1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከሱዳን እስከ ቻድ፦ የስደተኞቹ መከራ

ቅዳሜ፣ ኅዳር 14 2017

ከጦርነት እና ትርምስ መሀልr በርካታ ሱዳናውያን ተስፋ ቆርጠው ወደ ድሃዋ ቻድ እየተሰደዱ ነው ። ቻድ በዓለም ውስጥ ካሉት ግዙፍ ቀውሶች አንዱ የሚታይባት ናት ። በሱዳን እና ቻድ ድንበር ላይ የስደተኞቹ ሁኔታ እጅግ አስቸጋሪ መሆኑ ተገልጧል ። የሱዳን የርስ በርስ ውጊያ አስከፊነቱ ቀጥሏል ።

Tschad | Menschen auf der Flucht vor der Gewalt in West Darfur
ምስል Zohra Bensemra/REUTERS

የሱዳን ጦርነት ዳፋው ነዋሪዎቹ ላይ በርትቷል

This browser does not support the audio element.

እንደምንም መከራውን አምልጣ ከለላ ወደምታገኝበት ቦታ ደርሳለች ። ማሪያም ጉልበቷ እየተብረከረከ፥ የቻድን ድንበር ተሻግራለች ። በጦርነት ከምትታመሰው ሱዳን አምልጣ ነው ቻድ መግባቷ ። አሁን ያላት ቁስ በትንሽዬ መኪና ላይ የተሸከፈው ብቻ ነው ። ለወጣቷ እናት ሲዖሉ ከበስተጀርባዋ ቀርቷል ። ስለዚያ ግን ብዙም መናገር አትሻም ።

«የፈጣሪ ያለህ፥ መላ ሀገሪቱ ወድማለች ።»

ማሪያም ለስደት የተዳረገችበት ሱዳን እስከ አፍንጫቸው በታጠቁ ሁለት ጄኔራሎች በሚመሩ ጦሮች ትታመሳለች፥ በሱዳን ጦር ሠራዊት እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ (RSF) ። ካለፈው ዓንድ ዓመት ከሰባት ወር አንስቶ ሱዳን በሁለቱ ጦሮች የርስ በርስ ውጊያ የተነሳ በርካቶች ለሽብር እና ሰቆቃ ተዳርገዋል ። በርካታ መንደሮች ወደ አመድነት ተቀይረዋል ። እናቶች ከሴቶች ልጆቻቸው ጋር ተደፍረዋል፣ አውድማው እና ከብቱ ሁሉ ጠፍቷል ። ወንዶቹ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል ። ወንዶች ልጆች ደግሞ ለግዳጅ ውትድርና ታፍነው ተወስደዋል ። በቃላት ሊገለጥ የማይችል መከራ ሱዳናውያን ላይ እየደረሰ ነው ። ፍጻሜውም የሚታይ አይመስልም፦ ትላለች በቦታው ሁኔታውን የታዘበችው የዶይቸ ቬለዋ ካትሪና ክሮል ።

ወደ ድህነት ሽሽት

አድሬ በቻድ እና በሱዳን ድንበር መካከል የምትገኝ ወሳኝ ትንሽዬ ከተማ ናት ። በሱዳን ድንበር በኩል ሦስት የታጠቁ ወታደሮች ቆመዋል ። ከፊት ለፊታቸው የድንበር መለያው ድንበር ተገሽሯል ። ስደተኞቹ ወታደሮቹ ጋር ሳይደርሱ በጥንቃቄ ያልፋሉ ። እዚህ የማንም ባልሆነው ሥፍራ ላይ አንድ የወደመ ድልድይ ይገኛል። ። ድልድዩ በደንብ የተገነባውን መንገድ የሚያገናኝ ነበር፥ በሁለቱ ጎረቤታም አገራት መካከል ንግዱ እንዲያብብ በማሰብም ነበር የተገነባው ። የሆነው ግን ሌላ ነው ። በቀይ አፈሩ መንገድ በየቀኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ድንበሩን እየተሻገሩ ይነጉዳሉ ።

ጦርነቱ በሱዳን በበረታ ቁጥር ድንበሩን የሚያቋርጡ ሰዎች ቁጥርም ይጨምራል ። ዐሥራ አንድ ሚሊዮን ሱዳናውያን አገር ጥለው ተሰድደዋል ። አብዛኞቹ እዛው ሱዳን የተፈናቀሉ ናቸው ። ቻድ እስካሁን 1,1 ሚሊዮን ስደተኞችን ተቀብላለች ። ለድሀዪቱ የዓለማችን አገር ቻድ ተጨማሪ ጫና ። በዚያ ላይ አገሪቱን የከባቢ ዐየር ለውጥ በብርቱ ጎድቷታል ።  እጅግ ብርቱ ከሆነው ድርቅ ጋር ያልታሰበ የጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋም ተከስቶባታል ። እዚህ ከእያንዳንዱ ሦስት ነዋሪ አንዱ በከፋ የድህነት አረንቋ ውስጥ ይማቅቃል ።

ከመቶ ሺዎቹ አንዷ፦፡ ማርያም ከሱዳን ሸሽታ አድሬ ደርሳለች ምስል Katharina Kroll/DW

«እያንዳንዱ አገር እዚህ እንዳለው የስደተኛ ብዛት ይጨናነቅ ነበር»

ማርያም በመጀመሪያ አድሬ ውስጥ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር (UNHCR) የስደተኞች መቀበያ ሥፍራ ትመዘገባለች ። ከዚያ ደግሞ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ወደ ሚገኘው መሸጋገሪያ የመጠለያ ጣቢያ ትሄዳለች ።  እዚያ አምስት ልጆቿ ይጠብቋታል ። እናቲቱ መምጣት የቻለችው ገና አሁን ነው ። አድሬ በእርግጥ 40,000 ነዋሪዎች ያሏት ትንሽዬ ከተማ ናት ።  በአሁኑ ወቅት የስደተኞች ጊዜያዊ መጠለያ ሆናም ታገለግላለች ። እዚህች ትንሽዬ ከተማ ውስጥ 230,000 ሰዎች ይኖራሉ ። በጊዜያዊ የላስቲክ ሸራዎች የተወጠሩ መጠለያዎች እስከ አድማሱ ዳርቻ ድረስ ተዘርግተዋል ። እዚህ ያሉት ሴቶች እና ልጆች ብቻ ናቸው ማለት ይቻላል ።

የጀርመን የልማት ሚንሥትር ስቬን ሹልትሰ ወደዚህ ድንበር ተጉዘዋል ። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በዓለም ትልቁ እና በፍጥነት እያደገ ያለው የስደተኞች ቀውስ ሲል የሰየመውን ሥፍራ ትኩረት እንዲያገኝ ይሻሉ ።

«እያንዳንዱ አገር እዚህ እንዳለው የስደተኛ ብዛት ይጨናነቅ ነበር ይህም አንድ ክልል አለያም አገር ብቻውን አይችለውም ያም በመሆኑ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እዚህ ድጋፉን ማሳየት አለበት ቻድን በደንብ መደገፍ አለባቸው »

ለዚያም  ከጀርመን ተጨማሪ የ57 ሚሊዮን ዩሮ ርዳታ እንደሚኖር ሚንሥትሯ ቃል ገብተዋል ። ገንዘቡ ለአብነት ያህል የርዳታ ድርጅቶች ለረጅም ጊዜ ለኤሌክትሪክ ግንባታ እና የውኃ አቅርቦት ልማት የሚጠቀሙበት ነው ።

ቻድ የረዝም ጊዜ አምባገነን መሪዋ ኢድሪስ ዴቢ በቅርቡ ያረፉባት አስቸጋሪ አጋር አገር ናት ትላለች የዶይቸ ቬለዋ ካትሪና ። ከሦስት ዓመት በፊት በ69 ዓመታቸው ፕሬዚደንቷ እንዳረፉ ልጃቸው ማሐማት ኢድሪስ ዴቢ የአገሪቱ ጊዜያዊ ወታደራዊ ምክር ቤት መሪ ሆነው ብቅ ብለዋል ።  በአጨቃጫቂው ምርጫ መንበረ ሥልጣኑን ባለፈው ሚያዝያ ወር የተቆናጠጡትም እኚሁ የ40 ዓመቱ ጎልማሳ ማሐማት ናቸው ። ቻድን በጠንካራ አምባገነን እጃቸው እየመሩ ነው። የተቃዋሚ አባላት እና ጋዜጠኞች ቻድ ውስጥ በአደገኛ ሁኔታ ነው የሚኖሩት ። የቻድ መንግሥት እጅግ አስፈላጊው እና የአገሪቱ የቀድሞ ቅኝ ገዢ ከሆነችው ስትራቴጂካዊ አጋሩ ፈረንሳይ በተጨማሪ በአዳዲስ አጋሮች እየተመካ ነው ። የተባበሩት ዓረብ ኢምሬትስ መንግስትን ብንወስድ ውድ ያልሆነ ብድር በመስጠት የበጀት ድጋፍም እያደረገች ነው ።

ሕይወትን መታደግ፦ በሱዳን እና በቻድ ድንበር ላይምስል Katharina Kroll/DW

ቻድ ድንበሯን ከሱዳን ለሚጎርፉ ስደተኞች ብቻ ሳይሆን ለጦር መሣሪያ ዝውውርም ክፍት ማድረጓ የአደባባይ ሐቅ ነው ይላሉ በኮንራድ አደንአወር ተቋም የሣኅል ቀጣና መርሐግብር ኃላፊው ዑልፍ ሌሲንግ ። «ሩስያ እና የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች የጦር መሳሪያ ማቀበላቸውን ማቆም አለባቸው» ቻድ ላይም የጦር መሣሪያ ማእቀብ መጣል አለበትም ሲሉ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል ።  ከዚያ በፊት የሚደረግ የሰላም ንግግር ዋጋ ቢስ ነው ሲሉም አስምረውበታል ።

የሚንሥትሮቹ መሐላ

የቻድ የውጭ ጉዳይ ሚንሥትር፦ አብደራማን ኩላማላህ ዋና ከተማዪቱ እንጃሜና በሚገኘው ጽ/ቤታቸው ደጃፍ ላይ ቆመዋል።  ከጀርመን ከመጡ እንግዶች ጋር አጠር ያለ ጋዜጣዊ መግለጫ እየሰጡ ነው ። አገራቸው ከቻድ ወደ ሱዳን ስለሚሻገረው የጦር መሣሪያ ዝውውር ምን እያደረገች ነው ተብለው ተጠይቀው ሚንሥትሩ በመሐላ ታጅበው መልስ ሰጥተዋል ።

«እኔ በግሌ ጦር መሣሪያ ወደዚያ የሚልክ አንድም አገር ዐላውቅም ያን ባውቅ ኖሮ ፈጣሪ በሚያውቀው ያን እናገር ነበር »

ከሚንሥትሩ ንግግር አፍታ ቆይታ በኋላ ባልዳል ዖያማታ፦ «ምን መልስ ጠብቀሽ ነበር ። ሚንሥትሩ ፍላጎታቸውን ነው የሚያስጠብቁት» ብለዋል ። ባልዳል ቻድ የሚገኘው የሰብአዊ መብቶች ሊግ ብሔራዊ አስተባባሪ ናቸው ። ሚንሥትሩ መንግሥታቸውን የሚተቹትን እንዴት ማስተናገድ እንደሚችሉ ነው በደንብ የሚያውቁትም ባይ ናቸው ።  «የስደተኞች ጉዳይ አንድ ነገር ነው፥ የፖለቲካ እና የወታደራዊ ፍላጎት ደግሞ ሌላ» ሲሉም አክለዋል ።

አድሬ 40,000 ነዋሪዎች ያሏት ትንሽዬ ከተማ ናት ።  በአሁኑ ወቅት የስደተኞች ጊዜያዊ መጠለያ ሆናም ታገለግላለች ። እዚህች ትንሽዬ ከተማ ውስጥ 230,000 ሰዎች ይኖራሉ ።ምስል Sam Mednick/AP

ከሞት ለመትረፍ አንዲት ትንሽዬ መሬት

በቻድ በስተምስራቅ፥ ከሱዳን ጋር በሚያዋስነው ድንበር  ላይ፥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የርዳታ ድርጅቶች ከሱዳን የመጡ ስደተኞችን ለረጅም ጊዜ ለማስተናገድ እየሞከሩ ነው። በመላ አገሪቱ 21 የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች አቋቁመዋል፥ እያንዳንዳቸው 50,000 ሰዎችን ያስተናግዳሉ ። በተሰነጣጠቀውና አቧራማ በሆነው መልክዓ ምድር ለመጠለያ ጣቢያዎቹ ግንባታ ተስማሚ ቦታዎችን ማግኘት በጣም ከባድ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ኮሚሽን (UNHCR) አባል ፒዬር ካሜራ ተናግረዋል ። ምክንያቱ ደግሞ፦ በአካባቢው አንዳችም አይነት መሰረተ ልማት አለመኖሩ ነውም ብለዋል ።

«እጅግ ፈታኝ ነው አንዳችም መሠረተ-ልማት የለም በእያንዳንዱ መጠለያ 50,000 ስደተኞችን ለማስተናገድ ከምንም ተነስቶ ነው የሚገነባው ብዙ ገንዘብ ያስወጣል እና ደግም በቂ ገንዘብ የለንም አፋጣኝ ድጋፍ ከሚያስፈልጋቸው ስደተኞች 29 ከመቶው ብቻ ነው ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የገንዘብ ድጋፍ ቃል የተገባው ለስደተኞቹ የኑሮ ሁኔታቸውን ክብር በማይነካ መልኩ ለማቅረብ በቂ አይደለም»

የተባበሩት መንግስታት የርዳታ ድርጅቶች ከቻድ መንግስት ጋር በቅርበት እየሠሩ ነው። ስደተኞች በመጠለያ ጣቢያው ዙሪያ የራሳቸውን ምግብ ማምረት እንዲችሉም መሬት ይሰጧቸዋል ። የዓለም ምግብ መርሐ-ግብር (WFP) ምክትል ኃላፊ አሌክሳንደር ሌ ኩዚያት ስደተኞቹ ተስፋቸው እንዲለመልም ይሻሉ ።

የጀርመን የልማት ሚኒስትር ስቬንያ ሹልሰ የቻድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብደራማን ኩልማላህን በጎበኙበት ወቅትምስል Katharina Kroll/DW

«አዲስ ሕይወት መገንባት የሚችሉበትን መንገድ መፈለግ ለእኛ ወሳኝ ነው በወር በሚሰጣቸው ዳረጎት ብቻ እንዲወሰኑ አንሻም የሚያለሙት መሬት እንዲሰጣቸው፤ አትክልቶችን ተክለው በዚያ ገቢ እንዲያገኙ ድጋፍ እናመቻቻለን »

ሐሳቡ ዕውን እንዲሆንም በስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ዙሪያ የሚገኙ ማኅበረሰቦችም ተጠቃሚ መሆን አለባቸው ። የምግብ ተክሎችን ለማምረት ሁኔታው ሊመቻችላቸው ይገባል ። ያም እዚያ ባለው ትንሽ ነገር የሚፈጠር ውጥረትን ለማስወገድ ይረዳል ሲሉም አክለዋል ኃላፊው ።

ለመመለስ ተስፋ

የጀርመን የልማት ሚንሥትር ስቬን ሹልትሰ በጉብኝታቸው ወቅት፦ «በሚያሳዝን ሁኔታ  ወደ ሱዳን መመለስ ለአብዛኞቹ ስደተኞች በቅርቡ ዕውን እንደማይሆን መገመት አለበት» ብለዋል ። በእርግጥ ሰብአዊ ርዳታም ቢሆን በዘላቂነት መፍትሄ አይደለም ። «ለዚህም ነው ለስደተኞች እና ስደተኛ ተቀባይ ማኅበረሰቦች መሬት መስጠት እና መስኮችን ለተክል እና ለግጦሽ ዳግም ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ» እጅግ አስፈላጊ የሆነው ። ማንኛውም ለም መሬት ያለው የዕለት ጉርሱን ለራሱ ማቅረብ ይችላል » ብለዋል ።

ማርያም አሁን ቻድ ውስጥ በእሷ እና በቤተሰቧ ላይ የሚሆነውን ማየት አለባት ። በአንድ ወቅት ወደ አገሯ ሱዳን የመመለስ ተስፋዋን ግን አላጨለመችም ።  ትልቁ ምኞቷም ያ እንደሆነ ተናግራለች ። የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት ግን ማብቂያው መቼ ይሆን?

ካትሪና ክሮል/ ማንተጋፍቶት ስለሺ 

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW