1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከቻይና የኮሮና ወረርሽኝ አንስቶ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች እይታ ምን ነበር?

ቅዳሜ፣ መጋቢት 12 2012

የኮሮና ወረርሽኝ የማህበራዊ መገናኛ ብዙሀንን ያጨናነቀው ያለ ምክንያት አይደለም። ከጤና ጉዳቱ ባሻገር ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስም ስለሚያስከትል ነው። እንደ የአለም አቀፉ የሰራተኞች ድርጅት ILO ግምት ከሆነ መንግሥታት በፍጥነት ርምጃ ካልወሰዱ እና ለሰራተኞች ድጋፍ ካላደረጉ በአለም ዙሪያ እስከ 25 ሚሊዮን የሚደርሱ ስራዎች ሊታጡ ይችላሉ።

Twitter Logo
ምስል Imago Iamges/Zuma/J. Arriens

ከቻይና የኮሮና ወረርሽኝ አንስቶ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች እይታ ምን ነበር?

This browser does not support the audio element.

ከሁለት ወር ተኩል በፊት የኮሮና ተህዋሲ ቻይና ውስጥ ሲረጋገጥ ለብዙዎች የችግሩ ግዙፍነት ግልጽ አልነበረም። በቻይና ውኃን ከተማ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ሁኔታውን ሲገልጹም ፈተናው የቻይና ብቻ ይመስል ነበር። ስለሆነም በርካታ ኢትዩጵያውያን መንግሥት ዜጐቹን ወደ ሀገሩ እንዲመልስ በተደጋጋሚ አንደ ፌስቡክ ባሉ የመገናኗ ብዙሀን ጠየቁ። የበሽታውን ክብደት የተረዱ አንዳንድ ቻይና ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች ደግሞ ቢመለሱ ተህዋሲውን ወደ ሀገራቸው ሊያስገቡ እንደሚችሉ ስጋታቸውን ገለፁ።
ሌሎች ላልተወሰነ ጊዜ የተደረገው የእንቅስቃሴ እገዳ ያማረራቸው ተማሪዎች ደግሞ መንግሥታችን ከሀገር የምንወጣበትን መንገድ ያመቻችልን ሱሉ ጠየቁ። ጥያቄያቸው ይበልጥ ተሰሚነት ያገኘው ግን የማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች ዘንድ ነበር። ያኔም በመላው ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወደ ቻይና የሚደረገው በረራ እንዲቆም እና ተማሪዎቹ ከቻይና እንዲወጡ የሚል አስተያየት አቀረቡ።  ግን ሳይሆን ቀረ። መጋቢት 4 ቀን ኢትዩጵያም የመጀመሪያው ሰው በተህዋሲው መያዙን ይፋ አደረገች። ታማሚው እንደተሰጋው ከቻይና የገባ ሰው ሳይሆን ከቡርኪና ፋሶ የገባ ጃፓናዊ ነው ተባለ። በዚህ ላይ የማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን ተጠቃሚዎች ምላሽ በአንድ በኩል ንዴት በሌላ በኩል ደግሞ ስጋት ነበር ማለት ይቻላለል።
የታማሚው ቁጥር ኢትዮጵያ ውስጥ ሶስት ፣አምስት፣ ስድስት እያለ ሲጨምርም ቀን በቀን የህዝቡ ስጋት እያየለ መጥቷል። አብዣኞቹ እንደሚሉት አሁንም ተጠየቂው አየር መንገዱ ነው። ምክንያታቸውን ሲያብራሩም በአይሮፕላን ማረፊያ የሚያደርገው ቁጥጥር ብቻውን በቂ አይደለም የሚሉ ይገኙበታል። 
ሌላው ጉዳይ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የተከናወኑ በርካታ ሰዎች የተሰበሰቡባቸው እንደ «ቅድሚያ ለሴቶች» ሩጫ እንዲሁም ለብልፅግና ፓርቲ የገቢ ማሠባሰቢያ የነበሩት ዝግጅቶች ናቸው የህዝቡን ትኩረት የሳቡት። እነሱም ይህንን በማውገዝ መንግሥት የኮሮና ተህዋሲ ስርጭትን ለመቆጣጠር እየወሰደ ያለው ርምጃ በቂ አይደለም ሲሉ ገልጸዋል። ይህ በሆነ ማግስትም ኢትዮጵያ ለ15 ቀናት ትምህርት ቤቶች፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችና ትላልቅ ስብሰባዎችን እንደምትከለክል አስታውቃለች። እንደዛም ሆኖ ርምጃው ለብዙዎች በቂ አልነበረም። ችግሩን የሚያዩን አሁንም ሀገሪቱ የዓለም አቀፍ በረራዎቹን አለማቋረጧ ላይ ነው። 
ሌላው ደግሞ ተህዋሲው ወደ መተንፈሻ አካል እንዳይገባ ለመከላከል እጅን ቶሎ ቶሎ ታጠቡ የሚለው ምክር ጥሩ ሆኖ ሳለ የሚጠጣ ውኃ እንኳን በሌለበት ሀገር ምን የሚሉት ነው? በቂ የውኃ አቅርቦት ያስፈልጋል ሲሉም አስተያየት የሰጡት ብዙ ናቸው።   የተህዋሲው ስርጭት ከቻይና ቀጥሎ የተዛመተበት አውሮፓ እና አሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም ተሞክሮዋቸውን በማጋራት ላይ ይገኛሉ። ሌላው በርካቶች የተወያዩበት ሀሳብ እስካሁን መድሃኒት ላልተገኘለት በሽታ የባህል መድሃኒት ጥሩ ነው ወይስ ጥሩ አይደለም የሚለው እና ከበሽታው ስጋት ጋር በተያያዘ በአንዳንድ ነጋዴዎች ዘንድ የተደረገ የዋጋ ጭማሬ ላይ ነው። 
ልደት አበበ

ምስል Getty Images/L. Dray

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW