1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ከሱዳን የ42 ሃገራት ተፈናቃዮች በኢትዮጵያ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 24 2015

ከሦስት ሳምንት በፊት ሱዳን ውስጥ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ሽሽት ከ6 ሺህ በላይ የሚሆኑ የ42 አገር ዜጎች ተፈናቅለው ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ መግባታቸው ተገለጠ ። የውጭ ሃገራት ተፈናቃዮቹ ወደሚፈለጉበት አካባቢ መሸኘታቸውንም በአማራ ክልል የምዕራብ ጎንደር ዞን ዐስታውቋል ። ከተፈናቃዮቹ መካከል 900 የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ናቸው ተብሏል ።

Äthiopien l Metema in der Amhara Region
ምስል፦ Alemnew Mekonnen

ከሱዳን የ42 ሃገራት ተፈናቃዮች ኢትዮጵያ ገብተዋል

This browser does not support the audio element.

ከሦስት ሳምንት በፊት ሱዳን ውስጥ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ሽሽት ከ6 ሺህ በላይ የሚሆኑ የ42 አገር ዜጎች ተፈናቅለው ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ መግባታቸው ተገለጠ ።  የውጭ ሃገራት ተፈናቃዮቹ ወደሚፈለጉበት አካባቢ መሸኘታቸውንም በአማራ ክልል የምዕራብ ጎንደር ዞን ዐስታውቋል ። ከተፈናቃዮቹ መካከል 900 የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ናቸው ተብሏል ። ተፈናቃዮች በየኬላው የቆሙ የሱዳን የፀጥታ አካላትና ኢትዮጵያ መዳረሻ ላይ ያሉ የሱዳን ዜጎች ያለ አግባብ ገንዘብ እየጠየቁን በመሆኑ «ምናለ መንግሥት ችግሩን ቢያይ» ሲሉ የኢትዮጵያ መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል ።

በጀነራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሀን በሚመራው በሱዳን ጦርና በጀኔራል ሞሀመድ ሐምዳ ዳጋሎ (ወይም በስፋት በሚታወቁበት ሔምዲቲ) በሚመራው ፈጥኖ ደራሽ ጦር መካከል ሱዳን ውስጥ የተቀሰቀሰው ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፣ በጦርነቱ ምክንያት በካርቱምና አካባቢው የነበሩ ሱዳናውያንናየበርካታ የሌሎች አገሮች ነዋሪዎች ከተማዋን እየለቀቁ ወደ ተለያዩ አገሮች እየተፈናቀሉ ነው ፡፡

ኢትዮጵያም ከሱዳን የተፈናቀሉ በርካታ ሰዎችን እየተቀበለች መሆኗን የምዕራብ ጎንደር ዞን አመልክቷል ፡፡ የዞኑ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ ፋንታሁን ቢሆነኝ የ42 አገር ዜጎች የሆኑ ከ6,000 በላይ ሰዎችም በምዕራብ ኢትዮጵያ በኩል መተማ ዮሐንስ ከተማ ገብተዋል፣ ወደሚፈልጉበት አካባቢም ተሸኝተዋል ብለዋል ፡፡ ሁኔታዎችን እየተከታተለ አስፈላጊ የሆኑ እገዛዎችን የሚያደርግ ግብረኃይል መቋቋሙን የሚናገሩት አቶ ፋንታሁን፣ እስከ 200 ተሸከርካሪዎች ተመድበው ተፈናቃዮቹን ወደሚፈልግበት ቦታ እያደረሱ እንደሆነም አመልክተዋል ፡፡

የአማራ ክልል መተማ ከተማ፦ ፎቶ ከክምችት ማኅደርምስል፦ Alemnew Mekonnen

ውጊያው ምናልባትም የሚቀጥል ከሆነ የጦርነቱ ሁኔታ በኢትዮጵያ ላይ ሊፈጥረው የሚችለውን ጫና ለመከላከል የቅድመ ሁኔታ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነም ኃላፊው አመልክተዋል ፡፡
ከሱዳን ተፈናቅለው መተማ ከደረሱት ተፈናቃዮች መካከል አንድ ኢትዮጵያዊ በመንገድ ላይ በየኬላዎች እያስቆሙ የሶዳን ፖሊሶች ከፍ ለገንዘብ ይወስዱብናል፣ ገላባት (ኢትዮ- ሱዳን ድንበር) ስንደርስም ለሻንጣ ማውረጃ በሚል በዐሥር ሺዎች የሚቆጠር የኢትዮጵያ ወይም የሱዳን ገንዘብ ይቀበሉናል ነው ያሉት ፡፡

ሀሚድ ካሊፋላ የተባሉ ተፈናቃይ «በየመንገዱ ፍተሻ» በሚል የቆሙ አንዳንድ የሱዳን የፀጥታ አካላት ሲፈልጉ ያስፈራሩሀል፣ ሲፈልጉ ይተኩሱብሀል፣ ሲፈልጉ ኬላ ያሳልፉሀል፣ ወይም ይከለክሉሀል፣ ያለህን ገንዘብም አንገራግረው ይቀበሉሀል» ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል ፡፡ ተፈናቃዮቹ መተማ እንደደረሱ በየብስ ወደ ጎንደር ከተማ ከተላኩ በኋላ በየሀገራቱ ኤምባሲዎች ድጋፍ እተደረገላቸው ወደ አገራቸው እንደሚላኩ የምዕራብ ጎንደር ዞን የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊው አቶ ፋንታሁን ቢሆነኝ ገልጸዋል ፡፡

ሱዳን ውስጥ በጀነራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሀንና በጀኔራል ሞሀመድ ሐምዳ ዳጋሎ (ሔምዲቲ)አለመግባባት አል ቡርሀን በሚመሩት የሱዳን ጦር ሰራዊትና ጀኔራል ዳጋሎ በሚመሩት የፈጥኖ ደራሽ ጦር መካከል በተፈጠረው ጦርነት እስካሁን ከ500 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የተለያዩ ዓለምአቀፍ ብዙሀን መገናኛ ድርጅቶች ዘግበዋል ፡፡

ዓለምነው መኮንን

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW