1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከትራምፕ የፍርድ ሂደት ምን ይጠበቃል?

ማክሰኞ፣ መጋቢት 26 2015

ትራምፕና ሸሪኮቻቸው ክሱን ፖለቲካው አንደምታ አለው ሲሉ ያስተባብላሉ። የማንሐተን አውራጃ ዐቃቤ ሕግ ክስ ያቀረበባቸው፣ስቶርሚ ዳንኤልስ ከተባለች የወሲብ ፊልም ተዋናይ ጋር ነበራቸው ስለተባለው ግንኙነት እንዳትናገር የሰጧት አፍ ማስያዣ ክፍያ፣በኒውዮርክ ሕግ መሠረት፣ እስከ አንድ ዐመት የሚያስቀጣ ወንጀል መሆኑን ዶክተር ፍጹም ተናግረዋል።

Donald Trump New York City Ankunft Trump Tower
ምስል Yuki Iwamura/ASSOCIATED PRESS/picture alliance

ከትራምፕ የፍርድ ሂደት ምን ይጠበቃል?

This browser does not support the audio element.

የቀድሞ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምኘ፣በቀረበባቸው የወሲብ ቅሌት ክስ ዛሬ ኒውዮርክ ውስጥ ከሰዓታት በኋላ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል። ትራምፕ ፍሎሪዳ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ማሮላጎ ኒውዮርክ የገቡት ትናንት ምሽት ሲሆን፣በግዛቲቱ ከፍተኛ የጸጥታ ጥበቃ እየተካኼደ ነው። የትራምፕ ክስ በአሜሪካ ሕጋዊና ፖለቲካዊ ክርክሮችን አቀጣጥሏል።  አነጋጋሪነታቸው የቀጠለው ዶናልድ ጄ ትራምፕ፣የወንጀል ክስ የሚመሰረትባቸው የመጀመሪያው የአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሆነዋል። ዛሬ ማንሐተን ኒውዮርክ በሚገኘው ፍርድ ቤት በቀድሞው ፕሬዚዳንት ላይ ይቀርባሉ ተብለው ስለሚጠበቁ ዋነኛ የክስ ጭብጦች እንዲያስረዱ ዶይቸ ቨለ የጠየቃቸው፣በቨርጂኒያ የሕግ ባለሙያው ዶክተር ፍጹም አቻምየለህ፣ "የተከሰሱበት የወንጀል ዝርዝር፣ ወደ 30 ዐይነት ወንጀል ነው።ዋናው የዚህ ሁሉ ክስ መነሻ፣ የአፍ መዝጊያ ብር ሰጥተዋል ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በሚወዳደሩበት ጊዜ "ሐሽ መኒ"ይባላል።ይህ ደግሞ በአሜሪካ የምርጫ ሕግ መሠረት ወንጀል ነው። እና የግብረ ስጋ ግንኙነት ነበረን ላለችው ግለሰብ የከፈሉት፤ግን ያንን የተከፈለበት ምክንያት ዝም እንድትልና የእሳቸውን የመመረጥ ዕድል እንዳታደናቅፍ ተደርጎ ነው።ያን የከፈለው ደግሞ የርሳቸው ጠበቃ ነው፤ኮህን ይባላል።ስለዚህ ያ ጠበቃ ያንን ብር ከፈለ ያ እሱን የከፈለውን ብር ትራምፕ ባለቤት የሆኑበት ድርጅት የሱ የጠበቃውን ክፍያ ጨምሮ 400 ሺ ዶላር እንደጉርሻ ተሰጠው ማለት ነው።ያንን ግን ታክስ ሲያስሞሉ አካውንቶቻቸው ልክ እንደ ቢዝነስ ወጪ ተደርጎ ነው የተቀመጠው የታክስ ወረቀታቸው ጋር።"ብለዋል

ትራምፕና ሸሪኮቻቸው ክሱን ፖለቲካው አንደምታ አለው ሲሉ ያስተባብላሉ። የማንሐተን አውራጃ ዐቃቤ ሕግ ክስ ባቀረበባቸው፣ስቶርሚ ዳንኤልስ ከተባለች የወሲብ ፊልም ተዋናይ ጋር ነበራቸው ስለተባለው ግንኙነት እንዳትናገር የሰጧት አፍ ማስያዣ ክፍያ፣በኒውዮርክ ሕግ መሠረት፣ እስከ አንድ ዐመት የሚያስቀጣ ወንጀል መሆኑን ዶክተር ፍጹም ተanግረዋል። ሌሎቹ 29 ክሶች ግን ከባድ ናቸው ይላሉ የህግ ባለሙያው። "አሁንም በዝግ ነው ያለው፣በምስጢር ነው ያለው። የክሱ ዐይነት አፍ መዝጊያ ብር መስጠት በራሱ አነስተኛ ወንጀል ነው በራሱ ግን ለሌላ ጥቅም ተብሎ አፍ መዝጊያ ብር ከተሰጠ ለምሳሌ ለፕሬዚዳንትነት ምርጫዬ ያስተጓጉልብኛል ተብሎ ከተሰጠ ግን ከባድ ወንጀል ነው የሚሆነው ማለት ከዐንድ ዓመት በላይ የሚያሳስር ወንጀል ነው። ሌሎቹ ግን ከባድ ወንጀሎች ናቸው።ማለቴ አንድ ሰው ታክስ ሲሞላ፣የውሸት የሆነ የአካውንቲንግ መጣጥፍ ወይም ቁጥር ማስቀመጥ አይችልም።ስለዚህ ብዙዎቹ ከቢዝነሳቸው ጋራ የተያያዙ ከባድ ወንጀሎች ናቸው።"የቀድሞው ፕሬዚደንት ዛሬ በኒውዮርክ ሰዐት አቆጣጠር ከቀትር በኹዋላ ፍርድ ቤት ሲደርሱ፣ ምን እንደሚጠበቅ የተጠየቁት የሕግ ባለሙያው « ፍርድ ቤት ቀርበው ያው ክሱ ይነበብላቸዋል።ክሱ ተነቦላቸው አሻራ ይሰጣሉ።እንደማንኛዉም የኒውዮርክ ተከሳሽ እጃቸውን በካቴና ይታሰርና አሻራ ይሰጣሉ። ከእዛ በኹዋላ ፎቶ ግራፍ "ማግ ሻት"ይባላል። ማንኛውም ኒውዮርክ ውስጥ የሚከሰስ ሰው ወይንም አሜሪን ሃገር የሚከሰስ ሰው፣እንደ ጉርድ ፎቶ ግራፍ ዐይነት ነገር ይነሳል።ከእዛ በኃላ የዋስ መብታቸው ተከብሮ ዋስ ጠርተው የዋስ መብታቸው ተከብሮ ወደቤታቸው ይሄዳሉ።ለቀጠሮ ዕማኝ ዳኞች ፊት ለሚደረግ ክርክር ይቀጠራል።"ሲሉ አብራርተዋል።

ትራምፕ ትናንት ኒውዮርክ ሲገቡ ለደጋፊዎቻቸው ያቀረቡት ሰላምታ ምስል Yuki Iwamur/AP/picture alliance

ከፍተኛ የጸጥታ ጥበቃ በሚደረግለት የትራምፕ የዛሬው የፍርድ ሒደት፣የፎቶ ካሜራ እንጂ የቀጥታ ሥርጭት እንደማኖር የፍርድ ቤቱ ዳኛ ተናግረዋል።ትራምፕ በሚቀርቡባቸው ክሶች ቢፈረድባቸውም እንደጎርጎሮሳዊው ጊዜ አቆጣጠር በ2024 ለሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በጀመሩት ቅስቀሳ በመቀጠል መወዳደር ይችላሉ የሚሉት ዶክተር ፍጹም፣ የሚያሰጋቸው ነገር ቢኖር ሪፐብሊካን ፓርቲያቸውን ሊፈጥባቸው የሚችለው ተግዳሮት እንደሆነ ጠቁመዋል። "ጥያቄው የሚሆነው ፓርቲው፣ እንደዚህ በወንጀል የተከሰሰን ሰዉ፣ ወይንም በወንጀል ጥፋተኛ የተባለው ሰው፣ የእኛ ዕጩ ይሁንልን ብለው ያቀርቡታል ወይ?እንግዲህ ሪፐብሊካን ፓርቲው ነው የሚወስነው።ሪፐብሊካን ፓርቲ ለመመረጥ የሚፈልግ ከሆነ፣እርሱ ወክሎን ከሆነ የምንወዳደረው ምርጫ ላናሸንፍ እንችላለን ብለው ፓርቲው ጫና ሊያበዙበት ይችላሉ። የፓርቲውን አጠቃላይ ስብሰባ በዚህ ሁኔታ ላይ ሊከፋፈል ይችላል።"ብለዋል።

ታሪኩ ኃይሉ 

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW