1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከትግራይ ክልል ወጣቶች በገፍ እየተሰደዱ ነው

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 2 2016

ከትግራይ ክልል ወጣቶች በገፍ እየተሰደዱ መሆኑ ተገለጸ ። በስደት ከክልሉ የሚወጡ ቁጥራቸው የበረከተ ወጣቶች ኅልውናም ለቤተሰቦቻቸው አሳሳቢ እየሆነ ነው ። የትግራይ ክልል አስተዳደር በተለይም ከጦርነቱ በኋላ በትግራይ የወጣቶች ፍልሰት በከፍተኛ መጠን ስለ ማሻቀቡ መረጃዎች እንዳሉት ይገልፃል።

Äthiopien | Arbeitslose Jugendliche in Tigray
ምስል Million H.Selasse/DW

ትግራይ ክልል፦ የገፍ ስደቱ ሰበብ ምን ይሆን?

This browser does not support the audio element.

ከትግራይ ክልል ወጣቶች በገፍ እየተሰደዱ መሆኑ ተገለጸ ። በስደት ከክልሉ የሚወጡ ቁጥራቸው የበረከተ ወጣቶች ኅልውናም ለቤተሰቦቻቸው አሳሳቢ እየሆነ ነው ። የትግራይ ክልል አስተዳደር በተለይም ከጦርነቱ በኋላ በትግራይ የወጣቶች ፍልሰት በከፍተኛ መጠን ስለ ማሻቀቡ መረጃዎች እንዳሉት ይገልፃል። እንደ አስተዳደሩ ገለፃ፦ በአብዛኛው በሀያዎቹ አጋማሽ ያሉ የትግራይ ወጣቶች፥ ከከተማም ከገጠርም በብዛት ወደተለያየ አካባቢዎች እየጓረፉ ነው። ሥራ ማጣት፣ ሌላ ጦርነት ይመጣል ብሎ መስጋት፣ የተሻለና የተረጋጋ ሕይወት መሻት እንዲሁም ሌሎች ምክንያቶች ወጣቶቹ ክልሉን ትተው እንዲሄዱ ከሚያስገድዱ ምክንያቶች መካከል መሆናቸው ተጠቅሷል ። 

ሟቹ የ30 ዓመት ወጣት ደስታ፥ ከቀዬው የትግራይ ክልልዋ አፅቢ ወረዳ ተነስቶ፣ የኢትዮጵያ ድንበር ተሻግሮ፣ በጂቡቲ ወደ የመን፣ ከየመን ሳውዲ አረብያ ድንበር የደረሰው አንድ ወር በፈጀ ጉዞ እንደነበረ ቤተሰቦቹ ነግረውናል። ከአንድ ወር ጉዞ በኋላ ግን የሳውዲ ድንበር ለመሻገር ሲሞክር ኅልፈቱ በመሰማቱ ወላጆቹ፣ ቤተሰቦቹ፣ ወዳጅ ዘመድ፥ መንደር ተሰብስቦ ሐዘን ተቀምጧል።

ይህ ሐዘን የአንድ የኅልፈቱ ዜና የተነገረ ወጣት ብቻ አይመስልም። በርካታ የመንደርዋ ነዋሪዎች ወደተለያየ አቅጣጫ የተሰደዱት ልጆቻቸው ያሉበት ሁኔታ አያውቁም።

ዓለም ሕሉፍ የገጠር ቀበሌዋ አስተዳዳሪ ነው። እንደ ዓለም ገለፃ ስደት በአካባቢያቸው የከፋ ማሕበራዊ ቀውስ ፈጥሯል።

የትግራይ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሓይሽ ስባጋድስ ምስል Million H.Selasse/DW

ከወረዳው አስተዳደር እንደሰማነው በአንድ ዓመት ውስጥ ከትንሿ አፅቢ ወረዳ ብቻ ከ500 በላይ ወጣቶች ወደ ተለያየ ሀገራት ተሰደዋል። በትግራይ በተለይም ከጦርነቱ በኃላ የወጣቶች ስደት በከፍተኛ መጠን እየታየ ይገኛል። የትግራይ ወጣቶች ስራ በማጣት፣ ሌላ ጦርነት በመስጋት፣ የተሻለና የተረጋጋ ሕይወት በመሻት እንዲሁም ሌሎች ምክንያቶች አካባቢያቸው ለቀው ይሰደዳሉ።  በመቐለ ክፍት የስራ ቦታ በሚለጠፍባቸው የማስታወቅያ ሰሌዳዎች እያነበበ አግኝተን ያነጋገርነው ወጣት ሰመረ ፀጋይ ከጦርነቱ በፊት በነበረ ግዜ በምህንድስና በመጀመርያ ዲግሪ የተመረቀ ቢሆንም፥ ለዓመታት ስራ አለማግኘቱ ነግሮናል። ወጣቱ ሰመረ እንደሚለው እርሱና መሰሎቹ ስራ ማጣታቸው ተከትሎ የስደት አመራጭ ጭምር ለመመልከት መገደዳቸው ያነሳል።

የትግራይ ክልል አስተዳደር በተለይም ከጦርነቱ በኋላ በትግራይ የወጣቶች ፍልሰት በከፍተኛ መጠን ማሻቀቡ መረጃዎች እንዳሉት ይገልፃል። እንደ አስተዳደሩ ገለፃ፥ በአብዛኛው በሀያዎቹ አጋማሽ ያሉ የትግራይ ወጣቶች፥ ከከተማም ከገጠርም በብዛት ወደተለያየ አካባቢ እየጓረፉ ነው። የትግራይ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኃላፊው አቶ ሓይሽ ስባጋድስ እንደሚሉት ከሆነ ለወጣቶቹ ስደት በርካታ ምክንያቶች መኖራቸው ያስረዳሉ።

የረሀብ አደጋ በርካቶችን ባሰጋባት ትግራይ ክልል፦ ሥራ ማጣት፣ ሌላ ጦርነት ይመጣል ብሎ መስጋት፣ የተሻለና የተረጋጋ ሕይወት መሻት እንዲሁም ሌሎች ምክንያቶች ወጣቶቹ ክልሉን ትተው እንዲሄዱ ከሚያስገድዱ ምክንያቶች መካከል መሆናቸው ተጠቅሷል ። ምስል Million Haileselassie Brhane/DW

እንደ አቶ ሓይሽ ገለፃ፥ የክልሉ አስተዳደር በስፋት እየታየ ያለው የወጣቶች ፍልሰት ለመቆጣጠር ጥረት እያደረገ ነው የሚሉ ሲሆን የፌደራል መንግስቱ፣ ዓለምአቀፍ ተቋማት እና ሌሎች ፥ ጦርነት ላይ ለቆየችው ትግራይ ትኩረት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW