1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከሶማሌ አዋሳኝ የተፈናቀሉ የኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች

ዓርብ፣ ሐምሌ 8 2014

በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን ጉራ ዳሞሌ ወረዳ የአንድ ቀበሌ ሙሉ ነዋሪዎች ይደርስብናል ባሉት ጥቃት ምክኒያት ተፈናቅለው ወደ አጎራባች ወረዳዎች መሸሻቸው ተገለጸ፡፡ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች እንደሚሉት ከጎረቤት ክልል ሶማሊ በኩል «የታጠቁ አካላት» ያሏቸው እርዳታ እንዳይደርሳቸው እና ገበያ እንዳይወጡ መንገድ ዘግተው ጥቃትን ይፈጽማሉ፡፡

Karte Äthiopien Regionen EN

በሚደርሰዉ ጥቃት ተፈናቅለው ወደ አጎራባች ወረዳዎች ሸሽተዋል

This browser does not support the audio element.

 

በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን ጉራ ዳሞሌ ወረዳ የአንድ ቀበሌ ሙሉ ነዋሪዎች ይደርስብናል ባሉት ጥቃት ምክኒያት ተፈናቅለው ወደ አጎራባች ወረዳዎች መሸሻቸው ተገለጸ፡፡ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች እንደሚሉት ከጎረቤት ክልል ሶማሊ በኩል «የታጠቁ አካላት» ያሏቸው እርዳታ እንዳይደርሳቸው እና ገበያ እንዳይወጡ መንገድ ዘግተው ጥቃትን ይፈጽማሉ፡፡ በወረዳው የሶማሊ ክልል ሃሮ ዲቤ ወረዳን ከሚያዋስነው ኦኮልቱ ቀበሌ ተፈናቅለው ወደ የባሌ ዞን ደሎ መና ወረዳ ብቻ የተሸሸጉ ነዋሪዎች ቁጥር ከ 8 ሺህ እንደሚልቅ የዞኑ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽ/ቤት (ቡሳ ጎኖፋ) ለዶይቼ ቬለ አረጋግጧል፡፡ እንደ የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ወንድማገኝ ከበደ ገለጻ የጉራ ዳሞሌ ወረዳ ኦኮልቱ ቀበሌ ሶማሊ ክልል ሃሮ ዲቤን በሚያዋስን ኪስ ቦታ የምትገኝ ስፍራ እንደመሆኗ ነዋሪዎች በወሰን አከባቢ ግጭት የተነሳ ለተለያዩ እንግልትና ስቃይ ይዳረጋሉ ብለዋል፡፡

ሀሰን ኢብሮ አደም ከባሌ ዞን ጉራ ዳሞሌ ወረዳ የሶማሌ ክልል ሃሮ ዲቤ አጎራባች ቀበሌያት ከተፈናቀሉ ናቸው፡፡ እኚ ነዋሪ ለዶይቼ ቬለ በሰጡት መረጃ እንዳረጋገጡት፤ ከአጎራባች ክልሉ ታጣቂዎች በሚደርስባቸው ጥቃት ከኦኮልቱ ቀበሌ ሙሉ በሙሉ ነዋሪዎች ወደ ባሌ ዞኑ ሌላኛው ወረዳ ደሎ መና ሲፈናቀሉ እስከ ስድስት የሚደርሱ ቀበሌያት ውስጥ ከሚኖሩ ነዋሪዎችም ወደ ዳዌ ቃቸን እና በርበሬ ወረዳዎች የተፈናቀሉም መኖራቸውን አመልክተዋል፡፡ “አሁን ያጋጠመን ነገር በክልል 5 ከዚህ በፊት የነበረው መንግስት ያደራጃቸው የታጠቁ አካላት የአስተዳደር ወሰናችን በማለፍ መሬታችን በማረስ ነው የሚያፈናቅሉን፡፡ በኦኮልቱ ቀበሌ ውስጥ ሰው ሙሉ በሙሉ ተፈናቅለዋል፡፡ በሌሎች ቀበሌዎችም እስከ ትናንት ማታ እንኳ ዝርፊያ እና ግድያ እየተፈጸመ ነው፡፡ ጥቃቱ እንደ ዲሽቃ ያለ ከባድ መሳሪያ በመጠቀም በብዛት ለሊት ነው የሚፈጸመው፡፡ እኛን አሁን የጎዳን ሁለት ነገር ነው፡፡ በድርቅ ምክኒያት ከብቶቻችን የሚመገቡት አጥተው እየተሰቃየን ነው፡፡ በዚህ ላይ እርዳታ እንዳይደርሰን መንገድ ተዘግቶ ለእርዳታ የሚመጣልን ነገርም መንገድ ላይ ይዘረፋል፡፡ ከዚህ የተነሳ ነው ሰው ሁሉ የቻለውን ይዘው ያልቻሉትንም ጥለው የተፈናቀሉት፡፡ ኦኮልቱ ቀበሌ ውስጥ አንድ ልጅ እንኳ የቀረ የለም፡፡ ሁሉም ወደ ደሎ መና ነው የተፈናቀሉት፡፡ከኮቱ እና ከበርከሌ ቀበሌዎችም ወደ በርበሬ እና ዳዌ ቃቸን ወረዳ እየተፈናቀሉ ነው” ብለዋል ለጥቃት መዳረጋቸውን ያወሱት ነዋሪው፡፡

እንደ ተፈናቃዩ አስተያየት ሰጪ በሚያዚያ ወር ውስጥ ጀምሮ የሚላክላቸው የድጋፍ እህል በታጣቂዎቹ መንገድ ላይ ይዘረፋል፡፡ ሰው ሁሉ ወደ ገበያ እንኳ ለመውጣት መንገድ በማጣት ተከበው እንደቆዩና በዚህም ምክኒያት ወደ 20 ሰዎች ገደማ በርሃብ ምክኒያት ህይወታቸው አልፏል ነው ያሉት፡፡ በጥይት ተመተው የተገደሉም አንድ ሁለት የሚባሉ ሳይሆን በርካቶች ናቸው ይላሉ የጥቃቱ ገፈት ቀማሽ በአስተያየታቸው፡፡ “መንገድ የሚባል ነገር የለም፡፡ ሰው እየተጠቃ ነው፡፡ እስከ ትናንት እንኳ ተዘርፈው የተገደሉ አሉ፡፡ ቀርሳ ገባባ ወደ ሚባል ስፍራ ገበያ እንዳንወጣም ነው ያደረጉን፡ አሁንም ጨፋ በሚባል ስፍራ ሰው እየተጠቃ ነው፡፡ በከበባ መውጪያ መግቢያ አጥተው የሞተ እኮ ነው ያለው፡፡ ችግሩ እኮ ወደ ስድስት ቀበሌያት ሰፍቷልም” ሲሉም አስተያየታቸውን አክለዋል፡፡

ምስል G. Fischer/blickwinkel/picture alliance

ሰላማዊ በነበረው በአከባቢው የተፈጠረው አለመግባባት አዲስ ነገር መሆኑን የሚገልጹት የባሌ ዞን አደጋ ስጋት ስራ አመራር በአዲስ አጠራሩ የዞኑ ‘ቡሳ ጎኖፋ’ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ወንድማገኝ ከበደ የኦኮልቱ ቀበሌ ነዋሪዎች ገበያ እንኳን ወጥተው እንዳይገበያዩ በማሴር ሰላማዊ ዜጎችን የሚያፈናቅሉት “የፖለቲካ ፍላጎት” ያላቸው ያሉት ግለሰቦች መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡ አቶ ወንድማገኝ ችግሩን ለመፍታት የአከባቢው ባለስልጣናት ያደረጉት ጥረት እምብዛም ፍሬ እንዳላፈራም ገልጸዋል፡፡ “የችግሩ መነሻ በሶማሊ ክልል በኩል ወሰን እያለፉ በኢንቨስትመንት ስም ሰው እያሰፈሩ ማረስ አለ፡፡ ይሄ ግጭት መስተዋል ከጀመረም ወደ ሁለት ወራት ተቆጥሯል፡፡ ችግሩን ለመፍታት በዞን ደረጃ ብዙ ብንገፋበትም ስላልተሳካልን ነው አሁን ሰው እስከመፈናቀል ያደረሰው ችግር የተፈጠረው፡፡ በተለይም ኪስ ቦታ ላይ የምትገኘው ያቺ የኦኮልቱ ቀበሌ በሶማሊ ክልል ተከባ የምትገኝ እንደመሆኗ፤ ሰው ላይ መተኮስ፣ የእርዳታ እህል ወደዚያ እንዳይገባም መንገድ በመዝጋት መዝረፍ በዚህም ሰውን በማፈናቀል አከባቢውን የመቆጣጠር ፍላጎት ነው ያለው፡፡ እንዲህ ያለን ጭካኔ ተመሳሳይ ምላሽ በመስጠት ለህብረተሰቡ እርዳታ እንዳናደርስ ህዝብ መሃል መቋሰል እንዳይፈጠር ነው በትዕግስት ለማየት የወሰነው፡፡ በዚህ የተሰላቸው ማህበረሰብ ነው እንግዲህ ባለፈው ሳምንት ሰኔ 30 ወደ ደሎ መና ወረዳ ከሌ ጎልባ ቀበሌ ቡርቃ ወደ ሚባል ስፍራ የተፈናቀሉት፡፡ አሁን በዚህ ስፍራ የደረሱ 1 ሺህ 38 አባወራዎች ሲሆኑ በሰው ቁጥር 8 ሺህ 759 ናቸው” ሲሉም አብራርተዋል፡፡

ዞኑ ተፈናቅለው በደሎ መና ወረዳ ለደረሱ ተለያዩ የእርዳታ ድጋፎች እያቀረበ መሆኑንም አቶ ወንድማገኝ አመልክተዋል፡፡ 4 ሺህ ኩንታል ሩዝና ዱቄት፣ ከአንድ ሺህ ሊትር በላይ ዘይት እና ወደ 400 ኩንታል ጥራጥሬ እህልም እስካሁን ማቅረባቸውንም ገልጸዋል፡፡ በቀይ መስቀል በኩልም የተለያዩ አልባሳት እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ሌሎች ቁሳቁስ መቅረቡንና የአከባቢው ማህበረሰብም በኩሉን ድጋፍ እያደረገም ነው ብለዋል፡፡

አሁንም ችግሩ ከመሰረቱ ካልተፈታ የተፈናቃዮች ቁጥር ሊጨምርና ወደ ከፋ ደረጃ ሊሸጋገር እንደሚችል ስጋታቸውን የገለጹት የዞኑ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽ/ቤት ኃላፊው፤ የሁለቱ ክልሎች ባለስልጣናት እና የፌዴራል መንግስት በጉዳዩ ጣልቃ እንዲገቡም ጠይቀዋል፡፡ “በጦርነት እየተሄደበት ያለው ይህ ችግር ተቀርፎ ተፈናቃይ ማህበረሰቡ ወደ ቀዬው ተመልሰው ኑሮውን መምራት አለበት የሚል አቋም ይዘን ሁለቱ ክልሎች እንዲወያዩበት ሪፖርት ስናቀርብ ነው የቆየነው፡፡ ከዚህም ከከፋ የፌዴራል መንግስት ጣልቃ ገብቶ ነው ችግሩ ከመሰረቱ መፈታት ያለበት፡፡ በሶማሊ ክልል በኩል የሚስተዋለው በአንድ ሁለት ሰው የመግደል፣ ሰው ወደ ገበያ እንዳይወጣ እና የእርዳታ ምግብ እንዳይደርስለት መንገድ በመዝጋት ሰው ማስራብ፣ መዝረፍ መቆም አለበት፡፡ በህገወጥ ታጥቀው ሰው የሚያፈናቅሉት አንድ ነገር ካልተባሉ ከዚያም ከዚህም ሰው ወደ ከፋ መቆሳሰል እንዳይገባ ያሰጋል” በማለትም ለእልባቱ ተጣርተዋል፡፡

የባሌ ዞን ባለስልጣኑ አቶ ወንድማገኝ ከበደ እንደሚሉት ሙሉ ነዋሪዎቿ የተፈናቀሉት የኦኮልቱ ቀበሌ ብቻ ይሁን እንጂ ይፈጸማል ያሉት ጥቃት እስከ ጉራ-ዳሞሌ የወረዳ ከተማ ጅብሪ እና ሌሎች ቀበሌያትም የተዘረጋ ነው፡፡ ግጭቱን ተከትሎ በተፈጠረው ጥቃት በቁጥር ባይገልጹትም በርካቶች መገደላቸውንም ኃላፊው አመልክተዋል፡፡ “በማስራብ ጦርም ጭምር በመጠቃታቸው ነው ቤታቸውን ዘግተው ባንዴ የወጡትም”

ነው ያሉት በማብራሪያቸው፡፡ በሶማሊ ክልል በኩል እነዚህን ቀበሌያት የምታዋስነው ሃሮ ድቤ ወረዳ በ1990ዎቹ መጨረሻ በህዝበ ውሳኔ ከኦሮሚያ ክልል ወደ ሶማሌ ክልል አስተዳደር መግባቷ ነው የሚነገረው፡፡ የባሌ ዞኑ ጉራ ዳሞሌ ወረዳ አሁን በተባባሰው ድርቅ እና የኑሮ ውድነት በእርዳታ ከሚኖሩ የአከባቢው ቆላማ ስፍራዎች ይጠቀሳልም፡፡

በአከባቢው ባለው የኔትዎርክ ችግር ምክኒያት የየወረዳዎቹን የአከባቢ ባለስልጣናት ማግኘት አልተቻለም፡፡ ስለ ጉዳዩ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ለሶማሊ ክልል የጸጥታ እና ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊዎችም በተደጋጋሚ የእጅ ስልኮቻቸው ላይ ደውለን ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለዛሬ አልተሳካም፡፡ ከዚህ ቀደም ከአራት ኣመታት በፊት በኦሮሚያ እና ሶማሊ ክልሎች አዋሳኝ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎች ያፈናቀለ ግጭት ተከስቶ የኋላ ኋላ ግን በሁለቱ ክልሎች አመራሮች እልባት ማግኘቱ አይዘነጋም፡፡

 

ስዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW