ከስማርት ስልክ ሱስ ለመውጣት የሚረዱ ሳይንሳዊ ዘዴዎች
ረቡዕ፣ ሐምሌ 30 2017
ወቅታዊ ዜናዎችን ለመመልከት፣ በበይነመረብ ግብይት ለማድረግ ወይም የጓደኛቻችንን ፎቶዎችን እና ቪዲዮዎችን ለመመልከት፣ ተንቀሳቃሽ ስልኮቻችንን በየጥቂት ደቂቃዎች መፈተሽ እና መመልከት የተለመደ ሆኗል። አብዛኞቻችን ያለ ተንቀሳቃሽ ስልኮቻችን የትም መንቀሳቀስ አንፈልግም። እናም በቀላሉ እና በፈቃደኝነት የእነሱ እስረኛ ያደርጉናል።በዚህ ሁኔታ የስማርት ስልኮች ሱስ በዓለም ዙሪያ በሁሉም የዕድሜ ክልል እና ሀገራት እየጨመረ ነው። ለምሳሌ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ፣ በቅርቡ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው ወደ 57% የሚጠጉ የጥናቱ ተሳታፊዎች የስልክ ሱስ እንዳለባቸው አምነዋል።
ይህ እያደገ የመጣው በስማርት ስልኮች ላይ ያለው ጥገኝነት ባለሙያዎች እንደሚሉት ለአእምሮም ሆነ ለአካላዊ ጤንነት ከፍተኛ አደጋን ይፈጥራል። ችግሩ እንቅልፍ መተኛት ሲገባን እንኳን ስልኮቻችን ያለማቋረጥ እንድንመለከት ይገፋፉናል።የሥነ ልቡና ባለሙያዋ ዶኒያ ቩዝ እንደሚሉት በዚህ ጊዜ አእምሮአችን በቂ እረፍት አያገኝም።
«በአእምሯችን ውስጥ ጥሩ ነገር ሲያጋጥመን የሚሸልሙን ስርዓቶች አሉን፣ ጣፋጮች፣ ምግብ፣ ጥሩ ፊልም ማየት፣ በፍቅር መያዝን የመሳሰሉ። በተንቀሳቃሽ ስልካችን ላይ የምናያቸው ብዙ መልክቶች እና ምስሎችም ተመሳሳይ ውጤት አላቸው። ነገር ግን በጊዜ ሂደት ይጠፋል። የሽልማት ስርዓታችን እየቀነሰ እና እየቀነሰ ይሄዳል።ስለዚህ የበለጠ እንፈልጋለን። በዚህ የተነሳ ሱሰኛ እንሆናለን።» ብለዋል።
የስልክ አጠቃቀም ሱስ የሚባለው ምን ደረጃ ላይ ሲደርስ ነው?
ከዚህ አንፃር የሰዎች አጠቃቀም ሱስ የሚባለው ምን ደረጃ ላይ ሲደርስ ነው? የሪኔሳንት/Renascent/ የአዕምሮ ጤና እና የሱስ ማገገሚያ ማዕከል መስራች የሆኑት የሥነ አእምሮ ባለሙያው ፕሮፌሰር ሰለሞን ተፈራ ከዚህ ቀደም እንዲህ ነበር የገለፁት።
«ሱስ ባጭሩ አራት መገለጫዎች አሉት።አራቱ «ሲ»ዎች ይባላሉ። በእንግሊዥኛ በ«ሲ» የሚጀምሩ አራት ቃላት አሉ።እነዚህ መገለጫዎች ናቸው,»ካሉ በኋላ «አንደኛው «ኮንትሮል» ነው።ቁጥጥር ማለት ነው።ባለን ባህሪ ፣ሱስ በተያዝንበት ልምምድ ላይ ቁጥጥር ማጣት ነው።,ሁለተኛው «ክሬቪግ»ሰቅዞ የሚይዝ ፍላጎት ነው።ልምምዱን የመደጋገም ጉጉት እና ፍላጎት ማለት ነው።ሶስተኛው «ኮምፐልሽን»በዚያ ተግባር ውስጥ በፈቃደኝነት ሳይሆን በከፍተኛ በውስጣዊ ግፊት መሰማራት ማለት ነው።» በማለት ገልፀዋል።
ቴክኖሎጅ በተለይም የስማርት ስልኮች የሰውን ልጅ የዕለተ ዕለት ኑሮ ለማቅለል፣ መረጃ ለማግኘት፣ ለመዝናናት፣ ለተግባቦት፣ለትምህርት፣ ከሰዎች ጋር ያለንን ግኑኙነት ለማሻሻል እና ስራን ውጤታማ ለማድረግ የላቀ ጠቀሜታ አላቸው።ከዚህ ጠቀሜታቸው አንፃር ፤ የሞባይል ስልክ ባለቤትነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱን መረጃዎች ያሳያሉ።በጎርጎሪያኑ 2024 ዓ/ም የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው በዓለም ዙሪያ ወደ 6.84 ቢሊዮን የሚጠጉ የስማርት ስልክ ተጠቃሚዎች አሉ። በዚያው ልክ ደግሞ ለተንቀሳቃሽ ስልክ ሱስ ተጋላጭ የሚሆኑ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል።
የተንቀሳቃሽ ስልኮቻችን ለምን በሱስ እንድንያዝ ያደርጉናል?
ለመሆኑ የተንቀሳቃሽ ስልኮቻችን ለምን በሱስ እንድንያዝ ያደርጉናል? በስዊዘር ላንድ የሶፍትዌር መሀንዲስ የሆኑት አቶ ዳዊት ዓለሙ በአንድ ወቅት በሰጡን ማብራሪያ።አሰራራቸው በራሱ ሱስ ውስጥ የሚከት ነው።የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሱስ የመከላከል ባለሙያ ዩስቶስ ሞለንበርግ በበኩላቸው ይህንኑ ሀሳብ ያጠናክራሉ። «በእርግጥ ኢንዱስትሪው ስልኮቻችን እና መተግበሪያዎች የበለጠ ተወዳጅ እንዲሆኑ ለማድረግ ፤ የእለት ተእለት ህይወታችንን የበለጠ ምቹ በሚያደርጉ ነገሮች ላይ አዘውትሮ እየሰራ ነው። የምግብ አዘገጃጀት መመሪያም ይሁን አዲስ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለማየት እና የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በስልኮቻችን ላይ የምናሳልፈው የጊዜ መጠን እየጨመረ ነው።»ሲሉ ገልፀዋል።
ይህም ለትኩረት መቀነስ እና ለድካም ይዳርጋል። የስማርት ስልክ ሱስ ወደ ሥነ ልቦናዊ ችግሮች ሊያመራም ይችላል። በብሪታንያ የኖቲንግሃም ትሬንት ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ ምሁር የሆኑት ዛሄር ሁሴን "ችግር ያለበት የስማርት ስልክ አጠቃቀም በብዙ ሰዎች ህይወት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር የሚያሳይ ማስረጃ አለ ይላሉ። በተንቀሳቃሽ ስልክ አጠቃቀም እና እንደ ድብርት እና ጭንቀት ያሉ የአእምሮ ጤና እክሎች መካከል ግንኙነቶች መኖራቸውንም ያስረዳሉ።
የተንቀሳቃሽ ስልክ ሱስ ከተለያዩ የጤና ችግሮች ይዳርጋል
በአጠቃላይ የተንቀሳቃሽ ስልክ ሱስ ከተለያዩ የጤና ችግሮች ጋር የተቆራኘ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የእንቅልፍ መዛባት፣ የዓይን ድካም፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ እና የአንገት እና የጀርባ ህመምን ያስከትላል። በአእምሮ ጤንነት ላይም እንደ ድብርት፣ ጭንቀት፣ ብቸኝነት፣ እና ትኩረት እና ትውስታን መቀነስን የመሳሰሉ ችግሮችን በማስከተል፤ በተለይም በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ በሚገኙ ወጣቶች ላይ ተጽእኖ ያሳድራል። ከዚህ የተነሳ የስልክ ሱስን ማቆም ለአእምሮ እና ለአካላዊ ጤንነት መልካም ነው።ነገር ግን ልክ እንደ ሲጋራ ማጨስ ያሉ ሌሎች ሱሶች ማቆም ፈታኝ ሊሆን ይችላል ።ከባድ የስነ-ልቦና ትግል ይጠይቃል።።የባለሙያ እገዛና ምክርም ያስፈልጋል። የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሱስ የመከላከል ባለሙያው ዩስቶስ ሞለንበርግ ተከታዩን ምክር ለግሰዋል።
«በኢንስተግራም እና ሪልስ ቅንብር ላይ፤ ለምሳሌ፣ የታሪኮቹን ጊዜ ስድስት ወይም ስምንት ሰዓት በማድረግ መገደብ ትችላለህ። ነገር ግን ከዚያ በኋላም በእርግጠኝነት እነሱን ለማየት እንገደዳለን።ሌላው ሰዎች ሊያዩት የሚችሉት ጉዳይ፣መልዕክቱን አንብቤያለሁ የሚለው ምልክት ነው። በዋትስ አፕ ላይ ያለው ሰማያዊ ጽሑፍ ወዘተ ላይ ያለው ቅንብር፤ ማኅበራዊ ግንኙነቱ ለእርስዎ አስፈላጊ መሆኑን በማሳየት እና ወዲያውኑ መልስ እንዲሰጡ ግፊት የሚያሳድር ነው።»ብለዋል።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ጀርመናውያን በአማካይ በወር እስከ 40 ሰአታት ድረስ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ ጊዚያቸውን ያሳልፋሉ። በርካታ ሰዎች በቀን ከሁለት እስከ አራት ሰአት በስማርት ስልኮቻቸው ላይ ጊዜ ያሳልፋሉ።ነገር ግን በየቀኑ ከ4 ስዓት በላይ በስልከዎት ላይ ጊዜ ካጠፉ እና በአማካኝ 58 ጊዜ ያህል ስልከውን ከፈተሹ የስልክ አጠቃቀም ችግር እንዳለብዎት ያሳያል።ይህም ብዙውን የአስገዳጅነት ባህሪ ይኖረዋል።ስልክ በሌለበት ጌዜ የጠፉ ያህል እንዲሰማዎት እና ፍርሃት ስሜት እንዲኖር ያደርጋል።
የተንቀሳቃሽ ስልክ ሱስ ያለባቸው ሰዎች ባህሪያት
ባለሙያው ዩስቶስ ሞለንበርግ እንደሚሉት የተንቀሳቃሽ ስልክ ሱስ ያለባቸው ሰዎች ቶሎ የሚሰለቹ ሲሆን፤ ከማህበራዊ ግንኙነት የበለጠ ይገለላሉ ፣ ያለ ስማርት ስልካቸው የመጥፋት ስሜት ይሰማቸዋል።ከዚህ አንፃር ስማርት ስልከዎ በእጅዎ ከሌለ እራስዎን ሲቸገሩ ያገኙታል? ወይም ከሰዎች ጋር መገናኘትን ወደ ጎን በመተው ብቸኝነትን ይመርጣሉ? ሲሉ ይጠይቃሉ። መልሱ አው ከሆነ እነዚህ ባህሪያት የእርስዎ የስልክ አጠቃቀም ጤናማ እንዳልሆነ የሚያሳዩ የማስጠንቀቂያ ምልክቶች ናቸው ይላሉ ።
ስለሆነም የስማርት ስልክ አጠቃቀምዎ በአእምሮ ጤናዎ፣ እና በእለት ተእለት ህይወትዎ ላይ ተጽእኖ እያሳደረ እንደሆነ ከተሰማዎት የባለሙያ እርዳታ ለመጠየቅ አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል።ከዚያ በፊት የሚቀድመው ግን ራስን መጠየቅ ነው።
«የመገናኛ ብዙሃን ፍጆታ መሆንዎ አስደሳች እንደሆነ እራስዎን ይጠይቁ። ይህ የተወሰነ የአጠቃቀም ጊዜን በመፍጠር እራስን ለመቆጣጠር የሚያስችል ነገር ነው። ለምሳሌ ያ ጊዜ ካለፈ በኋላ ትኩረተዎን እንዳይከፋፍል የተንቀሳቃሽ ስልክዎን ቀለሞች ወደ ግራጫ ቀለም ይቀይሩ። ማሳወቂያዎችን በመዝጋትም ራሰዎን በተደጋጋሚ ትኩረት ከሚከፋፍሉ ነገሮች መጠበቅ ይችላሉ።»
የተንቀሳቃሽ ስልክ ሱስን ለማቆም ብዙ ዘዴዎችን መሞከር
የስማርት ስልክ ሱስን ለማሸነፍ ፈጣንና አንድ አይነት መፍትሄ የለም። የተለያዩ ሰዎች የተለያዩ ዘዴዎችን ይፈልጋሉ። ከአንድ በላይ ዘዴ እና እውነተኛ ቁርጠኝነትንም ይጠይቃል።ነገር ግን ሳይንቲስቶች የተንቀሳቃሽ ስልክ ሱስን ለማሸነፍ የሚረዱ ብዙ ዘዴዎችን አረጋግጠዋል። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ ሌሎች ሱሶችን ለማሸነፍ ጥቅም ላይ ከሚውሉ ዘዴዎች ጋር ተመሳሳይ ናቸው። ብዙ ጊዜም የሰዎችን ባህሪ ለመለወጥ በሚረዳ ስልጠና ላይ ያተኮሩ ናቸው።
ሳይንቲስቶች የሚመክሯቸው አንዳንድ ዘዴዎች
በተጠቃሚዎች ዘንድ መደረግ ካለባቸው ጥንቃቄዎች መካከል ስልክን ከመኝታ ቤት ውጭ ወይም ራቅ አድርጎ ማስቀመጥ ጠቃሚ ነው።በኢሜል ወይም በዋትስ አፕ እና በሌሎች መተግበሪያዎች መልዕክቶችን መምጣታቸውን የሚያሳውቁ ድምፆችን ንዝረቶችን ማጥፋት። የስልኩን ስክሪን ገፅ ወደ ጥቁር እና ነጭ መቀየር፣የማህበራዊ መገናኛ ዘዴ መተግበሪያዎችንከመነሻ ገፅ ወይም /ስክሪን/ ማስወገድ እና ረጅም የይለፍ መለያ ኮድ መፍጠር ያሉ ቀላል እርምጃዎች ስልክን ከመጠን በላይ እንዳንጠቀም ሊረዱ ይችላሉ።
ችግሩን የፈጠረውን ቴክኖሎጅን በመጠቀምም መፍትሄ ማግኘት ይቻላል።ከነዚህም መካከል ራስን ለመግዛትን የሚያግዙ መተግበሪያዎችን መጠቀም። እንደ Space፣ Forest፣ Flipd እና Screentime ያሉ መተግበሪያዎች ዕለታዊ የተንቀሳቃሽ ስልክ አጠቃቀምን መገደብ፣ ትኩረት የሚከፋፍሉ መተግበሪያዎችን መቆለፍ፣ የስልክ አጠቃቀም ልማዶችን ለማስተካከል ይችላሉ። አቶ ዳዊትም ተጨማሪ የጥንቃቄ ርምጃዎችን ይጠቅሳሉ።
ስለሆነም እነዚህን ርምጃዎች ከወሰዱ የበለጠ ደስተኛ ሊሆኑ ይችላሉ። ምክንያቱም እውነተኛው የገሀዱ ዓለም ከምናባዊው የሳይበር ዓለም የበለጠ ጤናማ ነውና።
ፀሐይ ጫኔ
ሂሩት መለሰ