1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

ከቆሻሻ ገቢ የሚፈጥረው ቴክኖሎጅ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 30 2015

መረጃዎች እንደሚያሳዩት በኢትዮጵያ 280,000 ቶን የቡና ተረፈ ምርት ጥቅም ላይ ሳይውል በየዓመቱ ይወገዳል። ይህንን ችግር የተገነዘበው ሀስኪ ኢነርጅስ እና ቴክኖሎጅ የተባለው ሀገር በቀል ጀማሪ የቴክኖሎጅ ኩባንያ፤ የቡና ተረፈ ምርትን ወደ ኃይል ምንጭነት በመለወጥ የኃይል እጥረትን እንዲሁም ብክለትን ለመቅረፍ በመስራት ላይ ይገኛል።

Äthiopien | Gründer des Startups Hasky Energies and Technology | Hoheyat Birhanu und Yohannes Wasihun
ምስል Privat

ቴክኖሎጅው የደን መጨፍጨፍ እና የማገዶ እጥረትን ይቀንሳል

This browser does not support the audio element.


ኢትዮጵያ በቡና ምርቷ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስሟ የሚጠቀስ ሀገር ነች። ቡና በኢትዮጵያ  ከ30 በመቶ በላይ የውጭ ምንዛሪ ገቢን በመያዝ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት  ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል።ከዚህ በተጨማሪ ከ15 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ አነስተኛ አርሶ አደሮች እና  በቡና ዘርፍ ለተሰማሩ ሌሎች ተዋናዮች መተዳደሪያ ሆኖ ያገለግላል። 
ያም ሆኖ  በኢትዮጵያ ስለቡና ምርት እንጅ  ከቡና ስለሚወጣው ተረፈ ምርት  ብዙ ትኩረት  የተሰጠው አይመስልም። መረጃዎች እንደሚያሳዩት በኢትዮጵያ  280,000 ቶን የቡና ተረፈ ምርት  ጥቅም ላይ ሳይውል በየዓመቱ ይወገዳል።
ይህንን ችግር  የተገነዘበው /Husky Energies & Technology/ የተባለው ታዳሽ ሀይል ላይ ያተኮረው ሀገር በቀል ጀማሪ የቴክኖሎጅ ኩባንያ ታዲያ፤ የቡና ተረፈ ምርትን  ወደ ኃይል ምንጭነት በመለወጥ የኃይል እጥረትን እንዲሁም  ብክለትን  ለመቅረፍ በመስራት ላይ ይገኛል። ከኩባንያው መስራቶች አንዱ የሆነው ሆሄያት ብርሃኑ  እንደሚለው ይህንን ችግር  የተገነዘቡት የዩንቨርስቲ ተማሪ እያሉ ለልምምድ በወጡበት ወቅት ነበር።
«ሀሳቡን የጀመርነው የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ተማሪዎች በነበርንበት ወቅት ነው። በዚያ ጊዜ «ኢንተርን ሽፕ ታይም» ነበረን።በዚያ ጊዜ ከቤንች ማጅ እና ከይርጋ ጨፌ የመጡ የቡና አምራች ማህበራት ተወካዮችን ስልጠና የመስጠት ዕድል ነበረን።በምንሰራበት ድርጅት የተመረተላቸው ማሽን ስለነበረ ስለአጠቃቀሙ ስልጠና እንሰጥ ነበር።በሻይ ስዓት በምንነጋገርበት ጊዜ በቡና ምርት ሂደት የሚያስቸግራችሁ ነገር ምንድነው? ብለን ጠየቅናቸው,ገበሬዎቹን።የነገሩን ነገር የሚያስቸግራቸው የቡና ገለባው ተረፈ ምርቱ በጣም እንደሚያስቸግራቸው ነግረውናል።ግቢያቸውን እንደሚሞላባቸው ከቆየ በኋላ ሽታም እንደሚያመጣ ነገሩን።»በማለት ተናግሯል።
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ  በሜካኒካል ምህንድስና በ2014 ዓ/ም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን የያዙት  ሆሄያት ብርሃኑ እና ዮሃንስ ዋሲሁን በዚህ ሁኔታ የቡና ተረፈ ምርት ለገበሬዎች ትልቅ ችግር መሆኑን  ከተገነዘቡ በኋላ ችግሩን  ለመፍታት የመመረቂያ ስራቸውን በዚሁ ጉዳይ ላይ እንዲያተኩር አደረጉ።ከገበሬዎቹ  ያገኙትን መረጃ ይዘውም ጠለቅ ያሉ ጥናቶችን ማድረግ ጀመሩ።
በዚህ ጥናትም የቡና ገበሬዎች ብዙ ወጭ አውጥተው ተረፈ ምርቱን  ለመጣል ወይም ለማቃጠል እንደሚገደዱ ፣ ለብዙ ጊዜ ተከማችቶ ሲቆይ ደግሞ ስለሚበሰብስ  ሽታው ለመተንፈሻ አካል ችግር እንደሚዳርግ እንዲሁም የአካባቢ ብክለትን እንደሚያስከትል ተገነዘቡ።
በሌላ በኩል የቡና ተረፈ ምርት  በተወሰነ መጠን  «ካፌይን» እና «ታኒን»የተባሉ ንጥረ ነገሮችን የያዘ በመሆኑ  ለእንስሳትን መኖ ቢውል እንኳ  መርዛማ እና የምግብ መፈጨት ስርዓትን የሚያውክ መሆኑን  መረጃ አገኙ።
ሆሄያት እንደሚለው በዓለም አቀፍ ደረጃ የቡና ቅርፊትን ለማዳበሪያነት መጠቀም  የተለመደ ቢሆንም በኢትዮጵያ  ቡና የሚደርስበት ወቅት አመቺ ባለመሆኑ ቅርፊቱን እና ገለባውን ለማዳበሪያነት መጠቀምም አስቸጋሪ ነው። 
በመሆኑም አውጥተው አውርደው ይህንን ችግር ለመፍታት ተረፈ ምርትን ወደ ሀይል ምንጭነት መቀየር  የሚችል የማሽን ንድፍ ሰርተው ለመመረቂያ ጥናታቸው አቀረቡ ።
ይህ ስራቸው በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የሜካኒካል የኢንዱስትሪ እና ምህንድስና ትምህርት ቤት  ምርጥ የመመረቂያ ፅሁፍ የሚል እውቅና ማግኜቱን የሚገልፀው ሆሂያት፤ «ስቲም ፓወር »የተባለ በምህንድስና፣ በሂሳብ ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጅ ላይ የሚሰራ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ባደረገላቸው የገንዘብ  ድጋፍ ደግሞ ስራቸውን ከንድፍ ወደ ተግባር አሸጋገሩት።  
በዚህ ሁኔታ ከምረቃ  በኋላ «ሀስኪ ኢነርጂ እና ቴክኖሎጂ»/Husky Energies & Technology/  የሚል ጀማሪ የቴክኖሎጅ ኩባንያ በመመስረት ከመጀመሪያው ስራቸው የተሻለ አቅም ያለው ማሽን በመስራት ወደ  ሙከራ ተግባር ገቡ።

ዮሃንስ ዋሲሁን አና ሆሄያት ብርሃኑ ምስል Privat
የሃስኪ ኢነርጅስ እና ቴከኖሎጀ መስራቾች ዮሃንስ ዋሲሁን አና ሆሄያት ብርሃኑ (ከግራ ወደ ቀኝ) ምስል Privat
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

«ከዚያ በኋላ ግን አሁን አሳድገን እየሰራን ነው ።ቀደም ሲል የሰራነው ማሽን በስዓት አስር ኪሎግራም የሚያመርት ማሽን ነበር። አሁን የሰራነው በስዓት 100 ኪሎግራም የሚያመርት ማሽን ነው።» በማለት በንፅፅር ገልጿል።
ይህ ማሽን የቡና ቅርፊት እና ገለባን «ፔኔትስ» እና «ብሪኬትስ» ወደ ተባሉ ከሰል እና እንጨት መሳይ ማገዶ የሚቀይር ሲሆን እነዚህ ምርቶች ለተለያዩ ግልጋሎቶች ይውላሉ።

ከቡና ተረፈ ምርት የተሰራ ማገዶምስል Privat

« እነዚህ «ፔሌት»እና «ብሪኬቶች» የከሰለ እና ያልከሰለ አድርገን እናመርታቸዋለን።የከሰለ የሚፈልጉ «ከስተመሮች» አሉ ያልከሰለ የሚፈልጉ «ከስተመሮች» አሉ።የከሰለውን ጭስ ስለሌለው በቤት ውስጥ፣ለቡና ማፍያ መንገድ ላይ ቡና ጠጡ ለሚሰሩ ሴቶች፣ለሆቴሎች፣ለሬስቶራንቶች ለተለያዩ አገልግሎቶች ያገለግላል።ያልከሰለውን ደግሞ ቀጥታ እንጨት የሚጠቀሙ የተለያዩ ግለሰቦች እና ድርጅቶች አሉ።ለእነሱ እንጨትን ተክቶ ያገለግላል።»በማለት አገልግሎቱን አብራርቷል። 
በዚህ ሀሳብ እና ስራቸው ወጣቶቹ ከፈጠራ እና ክህሎት ሚንስቴር እንዲሁም ከቶታል ኢነርጅ ሽልማት አግኝተዋል።

ከኢተዮጵያ የሰራ አና ክህሎት ሚነቴር ሽልማት ሲወስዱምስል Privat

የቡና ተረፈ ምርትን ወደ ሀይል ምንጭነት የመቀየሩ ስራ  ገቢ ከማስገኘቱ ባሻገር የቡና አምራች ገበሬዎችን የቆሻሻ አወጋገድ ችግር ያቃልላል። እንጨትን እና ከሰልን የሚተካ በመሆኑ ፣የደን መጨፍጨፍ ፣ የአካባቢ ብክለት እና የማገዶ እጥረትን ይቀንሳል።ከዚህ በተጨማሪ  የሚመረተው ከሰል ጭስ አልቫ በመሆኑ በቤት ውስጥ የሚከሰት በጭስ መታፈን እና መመረዝን ያስቀራል። «በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ምግብ የሚበስለው በሶስት ጉልቻ ቤት ውስጥ በእንጨት ነው።ማድቤቱም፣ ሳሎኑም፣ አንድ ላይ ሆኖ ሰውም፣ ህፃናቱም ባሉበት እዚያው ነው የሚነደው ።ጭሱን ሰዎች በሚተነፍሱበት ጊዜ «ኢንዶር ፖሉሽን»ወይም የቤት ውስጥ አየር መበከል እንለዋለን። በዓለም ዙሪያ 4 ሚሊዮን ሰዎችን ይገድላል።ይህ ቁጥር ኤች አይቪ፣ ወባ እና ቲቪ በሽታዎች ተደምረው ይህን ያህል ቁጥር አይገድሉም። በኢትዮጵያም 50 ሺህ ሰዎች እንደሚገድል መረጃ አለን።»በማለት የችግሩን ግዝፈት ከገለፀ በኋላ፤በአብዛኛው ምግብ የሚያበስሉ ሴቶች በመሆናቸው የዚህ ችግር ሰለባዎችም በአብዛናው ሴቶች እና አብረዋቸው የሚሆኑ ህፃናት ሊሆኑ እንደሚችሉ ጠቁሟል።ስለዚህ ይህንን ችግር ለመፍታት እነሱ የሰሩት የማገዶ አይነት መፍትሄ ሊሆን እንደሚችል ተናግሯል። አጠቃቀሙን ውጤታማ ለማድረግም ለቤት ውስጥ እና መንገድ ላይ ለሚሸጡ የፈጣን ምግብ ማብሰያዎች የሚያገለግል  90 በመቶ ጭስን የሚቀንስ የማገዶ ቆጣቢ ምድጃ  ሰርተው ወደ ገበያ እያቀረቡ መሆኑን ገልጿል። 
ለዚህ  ስራቸው የምርት ግብዓት ለማግኘት ያቀዱት ለጊዜው በአዲስ አበባ ዙሪያ ከሚገኙ የቡና ማቀነባበሪያ ድርጅቶች ሲሆን፤አቅማቸው እያደገ ሲሄድ ግን የቡና አምራች ገበሬዎች ባሉበት ቦታ ሁሉ ግብዓት ለመሰብሰብ አስበዋል።በዚህ ሁኔታ በሙሉ አቅም ማምረት ሲጀምሩ በቀን ሶስት ነጥብ ሁለት  ቶን ፤ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ደግሞ አስር ቶን ማገዶ በየቀኑ ለገበያ እንደሚያቀርቡ ተናግሯል።ለጊዜው ግን ሆሄያት እንደሚለው ይህንን ዕቅዳቸውን ለማሳካት የገበያ ጥናት በማድረግ እና የመስሪያ ቦታ ለማግኘት በመጠባበቅ ላይ ናቸው።

የኢትዮጰያ የስራ እና ክህሎት ሚነስትር የማሽኑን ንድፍ ሲመለከቱ ምስል Privat

 

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

 

ፀሀይ ጫኔ
ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW