1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካሰሜን አሜሪካ

ከአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ጆ ባይደን ሲሰናበቱ ዶናልድ ትራምፕ ተፎካካሪያቸውን እየጠበቁ ነው

ሰኞ፣ ሐምሌ 15 2016

ጆ ባይደን ከአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ራሳቸውን ሲያገልሉ ይሁንታቸውን ለካማላ ሐሪስ ሰጥተዋል። ሐሪስ የሥመ-ጥር ዴሞክራቶችን ድጋፍ ቢያገኙም በይፋ የፓርቲው እጩ መሆናቸው የሚታወቀው በነሐሴ ነው። “ግብጽ የህዳሴ ግድብን ታፈርሳለች” ብለው ኢትዮጵያን ያስቆጡት፤ አፍሪካን በአጸያፊ ቋንቋ የጠሩት ዶናልድ ትራምፕ ተቀናቃኛቸውን ለመለየት ይጠብቃሉ

ዶናልድ ትራምፕ እና ካማላ ሐሪስ
ምክትል ፕሬዝደንት ካማላ ሐሪስ የዴሞክራቶች ፓርቲ እጩ ከሆኑ 47ኛ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ለመሆን ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ይፎካከራሉምስል Evan Vucci/AP/dpa/picture alliance | Shawn Thew/Pool EPA/AP/picture alliance

ከአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ጆ ባይደን ሲሰናበቱ ዶናልድ ትራም ተፎካካሪያቸውን እየጠበቁ ነው

This browser does not support the audio element.

የአሜካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን በስተ-መጨረሻ እጅ ሰጡ። የ81 ዓመቱ አዛውንት ጥቅምት 26 ቀን 2017 ከሚካሔደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ራሳቸውን እንዲያገልሉ ከዴሞክራቲክ ፓርቲ ጫና በርትቶባቸው ነበር። ከተደጋጋሚ ማንገራገር በኋላ ትላንት እሁድ ሐምሌ 14 ቀን 2016 የተጠየቁትን አደረጉ።

በማኅበራዊ ድረ-ገጾች በተሠራጨ ደብዳቤያቸው ባይደን ከምርጫ ራሳቸውን አግልለው በቀሪ የፕሬዝደንትነት ዘመናቸው የተጣለባቸውን ኃላፊነት መወጣት ለፓርቲያቸው እና ለሀገራቸው አሜሪካ ይበጃል የሚል ዕምነት እንዳላቸው ገልጸዋል። ባይደን በሥልጣን ላይ እያሉ ከፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ራሳቸውን በማግለል ባለፉት 56 ዓመታት የአሜሪካ ፖለቲካ የመጀመሪያው ናቸው።

ፕሬዝደንቱ ባለፉት ወራት ሐሳባቸውን መሰብሰብ፣ ንግግሮቻቸውን ማደራጀት ሲሳናቸው ታይተዋል። አረፍተ-ነገሮቻቸውን ለማጠናቀቅ ዘገምተኛ ይሆናሉ፤ ነገር ይዘነጋሉ፤ ሥም ያምታታሉ። ባለፈው ሣምንት በዋሽንግተን ዲሲ በተካሔደው የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል-ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ስብሰባ የዩክሬን ፕሬዝደንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪን በስሕተት “ፕሬዝደንት ፑቲን” ሲሉ ጠርተዋቸዋል።

ባይደን ከቀድሞው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ባለፈው ሰኔ ባደረጉት የፊት ለፊት ክርክር አንደበታቸው እንዳሻቸው አልታዘዝ እያለ፤ ቃላቶቻቸውም እየተደነቃቀፉ ከተቸገሩ በኋላ ነበር እጩነታቸው ይበልጥ ጥያቄ ውስጥ የወደቀው።

ረዳቶቻቸው ለደካማ ክርክራቸው በርካታ ማሳበቢያዎች ቢያቀርቡም በአንድ ጋዜጣዊ መግለጫ ምክትላቸው ኻሚላ ሐሪስን “ምክትል ፕሬዝደንት ትራምፕ” እያሉ ጥብቅና የቆሙላቸውን መልሰው አሳፈሩ። እንዲያም ሆኖ እስከ እሁድ ድረስ “በፕሬዝደንትነት ለመወዳደር ከፍተኛ ብቃት ያለው ሰው እኔ ነኝ። አንድ ጊዜ አሸንፌዋለሁ፤ ደግሜ አሸንፈዋለሁ” ይሉ ነበር።

ለአምስት አስርት ዓመታት ገደማ በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ የቆዩት ጆ ባይደን ባለፉት ወራት ሐሳባቸውን መሰብሰብ፣ ንግግሮቻቸውን ማደራጀት ሲሳናቸው ታይተዋል። ምስል Matt Rourke/AP Photo/picture alliance

ባይደን ለ50 ዓመታት ገደማ በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ ቆይተዋል። ለ36 ዓመታት በሴናተርነት ዴልዌርን ወክለዋል። ሴናተር ሳሉ ሳዳም ሁሴይንን ከሥልጣን ለማስወገድ አሜሪካ ኢራቅን እንድትወር የደገፉ ቢሆንም የኋላ ኋላ ዘመቻው አላስፈላጊ እንደነበር አምነዋል። ከአንዴም ሁለት ጊዜ ለፕሬዝደንትነት ተወዳድረው ሳይሳካላቸው ቢቀርም ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ዋይት ሐውስ የገቡት የባራክ ኦባማ ምክትል ሆነው ነበር።

በጥቅምት 2013 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዶናልድ ትርምፕን አሸንፈው ዋይት ሐውስ የገቡት ባይደን ለሁለተኛ የሥልጣን ዘመን ለመወዳደር ቁርጠኛ ቢሆኑም ገለል እንዲሉ ግፊት በበረታባቸው ወቅት ምክትላቸው ካማላ ሐሪስ “በፕሬዝዳንታችን ጆ ባይደን እና በቆሙለት ዓላማ እምነት አለን” እያሉ ጥብቅና ቆመውላቸዋል። ባራክ ኦባማ ምክትላቸው ጆ ባይደን ለፕሬዝደንትነት ሲወዳደሩ ድጋፍ በማሰባሰብ ከፍተኛ ሚና እንደተጫወቱ ሁሉ አሁን ባይደን በተራቸው ካማላ ሐሪስ እንዲተኳቸው ቡራኬ ሰጥተዋል።

የታሪክ አዋቂው ዳግላስ ብሪንክሌይ እንደሚሉት ባይደን ከፕሬዝዳንታዊው ምርጫ ራሳቸውን ማግለላቸው “አስደንጋጭ” አይደለም። “ሰዎች ባይደን በስተመጨረሻ ራሳቸውን በማግለል ትክክለኛውን ነገር ማድረጋቸውን ያስታውሳሉ” የሚሉት ብሪንክሌይ ባይደን ካማላ ሐሪስን በምክትል ፕሬዝደንትነት መምረጣቸው 80 ሚሊዮን አሜሪካውያን ድምጽ እንደሰጧቸው በማስታወስ “አሁን ሐሪስ ለፕሬዝደንትነት ሲወዳደሩ ባይደን እንደ አሰልጣኝ ሊረዷቸው ይችላሉ” ሲሉ ተናግረዋል።

የመጀመሪያዋ ሴት የአሜሪካ ፕሬዝደንት ካማላ ሐሪስ?

የባይደን ዴሞክራቲክ ፓርቲ የመጀመሪያዋ ሴት እና ጥቁር ምክትል ፕሬዝደንት ሆነው ታሪክ የጻፉት ካማላ ሐሪስን በመጪው ጥቅምት ለሚካሔደው ምርጫ በእጩነት ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል። የ59 ዓመቷ ሐሪስ በካሊፎርኒያ ይወለዱ እንጂ እናታቸው ከሕንድ አባታቸው ከጃማይካ ናቸው። ለስምንት ዓመታት የካሊፎርኒያ ግዛት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሆነው ሠርተዋል። ወደ ሴኔት ያመሩት በጎርጎሮሳዊው 2016 ሲሆን በወቅቱ ፕሬዝደንት የነበሩት ዶናልድ ትራምፕን የፍልሰት ፖሊሲ በጥብቅ በመተቸት ይታወቃሉ።

ካማላ በዕጩነት ለመቅረብ ነሐሴ 11 ቀን 2016 በሚካሔደው የዴሞክራቶች ብሔራዊ ጉባኤ የ1,986 ተወካዮችን ይሁንታ ማግኘት ይኖርባቸዋል። ፓርቲው ሐሪስ በእጩነት እንዲቀርቡ ይተባበራል ወይስ ሌላ አማራጭ ለማቅረብ ግብግብ ይፈጠራል የሚለው እስካሁን በውል አለየም።

የዘር ሐረጋቸው ከጃማይካ እና ከሕንድ የሚመዘዘው ካማላ ሐሪስ የዴሞክራት ፓርቲ ዕጩ ሆነው ዶናልድ ትራምፕን ቢያሸንፉ የመጀመሪያዋ የአሜሪካ ሴት ፕሬዝደንት ይሆናሉ። ምስል Avalon/Photoshot/picture alliance

የቀድሞው ፕሬዝደንት ቢል ክሊንተን እና ባለቤታቸው ሔላሪ ክሊንተን፣ የካሊፎርኒያ አገረ ገዢ ጋቪን ኒውሰም፣ የፔንሴልቫኒያ አቻቸው ጆሽ ሻፒሮ፣ የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ፒት ቡቲጄጅ፣ የቀድሞው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪን ጨምሮ በዴሞክራቲክ ፓርቲ ውስጥ ተደማጭ የሆኑ ፖለቲከኞች በይፋ ካማላን ደግፈዋል። የማሳቹሴትስ ሴናተር የሆኑት ኤልዛቤጥ ዋረን ካማላ ሐሪስ የዴሞክራቶቹ እጩ ቢሆኑ ፓርቲውን ማስተባበር ብቻ ሳይሆን ትራምፕን ማሸነፍ እንደሚችሉ ያምናሉ። 

አሶሼትድ ፕሬስ፣ ሲኤንኤን እና ኒው ዮርክ ታይምስን የመሳሰሉ ሚዲያዎች በተናጠል እና ከሌሎች ተቋማት ጋር በጥምረት ባከናወኗቸው መጠይቆች የ59 አመቷ ካማላ ሐሪስ ከባይደን የተሻለ የማሸነፍ ዕድል እንዳላቸው የሚጠቁም አስተያየት አግኝተዋል።

አመጻን እንደ መሣሪያ?

የባይደን ተተኪ ካማላ ሐሪስም ሆኑ ሌላ፤ ተቀናቃኛቸው ዶናልድ ትራምፕ ይሆናሉ። ባለፈው ሣምንት በይፋ የሪፐብሊካን እጩ መሆናቸው የታወጀው የ78 ዓመቱ ቢሊየነር ውጤቱን በጸጋ ባይቀበሉም በምርጫ ወደ ተሰናበቱት ዋይት ሐውስ ለመመለስ ሲዘጋጁ ቆይተዋል። ለምክትል ፕሬዝዳንትነት የመረጧቸው ጄዲ ቫንስ ኢራቅ የዘመቱ ወግ አጥባቂ ናቸው።

ከትዳራቸው ውጪ የነበራቸውን ወሲባዊ ግንኙነት ለመሸፋፈን አፍ ማስዘጊያ ከፍለው የተጭበረበረ ሒሳብ በማዘጋጀት በቀረቡባቸው ተደራራቢ ክሶች ጥፋተኛ የተባሉት ትራምፕ ለፕሬዝደንትነት የመወዳደር ዕድላቸው ሲያወዛግብ ቢቆይም የተደረገባቸው የግድያ ሙከራ በደጋፊዎቻቸው ዘንድ አርበኛ አድርጓቸዋል።

በቺካጎ ዩኒቨርሲቲ የደሕንነት እና ሥጋት ምርምር ፕሮጀክት ከግድያ ሙከራው ሁለት ሣምንታት በፊት ባከናወነው ጥናት ትራምፕን ከፕሬዝደንትነት ለማቆም 10 በመቶ አሜሪካውያን ጎልማሶች ወይም 24 ሚሊዮን ሰዎች ኃይል መጠቀምን እንደሚደግፉ ደርሶበታል። ከአሜሪካ ጎልማሶች 7 በመቶ በአንጻሩ ዶናልድ ትራምፕን ለአራት ዓመታት ወዳገለገሉበት ፕሬዝደነትነት ለመመለስ ኃይል መጠቀምን ይደግፋሉ።

ዶናልድ ትራምፕን ለመግደል የሞከረው ቶማስ ማቲው የተባለ የ20 ዓመት ወጣት ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ያጠናቀቀው በጎርጎሮሳዊው 2022 ነው። ምስል Bethel Park School District via AP/picture alliance

በመጠይቁ ኃይል መጠቀምን እንደሚደግፉ የገለጹት አሜሪካውያን “ራሳቸው አመጸኛ ይሆናሉ” ማለት ባይሆንም የፕሮጀክቱ ኃላፊ እና የቺካጎ ዩኒቨርሲ ፕሮፌሰር የሆኑት ሮበርት ፔፕ ግን “በፖለቲካችን ውስጥ አክራሪዎች አሉ። ሁለቱም ቁጥራቸው ጥቂት እንዳልሆነ መገንዘብ ጠቃሚ ነው። አንድ ላይ ሲደመሩ ደግሞ ቁጥራቸው ከፍተኛ ይሆናል” ሲሉ ጉዳዩ አሳሳቢ እንደሆነ ገልጸዋል።

በፔንሲልቫኒያ ግዛት በትለር የተባለች ከተማ ትራምፕን በጥይት ያቆሰላቸው የ20 ዓመቱ ወጣት ቶማስ ማቲው ክሮክስ ለጥቃቱ በቅጡ እንደተዘጋጀ በተሽከርካሪው ውስጥ የተገኙ ሁለት ፈንጂ ቁሳቁሶች እና የቀድሞው ፕሬዝደንት ንግግር ባደረጉበት ቦታ ለቅኝት ያበረረው ሰው አልባ አውሮፕላን ይጠቁማሉ። በቀድሞው ፕሬዝደንት ላይ በተኮሰበት ቦታ የተገደለው ተጠርጣሪ ሪፐብሊካን ሆኖ የተመዘገበ፤ የ17 ዓመት ወጣት ሳለ ለግራ ዘመም ዴሞክራት ፖለቲከኞች ድጋፍ ለሚያሰባስብ ድርጅት 15 ዶላር የለገሰ ሆኖ ተገኝቷል።

የወጣቱ የግድያ ሙከራ ገፊ ምክንያት ባይታወቅም ሮያል ዩናይትድ ሰርቪስ ኢንስቲትዩት የተባለው የመከላከያ እና ጸጥታ ጥናት ተቋም ኃላፊ ካሪን ቮን ሒፐል “በጥር 2021 በካፒቶል ሒል በተፈጸመው ጥቃት ሰዎች መሞታቸው መዘንጋት የለበትም። መከፋፈሉ ተጠናክሮ በሁለቱም ወገኖች ፖለቲካዊ ንግግሮች እየተባባሰ ሔዷል” ሲሉ ኹከት ለአሜሪካ ፖለቲካ እንግዳ እንዳልሆነ መዘንጋት እንደሌለበት ያስታውሳሉ።

ከግድያ ሙከራው በኋላ ፕሬዝደንት ጆ ባይደንም ሆኑ ዶናልድ ትራምፕ የፖለቲካ ትኩሳት የወለደውን ውጥረት ማርገብ እንደሚያስፈልግ በአጽንዖት ተማጽነዋል። ባለፈው ሣምንት በሚልዎኪ በተካሔደው የሪፐብሊካን ፓርቲ ብሔራዊ ጉባኤ ለደጋፊዎቻቸው 90 ደቂቃዎች ገደማ የረዘመ ንግግር ያደረጉት ትራምፕ በመጀመሪያዎቹ 28 ደቂቃዎች ለዘብ ብለው ብለው ነበር። ከዚያ ግን የቀድሞው ትራምፕ ተመለሱ።

“በሕብረተሰባችን ውስጥ ያለው አለመግባባት እና መከፋፈል መፈወስ አለበት” ሲሉ የሰበኩት ትራምፕ መልሰው ዴሞክራቶቹን “ዴሞክራሲን በማጥፋት” ወንጅለዋል። ተመልሰው ወደ ዋይት ሐውስ ከገቡ ወደ አሜሪካ የሚደረገውን ለማቆም ፍልሰት ቆምጠጥ ያለ እርምጃ እንደሚወስዱ እና የግብር ክፍያን እንደሚቀንሱ ለአሜሪካውያን ቃል ገብተዋል።

የሪፐብሊካን እጩ መሆናቸውን በይፋ ያረጋገጡት የቀድሞው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ “ለዴሞክራሲ ስል በጥይት ተመታሁ” ሲሉ ለደጋፊዎቻቸው ተናግረዋል። ምስል Matt Rourke/AP Photo/picture alliance

“በእኛ አመራር ዩናይትድ ስቴትስ እንደገና ትከበራለች። ማንም ሀገር ኃይላችንን አይጠይቅም፤ የትኛውም ጠላት ጉልበታችንን አይጠራጠርም” ያሉት የቀድሞው ፕሬዝደንት “ድንበሮቻችን ሙሉ በሙሉ የተጠበቁ ይሆናሉ፤ ኤኮኖሚያችን ያድጋል። ሕግ እና ሥርዓት በከተሞቻችን አውራ ጎዳናዎች፤ አርበኝነት በትምህርት ቤቶቻችን ይመለሳል” ሲሉ ተደምጠዋል።

“በመላው ዓለም ሰላም፣ መረጋጋት እና መስማማትን እናሰፍናለን” ያሉት ትራምፕ “ይኸን ለማድረግ ግን መጀመሪያ ሀገራችንን ከወደቀ እና አቅም አልባ አመራር መታደግ ይኖርብናል። የአሁኑ አመራር ሙሉ በሙሉ አቅመ-ቢስ ነው” እያሉ የጆ ባይደንን አስተዳደር ወርፈዋል።

በሚቀጥለው ዓመት የሚካሔደው ምርጫ ከኢትዮጵያ እስከ ሱዳን፤ ከኢራን እስከ ቻይና ዓለም በአይነ-ቁራኛ የሚከታተለው ነው። የምርጫው አሸናፊ ማንነት ሀገራት በሚከተሉት የውጭ ፖሊሲ ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተጽዕኖ ይኖረዋል።

በተለይ የሩሲያ እና ዩክሬን መሪዎች፣ የእስራኤል እና የፍልስጤም ተፋላሚዎች 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ማንነት አብዝቶ ያሳስባቸዋል። ፕሬዝደንት ጆ ባይደን በዩክሬን ጦርነት ለፕሬዝደንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ መንግሥት ከፍተኛ ድጋፍ ሲያቀርቡ ነበር። ሐማስ መስከረም 26 ቀን 2016 ከፈጸመው ጥቃት በኋላ ለእስራኤል ያላቸውን ከፍተኛ ድጋፍ ያሳዩት ባይደን ሰብአዊ ቀውሱ እየበረታ ሲሔድ በጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ መንግሥት ላይ ቆፍጠን የማለት አዝማሚያ አሳይተው ነበር። ሁለቱ ጦርነቶች ዶናልድ ትራምፕ ለምረጡኝ ዘመቻ የሚቀሰቅሱባቸው ኹነኛ የውጭ ፖሊሲ አጀንዳ ሆነውላቸዋል።

“እኔ ፕሬዝደንት ብሆን ኖሮ ሊቀሰቀስ የማይችለውን የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት ጨምሮ የአሁኑ አስተዳደር የፈጠራቸውን እያንዳንዳቸውን ዓለም አቀፍ ቀውሶች አቆማለሁ” ሲሉ ዶናልድ ትራምፕ ፈክረዋል። እስራኤል እና የፍልስጤም ታጣቂዎች የሚያደርጉት 39 ሺሕ ገደማ ሰዎች የተገደሉበት የጋዛ ጦርነት “ፕሬዝደንት ብሆን ኖሮ ሊፈጠር አይችልም ነበር” ያሉት ትራምፕ ሥልጣን ቢይዙ እንደሚያቆሙት ቃል ገብተዋል።

ትራምፕ በጥቅምት በሚካሔደው ምርጫ ማን እንደሚወዳደራቸው በሚቀጥለው ወር ይታወቃል። ካማላ ሐሪስ በእጩነት ቀርበው ምርጫውን ካሸነፉ የመጀመሪያዋ ሴት የአሜሪካ ፕሬዝደንት ይሆናሉ። ዋይት ሐውስን እያለሙ ባይደንን ሲያብጠለጥሉ የቆዩት ትራምፕ አሁን ፊታቸውን ወደ ካማላ ሐሪስ ማዞራቸው አይቀርም።

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW