1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከአማራ ክልል ሥምምነት የተፈራረመው አገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ አመራሮች ሹመት ይሰጣቸዋል ተባለ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 23 2016

ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የሰላም ሥምምነት የተፈራረመው የአገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ አመራሮች ሹመት እንደሚሰጣቸው ሊቀመንበሩ ተናገሩ። በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አበርገሌ እና ጻግብጂ ወረዳዎች ነፍጥ አንስቶ ከመንግሥት ሲዋጋ የቆየው ንቅናቄ ከክልሉ መንግሥት የተፈራረመውን ሥምምነት ትላንት በሰቆጣ ከተማ ለሕዝብ ይፋ አድርጓል።

 የአገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ አመራሮች በሰቆጣ ከተማ
ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የሰላም ሥምምነት የተፈራረመው የአገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ አመራሮች በክልሉ ሥልጣን እንደሚሰጣቸው ሊቀ መንበሩ ተናግረዋል።ምስል Waghemra Nationality Communication

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና የአገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ስምምነት

This browser does not support the audio element.

የአገው ዴሞክራሲ ንቅናቄ (አዴን) የጥቅምት 2013ቱን የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተከትሎ በአማራ ክልል ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በተለይም በአበርገሌና ፃግብጂ ወረዳዎች ትጥቅ ትግል ሲያካሄድ ቆይቷል፡፡

ታጣቂ ኃይሉ በሁለቱ ወረዳዎች ቆላማ አካባቢዎች እስከ 19 የሚሆኑ ቀበሌዎችን ሲቆጣጠር እንደነበረም ንቅናቄውና የመንግስት አካላት አመልክተዋል፡፡

የአገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ የመንግሰትን የሰላም ጥሪ ተቀብሎ ታህሳስ 13/2016 ዓ ም በአዲስ አበባ ከተማ ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጋር የሰላም ስምምነት ማድረጉንና ትናንት ደግሞ በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ማዕከል ሰቆጣ ከተማ የስምምነቱ አጠቃላይ ይዘት ለህዝብ ይፋ መደረጉን  የንቅናቄው ሊቀመንበር አቶ ኪሮስ ሮምሃ ዛሬ ለዶቼ ቬሌ በስልክ ተናግረዋል፡፡

“ፊርማ የተፈራረምነው ከ5 ጊዜ በላይ ከተመላለስን በኋላ ታህሳስ 13/2016 ዓ ም አዲስ አበባ ነው፡፡ ይፋ ለማድረግ ነው ትናንት ሰቆጣ ከተማ ላይ የተሰባሰብነው፣ ስምምነቱ የተደረገው በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና በአገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ መካከል ነው“ ሲሉ አቶ ኪሮስ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

“ጥያቄያችን በሰላማዊና ህገመንግስታዊ በሆነ መንገድ ለማቅረብ፣ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ደግሞ ግዴታውንእንዲወጣ ማለት ነው” ሲሉ ሊቀመንበሩ አክለዋል።

የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ብልፅግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳግም ባይነሳኝ ታጣቂ ኃይሉ ችግሮቹን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ስምምነት ላይ መድረሱን ገልጠዋል፡፡

በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አበርገሌ እና ጻግብጂ ወረዳዎች ነፍጥ አንስቶ ከመንግሥት ሲዋጋ የቆየው የአገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ከክልሉ መንግሥት የተፈራረመውን ሥምምነት ትላንት በሰቆጣ ከተማ ለሕዝብ ይፋ አድርጓል።ምስል Waghemra Nationality Communication

“ጥያቄዎች አሉኝ፣ ጥያቄዎች ሊመለሱ ይገባል በሚል ወደ ትጥቅ ትግል የገባ ኃይል ነበር” የሚሉት የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ብልፅግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጋር በተደረገ የሰላም ውይይት ከሥምምነት መደረሱን አረጋግጠዋል።

”ቡድኑ ከዚህ በኋላ በሚኖረው ሂደት አሉኝ የሚላቸውን ጥያቄዎች ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ወደ ህብረተሰቡ ተቀላቅየ ያለኝን ዓላማ አሳካለሁ በሚል የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ለዚህ ቡድን ባስተላለፈው የሰላም ጥሪመሰረት ትናንት በሰቆጣ ከተማ ታላላቅ የሐይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወታደራዊ አዛዦችና የክልል ከፍተኛ ኃላፊዎች በተገኙበት በሰላም ስምምነቱ ዙሪያ ውይይት ተደርጎ ለህዝብ ይፋ ሆኗል” ብለዋል፡፡

የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኃይሉ ግርማይ በበኩላቸው የአገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ ሆኖ ለመንቀሳቀስ ስምምነት ላይ ደርሷል ብለዋል። ንቅናቄው አሉኝ የሚላቸውን ጥያቄዎችም በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጋር የጋራ መግባባት ላይ መድረሱን ገልጠዋል፡፡

የአገው ዴሞክራሲ ንቅናቄ  ሊቀመንበር አቶ ኪሮስ ሮምሃ እንደሚሉት የአገው ህዝብ ራሱን በራሱ ማስተዳደር መብት ተነፍጎታል። የፍትሀዊነትና የእኩልነት ጥያቄዎች አሉበት በሚል ትያቄዎቹን ለመመለስ የትጥቅ ትግል ሲያካሂድ ነበር፡፡ ሆኖም የትጥቅ ትግል አስፈላጊ አለመሆኑን አውቆ ንቅናቄው ወደ ሰላም መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

የአገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ እና የአማራ ክልላዊ መንግሥት የሰላም ሥምምነት የተፈራረሙት ከረዥም ድርድር በኋላ ነውምስል Privat

የታጣቂዎቹን የወደፊት እጣፋንታ በተመለከተ አቶ ኪሮስ “የሚሰሩ ተግባራት አሉ፣መደበኛ ድርደር ነው ያደረግነው፣ በማንነታቸው ምክንት ከስራ የተባረሩ የመንግስት ሰራተኞች የአገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ በሚያቀርበው ዝርዝር መሰረት ወደ ነበሩበት እንደሚለሱ ይደረጋል፣ አመራር የነበሩ ግን በማንነታቸው ምክንት ከክልል የወጡ አካላት ተሐድሶ ከወሰዱ በኋላ ክልሉ በሚያመቻቸው መንገድ በሲቪልና በልማት ተቋማት ላይ በከፍተኛ እርከኖች ላይ ኃላፊነት በልዩ ሁኔታ የሚሰጥ ይሆናል” ብለዋል። 

አንዳንድ አካላት የአገው ሸንጎንና የአገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄን በተመለከተ ብዥታ እንዳለባቸው የጠቆሙት አቶ ኪሮስ ሁለቱ ድርጅቶች ተለያዩ መሆናቸውን  ግልፅ አደርገዋል፡፡

“አገው ሸንጎ የአገው ህዝብን ጥያቄ እፈታለሁ ብሎ በምርጫ ቦርድ እውቅና ያለው ፓርቲ ነው፣ እኛ (የአገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ) በስልትና አጠቃላይ በአለን የአገው ህዝብ ግንዛቤ  በከፍተኛ ደረጃ ልዩነት አለን፣ ምንም ዓይነት ግንኙነት የለንም” ነው ያሉት። 

የአገው ዴሞክራሲ ንቅናቄ ለአለፉት 3 ዓመታት በአማራ ክልል ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በአበርገሌና ፃግብጂ ወረዳዎች በ19 ያህል ቀበሌዎች ነፍጥ አንስቶ ከመንግስት ጋር ሲዋጋ የነበረ ታጣቂ ኃይል ነው፡፡

ዓለምነው መኮንን

እሸቴ በቀለ

ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW