1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከሰላም ስምምነቱ ቦኋላ በመቐለ እየተነቃቃ ያለው የሰርከስ ስፖርት

ቅዳሜ፣ ጥር 20 2015

"ብዙ ሀገራት እየተዘዋወርኩኝ ሰርቻለሁ። በሰላሙ ግዜ በጣልያን እና ስፔን ስራዎቻችን አቅርበን ነበር። ብዙ ተስፋ ነበረን። በማህል የተጀመረው ግን የነበረን ተስፋ እንድናጣ ነው ያደረገን"

Äthiopien | Tigray-Zirkusteam
ምስል Million Hailesillassie/DW

ከሰላም ስምምነቱ ቦኋላ በመቐለ እየተነቃቃ ያለው የሰርከስ ስፖርት

This browser does not support the audio element.


በትግራይ ተወዳጅና ተዘውታሪ ከሚባሉት ስፖርቶች መካከል አንዱ ሰርከስ ነው። በመቐለ የሚገኙ ፕሮፌሽናል የሰርከስ አርቲስቶች ባለፊት ሁለት የጦርነት ዓመታት ከእንቅስቃሴ ውጭ ሆነው እንደቆዩ ይገልፃሉ። አሁን የተፈጠረው የሰላም ዕድል ተጠቅመው ደግሞ ወደ ሚወዱት ስፖርት የተመለሱ ሲሆን በተለያዩ መድረኮች ትርኢቶቻቸው ለማሳየት ደግሞ ጠንክረው እየሰሩ ስለመሆኑ ይናገራሉ። ሰርከስ መቐለ በተባለ ቡድን ታቅፈው የሚሰሩ ወጣቶችን አነጋግረናል።

ለሁለት ዓመታት በትግራይ የተደረገው ጦርነት የመላው ህዝብ በተለይም የወጣቶች ህይወት በጅጉ የፈተነ ነበር። ጦርነቱ በትግራይ የሰርከስ ትርኢት በማቅረብ የሚታወቁ ወጣቶች ህልም፣ ምኞትና እቅድ አደናቅፏል፣ ከሚወዱት ሙያቸውም ለይቷቸዋል። በትግራይ ካሉ ታዋቂ የሰርከስ ቡድኖች መካከል የሆነው እና ከ10 በላይ ዓመታት በዘለቀው ሰርከስ መቐለ አባል የሆነችው ወጣት ስፖርተኛ ፍዬሪ ተኽሉ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት በሰርከስ ስትቆይ፣ በተለይም ከጦርነቱ በፊት በነበሩ ግዜያት በርካታ ስኬቶች አስመዝግባለች። ፍዬሪና ሌሎች የሰርከስ መቐለ አባላት በስፔንና ጣልያን ጨምሮ በተለያዩ የዓለም ሀገራት እየተዘዋወሩ የሰርከስ ትርኢት ያቀረቡ፣ በዚህም በርካታ አድናቂዎች ያፈሩ ሲሆን፤ ጦርነቱ እንዲሁም ተከትሎት የመጣ መዘጋጋት ግን ከስፖርቱ ለይቷቸው፣ ከስራቸው ገትቷቸው እንደቆየ ይናገራሉ። 

ምስል Million Hailesillassie/DW

"ብዙ ሀገራት እየተዘዋወርኩኝ ሰርቻለሁ። በሰላሙ ግዜ በጣልያን እና ስፔን ስራዎቻችን አቅርበን ነበር። ብዙ ተስፋ ነበረን። በማህል የተጀመረው ግን የነበረን ተስፋ እንድናጣ ነው ያደረገን" የምትለው ፍዬሪ  አሁን ላይ ጦርነቱ ቆሞ ሰላም መስፈኑ ደስታ እንደፈጠረባት ትናገራለች።  ያለፈው ግዜ ለማካካስ  በሳምንት ስድስት ቀናት ልምምድ እንደሚያደርጉ የምትናገረው ፍዮሪ በቅርቡ ወደ ቀድሞ ሁኔታዋ ልትመለስ፣ ስራዎችዋ በዓለም መድረክ ልታቀርብ እየተዘጋጀች መሁኗን ገልጻለች።

ዮሃንስ ተስፉ ሌላው የሰርከስ መቐለ አባል ነው። ሰርከስ የምወደው ስፖርት ብቻ ሳይሆይ ራሴን እና ቤተሰቤን የማስተዳደርበት የገቢ ምንጬ ጭምር ነው የሚለው ዮሃንስ፥ ያለፈው የጦርነት ግዜ እንዲሁም ከጦርነቱ በፊት የነበረው የኮረና ቫይረስ ስጋት ያስከተለው መከርቸም ከሚወደው ሰርከስ እንዲርቅ፣ መተዳደሪያ ገቢው እንዲያጣ፣ ህልምና ስኬቶቹ እንዲገደቡ አድርጎት እንደቆየ አጫውቶናል።

ምስል Million Hailesillassie/DW

ዮሃንስ "በሰላሙ ግዜ በአውሮፓ የተለያዩ ሀገራት ትርኢት አቅርበናል። ብዙ አድናቂዎች አፍርተን ነበር። ነገሩ የተበላሸው ጦርነቱ ሲጀመር ነው። ብዙ ነገር አጥተናል። አይደለም የተለያየ ሀገር እየተዟዟርን ትርኢት ልናሳይ በአግባቡ ትሬኒንግ መስራት አልቻልንም፣ ሙሉ በሙሉ ከእንቅስቃሴ ውጭ ሆነን ነው የቆየነው" ይላል። በዚህም የነበሩ የስራ ዕድሎች ማጣታቸው፣ ከሙያው ርቀው መቆየታቸው የሚናገረው ዮሃንስ "አሁን ሰላም የሆነ ይመስላል፣ ይህ ለኛ መልካም ዕድል ነው። ሁኔታው ተጠቅመን ጠንክረን እየሰራን ነው። ሁሉም የሰርከስ ባለሙያ በአዲስ መንፈስ ነው እየሰራ ያለው" ይላል።

በመቐለ በሚገኘው የሰርከስ መቐለ የስልጠና ማእከል በነበረን ቆይታ እንደተመለከትነው በርካታ ህፃናት እና ወጣቶች በጦርነቱ ምክንያት አቁመውት የነበረ ስፖርት ዳግም ጀምረው ወደ ቀድሞ ብቃታቸው ለመመለስ ይጣጣራሉ፣ የተገኘው የሰላም ዕድል ተጠቅመው ብቃታቸው ለማሳየት ጠንክረው ይሰራሉ። የሰርከስ መቐለ ዳይሬክተር ዮሃንስ ኢታይ ቀንሶ የነበረ የስፖርተኞች ቁጥር አሁን አሁን እየጨመረ ስለመምጣቱ የሚገልፅ ሲሆን "በቀን በሶስት ሽፍት 150 አባላት በሰርከስ መቐለ ታቅፈው ይሰራሉ" ብሎናል። 

ምስል Million Hailesillassie/DW

በመዘጋጋቱ ምክንያት "ከተቀረው ዓለም ጋር የምንገናኝበት ዕድል አልነበረም፣ ትራንስፖርት አልነበረም። ይህ የሰርከስ አርቲስቱ ጎድቶት ቆይቷል" የሚለው የሰርከስ መቐለ ዳይሬክተር ዮሃንስ ኢታይ አሁን ነገሮች መስተካከላቸው ሁሉም በተስፋ እንዲሰራ እንዳደረጉት ይገልፃል። በቅርቡ በትግራይ የግንኙነት መስመር መከፈቱ እንዲሁም የትራንስፖርት አገልግሎት መጀመሩ ተከትሎ የሰርከስ ቡድኑ አባላት የሆነው ወጣቶች ስራቸው ለማቅረቅ ወደ ተለያዩ ሀገራት መጓዛቸውም ጨምሮ ገልጿል። 

ጦርነቱ አብቅቶ የሰላም ስምምነት ከተደረሰ በኃላ ከሰርከስ መቐለ በተጨማሪ ሌሎች በትግራይ ታዋቂ የሚባሉ የሰርከስ፣ ማርሻል አርት፣ ብስክሌት ቡድኖች ከሁለት ዓመት በኃላ ወደ እንቅስቃሴ እየተመለሱ ይገኛሉ።
ሚልዮን ሃይለስላሰ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW