1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከአሮጌው ዓመት ወደ አዲሱ ስፖርታዊ ክንዋኔዎች

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 22 2016

ከአትሌቲክስ መረጃዎች ፤ ኬንያዊቷ አትሌት ቢአትሪክ ቼቤት ትናንት እሁድ ባርሴሎና ውስጥ በተደረገው የ5 ኪ/ሜ የጎዳና ሩጫ አዲስ የዓለም ክብረወሰን በማስመዝገብ አሸነፋለች። ቼቤት በጎርጎርሳውያን አዲስ ዓመት ዋዜማ የራሷ ባደረገችው በዚሁ ክብረ ወሰን የገባችበት ሰዓት 14 ደቂቃ ከ13 ሰከንድ ሆኖ ተመዝግቧል።

USA Sport l Highschool in Iowa l Läufer im 3200-Meter-Lauf
ምስል Charlie Neibergall/AP/picture alliance

የታህሳስ 22 ቀን 2016 ዓ.ም የስፖርት ዝግጅት

This browser does not support the audio element.

የጎርጎርሳውያኑን አሮጌ ዓመት 2023ን ሸኝተን አዲሱን 2024 ዓ/ም በድምቀት ተቀበልን። በጎርጎርሳውያኑ የቀን ቀመር ለምትከተሉ አድማጮቻችን በዶይቼ ቬለ የስፖርት ዝግጅት ስም እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ ለማለት እንወዳለን ። በዛሬው የስፖርት ዝግጅታችን የሰሞንኛ ዋናዋና ስፖርታዊ ክንዋኔዎችን ጨምሮ በአዲሱ ዓመት የሚጠበቁ ዋና ዋና ስፖርታዊ ኩነቶችን እንቃኛለን ።

 ከአትሌቲክስ መረጃዎች ፤ ኬንያዊቷ አትሌት ቢአትሪክ ቼቤት ትናንት እሁድ ባርሴሎና ውስጥ በተደረገው የ5 ኪ/ሜ የጎዳና ሩጫ አዲስ የዓለም ክብረወሰን በማስመዝገብ አሸነፋለች። ቼቤት በጎርጎርሳውያን አዲስ ዓመት ዋዜማ የራሷ ባደረገችው በዚሁ ክብረ ወሰን የገባችበት ሰዓት 14 ደቂቃ ከ13 ሰከንድ ሆኖ ተመዝግቧል። የቼቤት አዲሱ የዓለም የአምስት ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ክብረ ወሰን ቀደም ሲል በኢትዮጵያዊቷ ሰንበሬ ተፈሪ ተይዞ የነበረ ሲሆን ቼቤት ይህንኑ በ16 ሰከንዶች ማሻሻል ችላለች። በውድድሩ ኢትዮጵያዊቷ እጅጋየሁ ታዬ ሁለተኛ ስትወጣ ሌላኛዋ ኬንያዊት ሊሊያን ሬንጌሩክ ሶስተኛ ወጥታለች። በወንዶቹ ምድብ የተደረገውን ውድድር ደቡብ ሱዳናዊው የ25 ዓመት ወጣት ዶሚኒክ ሎባሉ አሸናፊ ሆኗል። የታኅሣሥ 8 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
የተጠናቀቀው የጎርጎርሳውያኑ 2023 በተለይ በአምስት ሺ ሜትር የሴቶች የሩጫ ውድድር ታሪካዊ ክስተቶችን አስተናግዶ ማለፉን ዓለማቀፉ የአትሌቲክስ ማህበር ገልጿል። ማህበሩ በዓመቱ ውስጥ የተከናወኑ አበይት አትሌቲክሳዊ ሁነቶችን ጠቅሶ ባወጣው ዘገባው በተለይ የሴቶች አምስት ሺ ሜትር የሩጫ ውድድር በአንድ ዓመት ውስጥ ሁለት ጊዜ ክብረ ወሰን መሰበሩ አስደናቂ እንደነበር ገልጿል። በዓመቱ በመጀመሪያ  የርቀቱን ክብረ ወሰን በኢትዮጵያዊቷ ለተሰንበት ግደይ በ14 ደቂቃ 06 ሰከንስ ከ62 ማይክሮ ሰከንድ ተይዞ የነበረ ሲሆን ኬንያዊቷ ፌዝ ኪፒገን በአንድ ሰከንድ በማሻሻል የራሷ አድርጋ ነበር ። ነገር ግን ይህ ከጥቂት ወራት አልተሻገረም ።

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች፦ በቡዳፔስት የ19,000 ሜትር ሩጫ ፉክክር የወርቅ ሜዳይ ባለድል ጉዳፍ ጸጋዬ (ከመሀል) ለተሰንበት ግደይ የብር ሜዳይ ባለድል (ከግራ) እንዲሁም በስተቀኝ የነሐስ ሜዳሊያ ባለድል እጅጋየሁ ታዬ ።ፎቶ ከማኅደርምስል Antonin Thuillier/AFP

ሌላዋ ኢትዮጵያዊት ጉዳፍ ጸጋይ በአሜሪካው ኤውጅን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና መድረክ ከ5 ሰከንዶች በላይ በማሻሻል 14 ደቂቃ ከ00 በመግባት ክብረ ወሰኑን በስሟ እና በሃገሯ ስም ማስመዝገብ ችላለች። በዓመቱ በርቀቱ የተመዘገቡ አስር ምርጥ ሰዓቶች ከእስካሁኖቹ ሁሉ ፈጣኖች የነበሩ እንደነበር የገለጸው ዓለማቀፉ የአትሌቲክስ ማህበር አራቱ በኢትዮጵያውያን አትሌቶች የተመዘገቡ እንደነበር አክሏል። 

በተገባደደው በተሸኘው የ2023 የኦለም የአየር ንብረት ለውጥ ሁለት ሶስተኛ በሚሆኑ አትሌቶች ላይ ተጽዖኖ ማሳደሩን ባደረገው ጥናት ማረጋገጡን ዓለማቀፉ የአትሌቲክስ ማህበር ይፋ አድርጓል። የአየር ንብረት ለውጡ በአትሌቶች ወቅታዊ ብቃት ብሎም ከ85 በመቶ በላይ በሚሆኑት ላይ ከውድድር በኋላ አሉታዊ የጤና ችግር በማስከተል ተጽዕኖ ማሳደሩን ማህበሩ አስታውቋል። በጥናቱ ውስጥ ከተካተቱ አትሌቶች ውስጥ 90 በመቶ የሚሆኑት ውድድሩን የሚመራው ዓለም አቀፍ ተቋም ወደፊት ለውድድሮች ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር መስራት እንዳለበት አሳስበዋል። 400 ያህል በጥናቱ ውስጥ የተካተቱት አትሌቶች በቡዳፔስቱ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የተካፈሉ እንደነበር ማህበሩ ጠቅሷል። አትሌቶቹ ከጤናቸው ባሻገር ስፖርቱ በራሱ ለችግር መጋለጡ ግንዛቤ ሊያዝበት ይገባል ብለዋል።

የርምጃ ተፎካካሪዎች በቻይና አትሌቲክስ ውድድር። ፎቶ ከማኅደር ምስል picture-alliance/dpa/C. Charisius

ከአትሌቲክ ዜና ሳንወጣ ዛሬ አንድ አስደንጋጭ እና አሳዛኝ ዜና ከወደ ኬንያ ተሰምቷል። ዩጋንዳዊው የመሰናክል ሩጫ ተወዳዳሪ አትሌት  ኬንያ ውስጥ አንጋፋ አትሌቶች ልምምድ በሚያደርጉባት ኤልዶሬት በተባለች ከተማ ተሽከርካሪ ውስጥ ህይወቱ አልፎ ተገኝቷል። የ34 ዓመቱ አትሌት ቤንጃሚን ኪፕላጋት በስለት መሳሪያ በደረሰበት ጥቃት ህይወቱ ሳታልፍ እንዳልቀረ ዘገባዎች አመልክተዋል። ዩጋንዳን በሶስት ዓለማቀፍ ውድድሮች እንደወከላት የተነገረለት አትሌቱ በለንደኑ የ2004 ኦሎምፒክ በሶስት ሺ መሰናክል ግማሽ ፍጻሜ ደርሶ ነበር። የኬንያ ፖሊስ ስለ አሟሟቱ ምርመራ መክፈቱን ይግለጽ እንጂ ወንጀሉን የፈጸሙ ሰዎች በቁጥጥር ስር ስለመዋላቸው የተባለ ነገር የለም። የዓለም አትሌቲክስ ማህበር በአትሌቱ ሞት ድንጋጤ መፈጠሩን ገልጾ አሟሟቱን ደግሞ እጅጉን አሳዛኝ ብሎታል። 

አዲሱ የጎርጎርሳውያን ዓመት ኢትዮጵያ የምትካፈልባቸው እና ተጠባቂዎቹ ስፖርታዊ የውድድር መድረኮች የትኞቹ ይሆኑ ? በተለይ በአትሌቲክስ እና እግር ኳስ ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት የምትካፈልባቸውን የውድድር አይነቶች መቼ እና የት እንደሚከናወኑ የአዲስ አበባው ተባባሪ ዘጋቢያችን ምስጋናው ታደሰ በስልክ ያደረሰን አጭር ማብራሪያ ይዘናል ፤ ለድምጽ ጥራቱ ይቅርታ እየጠየቅን ከምስጋናው መረጃ በኋላ በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ መረጃዎች እንገናኛለን ፤ ምስጋናው ።
በእግር ኳስ ዜናዎች የታኅሣስ 1 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ


በሳምንቱ የገና ሰሞን የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ተጠባቂ ጫወታዎችን አስተናግዷል።  ሊቨር ፑል ነጥቡን 42 በማድረስ አዲሱን ዓመት የሊጉ መሪ በመሆን ሲቀበል አርሰናል በሜዳው እና ከሜዳው ውጭ በደረሰበት ተከታታይ ሽንፈት ወደ አራተኛነት ተንሸራቷል። በውድድር ዓመቱ በጥሩ ግስጋሴ ላይ የሚገኘው አስቶን ቪላ የ20ኛ ሳምንት መርሃ ግብሩን በርንሌይን ድራማዊ በሆነ መልኩ 3 ለ 2 ካሸነፈ በኋላ ነጥቡን ከሊቨርፑል በማስተካከል በጎል ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ባለፈው ቅዳሜ በሜዳው ማንችስተር ሲቲን ያስተናገደው ማንችስተር ሲቲም ከተከታታይ ነጥብ መጣል በኋላ በተከታታይ ማሸነፍ የቻለበትን ውጤት በማስመዝገብ ዛሬ ምሽት ከኒውካስል ዩናይትድ ጋር የሚያደርገው ጫወታ እንደተጠበቀ ሆኖ በ40 ነጦቦች በሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

የሊቨርፑሉ አጥቂ ሞሐመድ ሳላህምስል Jon Super/AP Photo/picture alliance

የሊጉን የመጀመሪያ አጋማሽ በጥሩ ግስጋሴ ላይ የነበረው አርሴናል በተከታታይ ካደረጋቸው ሶስት ጫወታዎች ማግኘት የቻለው አንድ ነጥብ ብቻ ነበር ። ከሊቨርፑል ጋር ባደረገው ጫወታ ፤ ከዚያ በኋላ ግን በሜዳው ዌስትሃምን አስተናግዶ 2 ለ 0 እንዲሁም ወደ ምዕራብ ለንደን ተጉዞ ከፉልሃም ጋር ያደረገውን ጫወታ ሁለት ለዜሮ በመሸነፍ ነጥቡ 40 ላይ እንዲገታ ኣ,ድርጓል። በዚህ የማይክል አርቴታ ቡድን የማጥቃት እንቅስቃሴ ጥያቄ ሲነሳበት ከፊታችን ባለው የጥር የዝውውር መስኮት በሚኖረው ተሳትፎ ላይ ጫና ሳያሳድርበት እንደማይቀር ተገምቷል። 
በዝውውር ወሬዎች ጭምጭታዎች አንዳንድ የፕሪምየር ሊግ ተጫዋቾች በጥር የዝውውር መስኮት ስማቸው  በሊጉ አልያም ከሊጉ ውጭ ባሉ ክለቦች ጋር እየተያያዘ ነው። ከእነዚህም ውስጥ የamንችስተር ሲቲው ካልቪን ፊሊፕስ ስሙ ከኒው ካስል እና የጣልያኑ ጁቬንቱዝ ጋር ሲያያዝ የማንችስተር ዩናይትዱ የደን ሳንቾ ከጀርመኑ ቦሩስያ ዶርትመንድ ጋር ተነስቷል። የታኅሣሥ 15 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባየዴቪድ ራያን መምጣት ተከትሎ ከአርቴታ የቋሚ አሰላለፍ ርቆ የቆየው በረኛው አሮን ራምስደልን ለማዘዋወር ቼልሲ እና ኒውካስል ፍላጎት ማሳየታቸው ተዘግቧል። 

የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን አጥቂ ሊዮኔል ሜሲምስል Jia Haocheng/Xinhua/picture alliance

የብሬንት ፎርዱ አጥቂ ኢቫን ቶኒ ደግሞ በአርሰናሎች የአጥቂ ፍላጎት መዝገብ ውስጥ መካተቱን መረጃዎች ያመለክታሉ ። የፉልሃሙ የመሃል ተጫዋች ከባየር ሙኒክ ፣ አርሰናል እና ሊቨር ፑል ጋር ሲያያዝ የአርሰናሉን የተከላካይ አማካይ ቶማስ ፓርቴን ለማዘዋወር ጁቬንቱሶች ፍላጎት እንዳላቸው የተነገረው።  ሌሎች ዋነኞቹ የአውሮጳ ሊጎች የገና ሰሞንን በእረፍት አሳልፈው ከነገ ጀምሮ ወደ ውድድር ይመለሳሉ ተብሎ ይጠበቃል። 
በመጨረሻ አርጀንቲና የዓለም ዋንጫ አሸናፊው እና ኮከቧ ሊዮኔል ሜሲ የሚለብሰው አስር ቁጥር ማሊያ እርሱ በጡረታ ከተገለለ በኋላ ጥቅም ላይ እንደማይውል ይፋ አድርጋለች። የአርጀንቲና እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ክላውዲዮ ታፒያ እንዳሉት ሜሲ 10 ቁጥር ማሊያው ለዘላለም መታሰቢያው ይሆንለታል ። ይህ ሀገሩ ልታደርግለት የምትችለው የመቸረሻው ትንሹ ነገር ነው ብለዋል። ሜሲ ለሀገሩ አርጀንቲና 108 ጨዋታዎችን አድርጎ 106 ግቦችን በማስቆጠር የአርጀንቲና የምንጊዜም ባለውለታ መሆን ችሏል፡፡ የአርጀንቲና እግር ኳስ ፌዴሬሽን ካሁን ቀደምም 10 ቁጥር ማሊያ ከማራዶና በኋላ እንዳይለበስ ወሰኖ የነበረ ቢሆንም ዓለማቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ ውሳኔውን ውድቅ በማድረጉ ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቷል። የአሁኑ ውሳኔስ በእርግጥ ይጸና ይሆን ጊዜ ይመልስዋል። እንግዲህ አድማጮች ለዛሬ ያልናቸው ስፖርታዊ መረጃዎቻችንም የእስካሁኑን ይመስሉ ነበር ፤ ለአብሮነታችሁ ምስጋናችን ትልቅ ነው። ጤና ይስጥልን።

ታምራት ዲንሳ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሄር

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW