1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ከምያንማር መውጪያ ያጡት ኢትዮጵያውያን

ሐሙስ፣ መጋቢት 18 2017

በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በሚላኩ አማላይ የውጭ ሀገር የሥራ ዕድሎች ተታለው ወደ ምያንማር የተወሰዱ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችና ቤተሰቦቻቸው ዛሬም የድረሱልን ድምፃቸውን እያሰሙ ነው። ለሥራ ነው በሚል በርካታ ዶላር ከፍለው ወደ ታይላንድ ተጉዘው መዳረሻቸው ምያንማር የሆነባቸው ወጣቶች ሕይወታችን ለአደጋ ተጋልጧል ይላሉ።

በአማላይ የሥራ ዕድል ተጭበርብረው ከተለያዩ ሃገራት ምያንማር በአጋቾች እጅ የተሰቃዩ
በአማላይ የሥራ ዕድል ተጭበርብረው ከተለያዩ ሃገራት ምያንማር በአጋቾች እጅ ሲሰቃዩ ቆይተው ነጻ ከወጡት ገሚሱ ወደየሃገራቸው ከመላካቸው አስቀድሞ ታይላንድ እንዲገቡ ተደርዋል። ምስል፦ Chalinee Thirasupa/REUTERS

ከምያንማር መውጪያ ያጡት ኢትዮጵያውያን

This browser does not support the audio element.

 

ከሀገር የወጣሁት በቴሌግራም በተለቀቀ አጓጊ የሥራ ማስታወቂያ ነው ትላለች አሁን ምያንማር በወታደሮች የጦር ሰፈር ውስጥ በሚያሳቅቅ ሁኔታ ላይ ያለችው ወጣት። ስሟን መግለፅ ያልፈለገችው ኢትዮጵያዊት እንደሌሎቹ በኢንተርኔት የማጭበርበሩ ሥራ ይከናወንበታል በሚባለው እሷን መሰል በርካታ የውጭ ዜጎች ተገደው በሚሠሩበት ስፍራ እንደ ዕድል ሆኖ ብዙ አልቆየችም። አሁን ያሉበትን ሁኔታ ግን አስከፊ ትለዋለች።

ሌላው ወጣት አንድ ዓመት አልፎታል። ተታልሎ በተወሰደበት ስፍራ ይፈጸምባቸው የነበረውን ጫና እና እንግልት ተቋቁሞ ዛሬ ደርሷል። ከአጋቾቻቸው ባስጣሏቸው የወታደሮች የጦር ሰፈር ከአንድ ወር በላይ ቆይቷል። እሱ ባለበት ስፍራ ብቻ ከ400 በላይ ኢትዮጵያውያን እንዳሉም ይናገራል።

ምያንማር ግዛት መሆኑን እንዲሁም የጦርነት ቀጣና እንደሆነ ከሚያውቁትውጪ ያሉበት አካባቢ የት ነው የሚለውን መግለጽ አልቻለም። የጦር ቀጣና እንደመሆኑ ሆን ተብሎ ካርታው ሳይሰወራቸው እንዳለቀረ ግን ገምቷል። የጦርነት ቀጣናነቱ ዋናው ስጋታችን ነው ይላል። ከዚህ ስፍራ በቶሎ ለመውጣት የመጓጓዣ ወጪ ቢያስፈልግም እነሱም ሆነ ቤተሰቦቻቸው አልቻሉትም ባይ ነው።

የተቀናጀው ወታደራዊ ዘመቻ

ከሳምንታት በፊት ነው የአካባቢው ሃገራት ከምያንማር መንግሥት ወታደሮች ጋር በትብብር የተለያዩ ሃገራት ዜጎችን አግተው በኢንተርኔት የማጭበርበር ተግባር ይፈጽማሉ ባሏቸው ማጎሪያ ስፍራዎች ላይ  የኃይል እርምጃ ወስደው በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩትን ማስለቀቃቸው የተነገረው። የውጭ ሃገራት ዜጎቹ ሲሰቃዩበት ከነበረው ስፍራ ቢወጡም ወደ የሀገራቸው መሄድ ባለመቻላቸው በመጠለያ ድንኳኖች ውስጥ በችግር ላይ እንደሚገኙ ነው ዘገባዎች ያመለከቱት።

በወታደሮች የጦር ሰፈር ምያንማር ውስጥ የሚገኘው ወጣትም ያሉበትን የጤናን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ተናግሯል።

ምያንማር በአጋቾች እጅ የሚሰቃዩትን ለማውጣት ከተሰማሩ ወታደሮች በከፊልምስል፦ STR/AFP

የቤተሰቦች የስጋት ድምፅ

በዚህ ስፍራ ቤተሰቦች እንዳሏቸው ለዶቼ ቬለ የገለጹ ወገኖች ወጣቶቹን ወደ ሀገራቸው በመመለሱ ሂደት መንግሥት እንዲረዳቸው ጥያቄ እያቀረቡ ነው። ልጃቸው ወደዚያ ከሄደ ዓመት ከሰባት ወር መሆኑን የተናገሩት እናት በተደጋጋሚ ወደ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ተሰባስበው በመሄድ አቤቱታ ማቅረባቸውን ይገልጻሉ። በትናንትናው ዕለትም ወደ ውጪ ጉዳይ ተሰባስበው ሄደዋል። የእሳቸው ልጅም ሆነ ሌሎች ከእገታው የተረፉት ለርሃብ ጭምር መጋለጣቸውን ነው የሚናገሩት።

እሳቸው እንደሚሉት አንድ ሺህ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በዚህ ሁኔታ ምያንማር ውስጥ ይገኛሉ። 138 የሚሆኑት ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ መንግሥት እና በአንዳንድ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ ወደ ሀገር ቤት መመለስ እንደቻሉም አክለዋል።

ወንድማቸው በዚህ አታላይ የሥራ ማስታወቂያ አማካኝነት ታይላንድ ሥራ አለ ተብሎ ከሀገሩ ከወጣ ዘጠን ወር ሆነው ያሉት አንደኛው ቤተሰብ፤ ወንድማቸው በአጋቾቹ እጅ ሳለ 5 ሺህ ዶላር እንዲያመጣ ተጠይቆ እየተደበደበ ብዙ መሰቃየቱን፤ በኋላም ገንዘቡ እንደተከፈለ ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል። አሁን በግዳጅ ከሚሠራበት ወጥቶ በወታደሮች የጦር ሰፈር እንዳለና፤ በዚያ ደግሞ በቂ ምግብ እንኳን አያገኙም ባይነው። ትናንት ወደ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በሄዱበት ጊዜ የተሰጣቸው ምላሽ ግን ተስፋ የሰጣቸው ይመስላል። 

የታጋቾቹ መጻኢ ዕጣ

ምንም እንኳን በርካቶች ከተጠቀሰው በኢንተርኔት የማጭበርበር ተግባር የተሰማራ አጋች ቡድን ቢወጡም አሁንም በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ የተለያየ ሃገራት ዜጎች የሚገኙባቸው ቦታዎች እንዳሉ ነው ሮይተርስ የዘገበው። እንደዘገባው ታይላንድን ጨምሮ የአካባቢው ሃገራት በእነዚህ ስፍራዎች ላይ በሚካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ በመሳተፍ ላይ ናቸው። በዘመቻውም ከእገታው ነጻ ከወጡት መካከል ከትናንት በስተያ 207 የፊሊፒንስ፤ ማሌዢያ፤ የኔፓልና እና ካምቦዲያ ዜጎች ወደየሃገራቸው መሸኘታቸው ተገልጿል። አሁንም ግን ኢትዮጵያውያኑን ጨምሮ ብዙዎች በምያንማር የወታደር ጦር ሰፈር ውስጥ መሄጃ አጥተው እንደሚገኙም ዘገባው አመልክቷል።

ሸዋዬ ለገሠ

ፀሐይ ጫኔ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW