«ከቄለም ወለጋ ዞን ከ45ሺ በላይ ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ቀርቧል» የዞኑ ንግድ ጽ/ቤት
ቅዳሜ፣ ግንቦት 9 2017
«ከቄለም ወለጋ ዞን ከ45ሺ በላይ ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ቀርቧል» የዞኑ ንግድ ጽ/ቤት
ከፍተኛ የቡና ምርት ከሚገኝባቸው የኦሮሚያ ዞኖች መካከል አንዱ የሆነው የቄለም ወለጋ ዞን በዚህ ዓመት ወደ ማዕከላዊ ገበያ ከቀረበው ቡና ከፍተኛ ገቢ ማስገኘቱን የቡና አቅራያዎችና አርሶ አደሮች ተናግረዋል፡፡ የዞኑ ንግድ ቢሮ እንዳለው ገቢው ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር 30 በመቶ ብልጫ አለው፡፡
በኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን መረጃ መሠረት ኢትዮጵያ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ወደ ውጪ ከላከችው ቡና 1.5 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የውጭ ምንዛሪ ማግኘቷን ያመለክታል፡፡ በምዕራብ ኦሮሚያ ከፍተኛ የቡና ምርት በሚገኝበት የቄለም ወለጋ ዞን ውስጥ እንደ አንፊሎ ፣ጊዳሚ፣ሀዋጋላን እና ሳዮን ከመሳሰሉ ወረዳዎች ከ40ሺ በላይ ቶን ቡና ወደ ማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን የዞኑ ንግድ ቢሮ አስታውቋል፡፡ በዞኑ አንፊሎ ወረዳ ካለፈው ዓመት ከነበረው የተሻለ ቡና ማግኘታቸውን እና ለገበያ መቅረቡን ያነጋርናቸው አርሶ አደሮችና አቅራቢዎች ተናግረዋል፡፡ አቶ ተመስገን ጫሊ የተባሉ ቡና አቅርቢና አርሶ አደር በሀገር አቀፍ ደረጃ የቡና ዋጋ መጨምር በቡና ምርት ለተሰማሩ አርሶ አደሮች የተሻለ ዋጋ ማስገኘቱን ተናግረዋል፡፡ በአንፊሎ ወረዳ የቡና ምርቱ ዘንድሮ የተሻለ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
እያደገ የመጣው የኢትዮጵያ ቡና የውጪ ገቢያ እና ተግዳሮቱ
‹‹ ምርቱ ከባለፈው ዓመት የተሻለ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት 200 ኩንታል ነው ወደ ማዕከላዊ ገበያ ያቀረብነው፡፡ ዘንድሮ ደግሞ 750 ኩንታል ቡና ነው ወደ ማዕከላዊ ገበያ ያቀረብነው ፡፡ አርሶ አደሩ ያመረተውን ያህል ገቢ አግኝቷል ብለን እናስባለን፡፡››
የቡና ዋጋ መጨመር የአርሶ አደሮችን ገቢ አሳድጓል
በቄለም ወለጋ ዞን ጊዳሚ ወረዳ አርሶ አደሩ ከ50 እስከ 80 ኩንታል በግለሰብ ደረጃ ቡና ለገበያ አቅርቧል፡፡ ሆኖም በወረዳው በዚህ ዓመት የምርቱ መጠን ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ መሆኑን ያነጋርናቸው አንድ አርሶ አደር ገልጸዋል፡፡ የአየር ንብረት መለወጥ እና የጸጥታ ችግር ለምርቱ መቀነስ በምክንያትነት ተጠቅሷል፡፡ በዚህ ዓመት የቡና ዋጋ ባለፈው ዓመት ከነበረው ዋጋ ጋር ሲነጻጸር በኪሎ ከ2 መቶ እስከ 3 መቶ ብር ጭማሪ ያለው መሆኑን ያነሱት አርሶ አደሩ የዋጋ መጨመር ለአርሶ አደሩን ገቢ ማሳደጉን ነው የሚናገሩት ፡፡ በአካባቢው የሚስተዋለው የሰላም እጦት ቢቀረፍ የተሻለ ምርት እንደሚገኝ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ገበያ ያገኘው ዕድል
‹‹ምርቱ ብዙም አይደለም የቡና ዋጋ ግን ጥሩ ነው፡፡ 50 ኩንታል ለገበያ አቅርቤአለሁ፡፡ የቡና ዋጋ ከባፈው ዓመት 2 እጥፍ ነው የጨመረው፡፡ ባለፈው ዓመት ከሸጥነው በኪሎ ከ 2 እስከ 3 መቶ ብር ብልጫ አለው፡፡ ከጸጥታ ሁኔታ ጋር ተያይዞ በጊዳሚ ሰው በተገቢው ሁኔታ ስራውን እየሰራ አይደለም ፤ ያገኘውን ነው ወደ ገበያ ያቀረበው፡፡ እኔ ባለፈው ዓመት 80 ኩንታል ነበር ለገበያ ያቀረብኩት፡፡ በጊዳሚ በትንሹ እስከ 400 መቶ ኩንታል ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ይቀርባል፡፡››
የቄለም ወለጋ ዞን ንግድ ቢሮ በዞኑ ስር ከሚገኙ አራት ወረዳዎች ከፍተኛ የቡና ምርት እንደሚገኝ ይገልጻል፡፡ በዞኑ አንፊሎ፣ጊዳሚ፣ ሀዋጋላን እና ሳዮ ወረዳዎች ውስጥ በየዓመቱ ከፍተኛ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ከሚቀርባቸው አካባቢዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው ተብሏል፡፡ የቄለም ወለጋ ዞን ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ ገመዳ በከኮ በዞኑ የቡና ምርት ጥራት መሻሻሉን እና ለአርሶ አደሩ እና አቅራቢያዎች የተሻለ ገቢ ማስገኘቱን ገልጸዋል፡፡
የትስስር የቡና ንግድ መንገዱ አቋራጭ ወይስ?
‹‹ ባለፈው ዓመት 37 ቶን ነው ለማዕከላዊ ገበያ የቀረበው፡፡ በዚህ ዓመት እስካሁን 45ሺ500 ገደማ ቶን ቡና ነው በዞን ደረጃ ለገበያ የቀረበው፡፡ በዚህ ዓመት መጨረሻ 48ሺ ቶን ይደርሳል ብለን እንጠብቃለን፡፡ ቡና በብዛት በሚገኝባቸው አንፊሎ፣ጊዳሚ እና ሰዮ ወረዳዎች ቡና በብዛትና ጥራት ለገበያ ይቀርባል፡፡ ››
ለረጅም ጊዜ አርሶ አደሩ በቀሌም ወለጋ እና ሌሎችም አካባቢዎች የጸጥታ ችግር በምርታቸው ላይ ተጽህኖ ሲያድር መቆየቱንም ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ ከአራቱ የወለጋ ዞኖች የቀሌም ወለጋ ዞን በቡና ምርት በመጀመሪያ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ይነገራል።
ነጋሳ ደሳለኝ
ታምራት ዲንሳ