም እንዲሰፍን ፣የታሰሩ ፖለቲከኞች እና ጋዜጠኞች እንዲፈቱ ተጠየቀ

ረቡዕ፣ ኅዳር 10 2018

የ5 ፓርቲዎች ስብስብ የሆነው «ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት» የተሰኘው ቅንጅት ከመጭው ምርጫ በፊት የኢትዮጵያ መንግስት በሀገሪቱ ሰላም እንዲያሰፍን ጠየቀ። ትብብሩ ያለፈው ሰኞ ባወጣው መግለጫ የታሰሩ ፖለቲከኞች እና ጋዜጠኞች እንዲፈቱም ጠይቋል። መንግስት ለዚህ ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጥም ትብብሩ ቀነ ገደብ አስቀምጧል።

ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ምስረታ
ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ምስረታምስል፦ Solomon Muchie/AA

ከምርጫ በፊት ሰላም እንዲሰፍን ፣የታሰሩ ፖለቲከኞች እና ጋዜጠኞች እንዲፈቱ ተጠየቀ

This browser does not support the audio element.

የ5 ፓርቲዎች  ስብስብ የሆነው  «ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት» የተሰኘው ቅንጅት ከመጭው ምርጫ በፊት የኢትዮጵያ መንግስት በሀገሪቱ ሰላም እንዲያሰፍን እንዲሁም  ጠየቀ። ትብብሩ  ያለፈው ሰኞ ባወጣው መግለጫ የታሰሩ ፖለቲከኞች እና ጋዜጠኞች  እንዲፈቱም ጠይቋል። መንግስት ለዚህ ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጥም ትብብሩ ቀነ ገደብ አስቀምጧል።

የ5 የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች  ስብስብ ማለትም ኢሕአፓ፣ መኢአድ፣ እናት፣ አኢዴፓ እና አግን የመሰረቱት «ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት» የተሰኘው ቅንጅት «ምርጫ የዴሞክራሲያዊ ሂደት ማሳለጫ እንጂ የይስሙላመርሐ ግብር ማሟያ ሊሆን  አይገባም! » በሚል ያለፈው ሰኞ ባወጣው መግለጫ ፤  ከመጭው ምርጫ በፊት የኢትዮጵያ መንግስት በሀገሪቱ ሰላም እና መረጋጋት እንዲያሰፍን ጠይቋል።መግለጫውን በተመለከተ ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው የትብብሩ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጌትነት ወርቁ እንደገለፁት የሀገሪቱ የፖለቲካ የስልጣን ሽግግር በሰላማዊ እና ሕጋዊ መንገድ መደረግ አለበት ብሎ ትብብሩ ያምናል። ምርጫ ካሉት ሰላማዊ አማራጮች ውስጥ የተሻለ ነው በሚል እምነትም አለው ብለዋል።ያም ሆኖ ግን ምርጫ ለይስሙላ ሳይሆን ለውጥ የሚያመጣ መሆን አለበት ይላሉ።

ስለሆነም ምርጫን ለውጥ በሚያመጣ እና በአግባቡ ለማከናወን  በመንግስት በኩል መደረግ ያለበት ያሏቸውን መሠረታዊ  ጉዳዮች መኖራቸውን አስረድተዋል። ከነዚህም መካከል ቀዳሚው  ሰላም በመሆኑ፤ ከምርጫ በፊት የሀገሪቱ  ሰላምና ፀጥታ የተረጋጋ እንዲሆን አቶ ጌትነት አመልክተዋል።ከሰላም እና ፀጥታ ባሻገር በየእስር ቤቱ  ይገኛሉ ያላቸውን  የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ እና በምርጫ ሂደቱ በነፃነት እንዲሳተፉ ትብብሩ ጠይቋል።

ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነትን የመሰረቱት የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ እናት ፓርቲ፤ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፣ አንድ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ እና አማራ ግዮናዊ ንቅናቄ ናቸው።ምስል፦ Solomon Muchie/AA

እንደ ሕዝብ ግንኙነቱ ገለፃ ምርጫውን  በነጻነት እንዲዘግቡ የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት ሊረጋገጥ እንዲሁም የታሰሩ ጋዜጠኞችም ከ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ በፊት ሊፈቱ ይገባል።በዚህ ሁኔታ የምርጫ የጊዜ ሠሌዳው በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሕዝብ ይፋ ከመደረጉ አስቀድሞ ወይም ደግሞ እስከ ኅዳር ወር መጨረሻ ሳምንት ድረስ መንግሥት ትብብሩ  የጠየቃቸውን ሦስት ጉዳዮች ተግባራዊ በማድረግ ለምርጫው ምቹ  ሁኔታ እንዲፈጠር አሳስበዋል፡፡ ይህ ካልሆነስ  የትብብሩ ቀጣይ እርምጃ ምን ይሆናል? በሚል ዶቼ ቬለ ላቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱም ፤« አንድ ነገር ማድረግ አንፈልም በእርግጠኝነት መቶ አንድ ከመቶ የማውቀው የመንግስት አጃቢ ሆነን  ሀገር ትቀጥል ብለን በ2013 እንዳደረግነው በትከሻችን ተሸክመን እንዳሳለፍነው በ2018 ማለትም በሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ማሟያ ሆነን አንቀጥልም።»በማለት ገልፀዋል። የትብብሩን ቀጣይ እርምጃ በቀጣይ ለህዝብ እናሳውቃለን ብለዋል።
የትብብሩን መግለጫ  በተመለከተ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት እና የምርጫ ቦርድን ሐሳብ ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሐይ ጫኔ
ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW